አትሌት ኮማንደር ስለሺ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ፕሬዚደንት ሆኖ ተመረጠ።
አትሌት ኮማንደር ስለሺ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ሆኖ ተመረጠ። ስለሺ የቀድሞዋ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን በመተካት ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን ይመራል። ፌዴሬሽኑን በፕሬዚደንትነት ለመምራት ከተለያዩ ክልሎች አራት ዕጩዎችን ባወዳደረው የዛሬው ምርጫ የኦሮሚያ ክልልን የወከለው ስለሺ 11 ድምጾችን ሲያገኝ ፤ የትግራይ ክልልን የወከለው አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማሪያም በ9 ድምጾች ሁለተኛ ሆኗል። የአማራ ክልልን ወክለው የተወዳደሩት አቶ ያየህ አዲስ ደግሞ 4 ድምጾችን በማግኘት ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ብሎም የየሀገሪቱን የስፖርት ኮሚሽን በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በመወከል ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ ዱቤ ጅሎ ድምጽ ሳያገኙ ቀርተዋል። በ28ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉባኤ ላይ ፕሬዚዳንት ሆኖ የተመረጠው አትሌት ስለሺ ስህን በአቡጃ የመላው አፍሪቃ ዋንጫዎች የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም የሄልሲንኪ እና የኦሳካ የዓለም ሻምፒዮናዎችን ጨምሮ ለኢትዮጵያ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያዎችን አስገኝቷል። በተጨማሪ በጉባኤው በተደረገው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ አንጋፋዋ አትሌት መሠረት ደፋር መካተቷ ታውቋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሀገሪቱ የአትሌቲክስ ውጤት መውደቅ ኃላፊነት አለበት የሚል ተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል።
በናይጄሪያ የምግብ ርዳታ ለመቀበል በተሰበሰቡ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 32 መድረሱን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።
በናይጄሪያ የምግብ ርዳታ ለመቀበል በተሰበሰቡ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 32 መድረሱን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ። አደጋው የደረሰው በደቡባዊ ናይጄሪያ በምትገኘው ኦኪጃ ከተማ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የምግብ ርዳታ በሚያቀርብ ቤተክርስትያን ደጅ ትናንት ቅዳሜ ግጭት ከደረሰ በኋላ ነው። ለአረጋውያን እና ለምግብ እህል እጥረት ለገጠማቸው ሰዎች የሚቀርበውን ሩዝ ለመቀበል በተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ተፈጠረ በተባለው ግጭት ህጻናትን ጨምሮ 22 ሰዎች መገደላቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። አደጋው እንዴት እንደተከሰተ በመመርመር ላይ እንደሚገኝ የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።
የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በማድቡርግ ከተማ በገና የገበያ ስፍራ የደረሰውን አደጋ ለመመርመር ቃል ገቡ።
የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በማግድቡርግ ከተማ በገና የገበያ ስፍራ ለደረሰው እና ለአምስት ሰዎች ሞት እንዲሁም ከ 200 በላይ ሰዎች መጎዳት ምክንያት የሆነውን በመኪና በመግጨት በተፈፀመ ጥቃት የጸጥታ አካላት አስቀድመው መከላከል ይችሉ ነበር ወይ የሚለውን ለማጣራት ቃል ገቡ ።
የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር እና የሀገር ውስጥ እና የውጭ የስለላ አገልግሎት ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡበት የፊታችን ጥር 1 ቀን 2017 ዓ ም ፓርላማ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሀገር ውስጥ ሚንስትሯ እና የደህንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎቹ ፓርላማ የሚቀርቡት ሁለት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት መልስ እንዲሰጥበት ከጠየቁ በኋላ ነው ተብሏል።
በከተማዋ የደረሰውን የተሽከርካሪ አደጋ ፈጽሟል ተብሎ በቁጥጥር ስር የዋለው ሳዑዲ አረቢያዊ የስነ አዕምሮ ሀኪም ጣሊብ አል አብዱልሞሀሰን የጀርመን ዜጎችን ለመግደል ይዝት እንደነበር ከኢንተርኔት የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል። በተጨማሪም የ50 ዓመቱ ግለሰብ አስቀድሞ ፍርድ ቤት የቀረበበት ጉዳይ እንደነበረው እና ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል።
ዴር ሽፒግል የተባለ አንድ የጀርመን ጋዜጣ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው የሳዑዲ ሚስጥራዊ አገልግሎት ከአንድ ዓመት በፊት ለጀርመን የስለላ መስሪያ ቤት BND አብዱልሞሀሰን በቲውተር ገጹ ጀርመንን ለማስፈራራት ያሰፈረው መልዕክት በጀርመን ላይ አደጋ ይዞ ሊያመጣ እንደሚችል አስጠንቅቆ እንደነበር ነው።
በተጨማሪም ተጠርጣሪው ግለሰብ ባለፈው የነሐሴ ወር በማህበራዊ የመገናኛ ገጾቹ ላይ ባሰፈራቸው ጽሁፎቹ «በጀርመን ፍትህን ለማግኘት ኤምባሲዎቿን ከማፈንዳት እና ዜጎቿን ከመግደል ያለፈ መንገድ ይኖር ይሆን?» ሲል መጻፉም ተመላክቷል።
የሀገር ውስጥ ሚንስትሯ ይህንኑ በተመለከተ እንዳሉት « "የምርመራ ባለስልጣናት ከጥቃቱ በፊት ምን አይነት መረጃ ነበራቸው የሚለውን ጨምሮ ምን አይነት ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር ሁሉንም ዳራዎች ያብራራሉ» ብለዋል።
የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ ሌላው ዕለታዊ ጋዜጣ ዲ ቬልት እንደዘገበው ደግሞ የጀርመን ግዛት እና የፌደራል ፖሊስ ባለፈው አመት አብዱልሞሀሰን ላይ “የአደጋ ግምገማ” ቢያካሂዱም “ምንም የተለየ አደጋ” የሚያስከትል ነገር የለም በማለት ደምድመዋል።
በየመን የሁቲ አማጽያን ይዞታ የማጥቃት ተልዕኮ ላይ የነበረ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ተመትቶ ወደቀ።
በየመን የሁቲ አማጽያን ይዞታ የማጥቃት ተልዕኮ ላይ የነበረ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ተመቶ ወደቀ። የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ግን በህይወት መትረፋቸው ተሰምቷል።
በቀይ ባህር ላይ ይበር በነበረ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ላይ በስህተት ተፈጸመ በተባለ ጥቃት በአንድ አብራሪ ላይ መጠነኛ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ሁለቱም በህይወት መትረፋቸውን የአሜሪካ ጦር አስታውቋል። የጦር አውሮፕላኑ በየመን ኢላማ የተደረጉ የሁቲ አማጽያን ወታደራዊ ይዞታዎችን ደብድቦ በመመለስ ላይ ነበር ተብሏል።
የአሜሪካ ጦር ኃይል እንዳለው አውሮፕላኑ ሃሪ ትሩማ በተሰኘ የአሜሪካ ባህር ኃይል አቅራቢያ እየበረረ በነበረበት ወቅት በስህተት መመታቱን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ CENTCOM ገልጿል።
የሁቲ አማጽያን የፍልስጤሙን ታጣቂ ቡድን ሃማስን በመወገን በእስራኤል ላይ በቀጥታ ሚሳኤሎች መተኮስን ጨምሮ በቀይ ባህር ላይ በሚመላለሱ የንግድ መረከቦች ላይ ተከታታይ ጥቃት በማድረስ ይታወቃሉ።
የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ትናንት ቅዳሜ በካዛን ከተማ ለፈጸመችው የድሮን ጥቃት የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናገሩ ።
የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ትናንት ቅዳሜ በካዛን ከተማ ለፈጸመችው የድሮን ጥቃት የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናገሩ ። ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት «ማንም በግዛታችን በሚያደርሰው ጥቃት ለሚፈጠረው ጥፋት አጸፋውን በእጥፍ ይቀበላል ፤ በስራቸውም ይጸጸታሉ ብለዋል። ዩክሬን ትናንት ቅዳሜ በካዛን በሚገኙ የመኖሪያ ህንጻዎች እና የኢንዱስትሪ መንደር ሰባት የድሮን ጥቃቶች መፈጸሟን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዲ ፒ ኤ ዘግቧል። በጥቃቱ የከፋ ጉዳት የደረሰበት ሰው አለመኖሩን ዘገባው አመልክቷል። ዩክሬን ግን ለጥቃቱ ኃላፊነት አልወሰደችም ። ካዛን ከዩክሬን ከ1 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት ።
ታምራት ዲንሳ
ልደት አበበ