1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ክልል ብድር ጠየቀ፣ ደሞዝ መክፍል ተስኖታል

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 17 2016

በትግራይ የሚገኙ በአጠቃለይ 131 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች ሊከፈለን ይገባል ያሉት የ2014 ዓመተምህረት ሙሉ ዓመት፣ የ2015 ዓመተምህረት 6 ወራት የተከማቸ ደሞዝ እስካሁን አለማግኘታቸው ተከትሎ የተለያዩ ቅሬታዎች እያሰሙ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/4aclq
ትግራይ ክልል የሚኖሩ ጡረተኞች አበል አልተከፈላቸዉም
የጡረታ አበል ያልተከፈላቸዉ የትግራይ ክልል ጡረተኞች ሰልፍምስል Million Haileselassie/DW

የትግራይ ክልል ብድር ጠየቀ፣ ደሞዝ መክፍል ተስኖታል

 

የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግስቱ ብድር መጠየቁን አስታወቀ። የክልሉ አስተዳደር የተከማቸ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ እንዲሁም የጡረታ አበል ለመክፈል መቸገሩን ገልጿል። የትግራይ ክልል መምሕራን ዉዝፍ ደሞጣቸዉ እንዲከፈል ከዚሕ ቀደም በተደጋጋሚ ላቀረቡት  ጥያቄ ተገቢ መልስ ባለማግኘታቸዉ በአንዳንድ ቦታዎች ስራ ማቆማቸዉ ተነግሯል።

በትግራይ የሚገኙ በአጠቃለይ 131 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች ሊከፈለን ይገባል ያሉት የ2014 ዓመተምህረት ሙሉ ዓመት፣ የ2015 ዓመተምህረት 6 ወራት የተከማቸ ደሞዝ እስካሁን አለማግኘታቸው ተከትሎ የተለያዩ ቅሬታዎች እያሰሙ ይገኛሉ። 

ከእነዚህ መካከል የሆኑት በትግራይ ክልል የሚገኙ 45 ሺህ መምህራን የተከማቸ የ18 ወር ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት ቅሬታ ከማሰማት አልፎ በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በተለይም ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ ስራ እያቆሙ እንዳለ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ብር
የትግራይ ክልል ከፍተኛ የበጀት እጥረት አጋጥሞታልምስል Solomon Muchie/DW

ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንደገጠመው የሚገልፀው የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር በበኩሉ፥ የመንግስት ሰራተኞቹ ጥያቄ አግባብነት ያለው ብሎ የሚቀበለው ቢሆንም፥ በበጀት መጓደል ምክንያት ግን የአስተማሪዎቹ ጨምሮ የሁሉም መንግስት ሰራተኞች ውዝፍ ክፍያ መክፈል አለመቻሉ ይገልፃል። የትግራይ ክልል ፋይናንስ እና ሐብት ማሰባሰብ ቢሮ ሐላፊ ዶክተር ምሕረት በየነ እንደሚሉት ከፌደራል መንግስቱ ለትግራይ የሚሰላ የበጀት መጠን ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር እኩል መሆኑ የሚያነሱ ሲሆን ይህም ከወቅቱ ፍላጎቶች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ በመሆኑ በክልሉ ከፍተኛ የበጀት እጥረት መከሰቱ ይገልፃሉ። እንደ የትግራይ ፋይናንስ ቢሮ ገለፃ፥ የ2014 ዓመተምህረት ሙሉ፣ ከ2015 ዓመተምህረት በጀት ዓመት ደግሞ 2 ነጥብ 6 ቢልዮን ብር በጀት ለትግራይ አልተለቀቀም። ይህ ለማግኘት ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሚሻም ሐላፊዋ ዶክተር ምህረት ያነሳሉ። ዶክተር ምሕረት"የተሟላ በጀት አላገኘንም። የ2015 ዓመተምህረት መምጣት የነበረበት 2 ነጥብ 6 ቢልዮን አልተለቀቀም። የ2014 ዓመተምህረት ደግሞ ምንም የለም። ይህ የበጀት መጓደል ለመፍታት የራሱ አሰራር አለ። ፖለቲካ ውሳኔ ያስፈልገዋል" ይላሉ።

የክልሉ አስተዳደር የገጠመው ከፍተኛ የበጀት ክፍተት ለመሙላት ለፌደራል መንግስቱ የብድር ጥያቄ ማቅረቡም የትግራይ ፋይናንስ እና ሐብት ማሰባሰብ ቢሮ ሐላፊዋ ዶክተር ምሕረት በየነ ጨምረው ገልፀዋል። ሐላፊዋ "ብድር እንጠይቅ ተብሏል። በሁለት ዓመት የሚከፈል ብድር ጠይቀናል። በሚቀጥሉት ዓመታት በኢኮኖሚ ረገድ እንሻሻላለን፣ ገቢም እናገኛለን፣ ኢኮኖሚው ይነቃቃል፥ ከዚያ በሚገኝ የውስጥ ገቢ የሚሸፈን ብድር ነው የጠየቅነው። የመንግስት ሰራተኛ ደሞዝ እንደምንከፍል ቃል ገብተናል። አንስተን የምንሰጠው ገንዘብ ግን የለም። ስለዚህ አንዱ ተስፋ ብድር ነው። ይህ ደግሞ ሂደት ላይ ነው" ብለዋል።

በጦርነቱ የተጎዳዉ ኤኮኖሚ አላንሰራራም
ትግራይ ክልል በጦርነቱ ክፉኛ ተጎድቷልምስል Amanuel Sileshi/AFP

እንደ የክልሉ አስተዳደር ገለፃ ባለፈው ዓመት የፌደራል መንግስቱ ለትግራይ 12 ቢልዮንብር ገደማ በጅቶ የነበረ ሲሆን ከዚህ መካከል ግን 2 ነጥብ 6 ቢልዮኑ ሳይለቀቅ የበጀት ዓመቱ ተጠናቋል። አሁን ላይ ባለው መረጃ መሰረት የትግራይ አስተዳደር በየወሩ 1 ነጥብ 2 ቢልዮን ብር ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ይከፍላል። በጦርነቱ ምክንያት ባለፉት ዓመታት ከውስጥ እንቅስቃሴ ገቢ መሰብሰብ እንዳልቻለ የሚገልፀው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ይህም ከበጀት ድጎማው ማነስ ጋር ተደምሮ ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ፈጥሯል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የ18 ወር ውዝፍ ደሞዛቸው ባለመከፈሉ በከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ እንዳሉ የሚገልፁት በትግራይ ያሉ አጠቃላይ መንግስት ሰራተኞች፥ በተለይ ደግሞ መምህራን ይገባናል ያሉት ውዝፍ ክፍያ ባለማግኘታቸው ስራ እያቆሙ ይገኛሉ። የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ሐላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ የመምህራኑ ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም ስራ በማቆም አድማ ምላሽ አይገኝም ብለዋል። ዶክተር ኪሮስ "ትምህርት ማቋረጥ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ትውልድን ስለሆነ፣ ጉዳቱም እንደ ትግራይ ስለሆነ፣ በማቋረጥም የሚፈታ ችግር ስለሌለ፣ የሚያግዘንም ስለሌለ፥ ተጎጂ የሚሆኑት ልጆቻችን አጠቃላይ ህዝባችን መሆኑ መገንዘብ አስፈላጊ ነው" ሲሉ አክለው ገልፀዋል።

ሰልፍ በማድረግ ጨምር በተለያዩ መንገዶች ጥያቄአቸው ሲያቀርቡ የቆዩት የትግራይ መምህራን፥ ላቀረቡት ጥያቄ ከመንግስት ምላሽ በማጣታቸው በማሕበራቸው በኩል አንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ውይይት ላይ መሆናቸው ገልፀዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ