የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ እንደ አዲስ ይቋቋም ጥሪ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2017በትግራይ ክልል ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ ዳግም እንደ አዲስ እንዲቋቋም ተቃዋሚው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ጥሪ አቀረበ ። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት አልተወጣም፥ ይልቁኑስ የትግራይ ክልል ጥቅሞችን አሳልፎ እየሰጠ ነው ሲል ተቃዋሚው ፓርቲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተችቷል። በሌላ በኩል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ አማካሪ ያለውን ምክር ቤት እንደሚያቋቁም ገልጿል። የመቐለ ወኪላችን ዝርዝሩን ልኮልናል ።
«ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚጠበቅበት አልተወጣም» ተቃዋሚዎች
ከሁለት ዓመቱ ጦርነት በኋላ፥ በዋነኝነት በትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር እንዲኖር በ2015 ዓመተ ምህረት መጋቢት ወር የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ አይደለም ተብሎ በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተተቸ ይገኛል ። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይጠበቅ እንደነበረው የጦርነቱ ተፈናቃዮች አልመለሰም፣ የትግራይ ክልል ግዛት አላስከበረም፣ ሰላም እና ፀጥታ አላረጋገጠም የሚሉ ተቃዋሚዎች እና ሌሎች ተቺዎች ይህን ሁኔታ ለመቀየር ደግሞ የተለያዩ ሐሳቦች ያቀርባሉ።
በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሆነው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፥ የሚጠበቅበት ኃላፊነት መወጣት አልቻለም ያለው አሁን ላይ ያለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ እንደገና ሊቋቋም ይገባል ሲል ገልጿል። የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ኃይሉ «ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደገና እንዲቋቋም፥ ይህ ለማቋቋም ደግሞ ብሔራዊ ጉባኤ እንዲጠራ እና የተለያዩ አካላት ያካተተ ግዚያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት ነው ጥሪ የምናቀርበው። እሱን ተከትሎ ደግሞ ጠንካራ ምክር ቤት ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲኖረው ነው ጥሪ እያቀረብን ያለነው» ብለዋል።
የሕወሓት በሁለት ቡድኖች ተከፍሎ መፋጠጥ አስተዳደሩን አዳክሟል ተብሏል
ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበላይነት የተቆጣጠረው ሕወሓት በሁለት ቡድኖች ተከፍሎ የሚያደርገው ፍጥጫ አስተዳደሩን ከማዳከም በዘለለ፥ የትግራይ ክልል ጥቅሞችንም አሳልፎ የሰጠ ሆኗል ሲል ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አብራርቷል። የፓርቲው የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ካሳ «ሥልጣን ላይ ባሉ ሁለት ቡድኖች መካከል ያለው ፖለቲካዊ መሳሳብ፥ የትግራይ ወሳኝ አጀንዳዎች ለማስፈፀም በፌደራል መንግስቱ ላይ ጫና መፍጠር አልቻለም፣ ፍላጎት የለውም። ይህ ለምን ቢባል በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ፍጥጫ አንዱ ላላው ለማሸነፍ የፌደራል መንግስቱ ድጋፍ ስለሚሹ፥ የትግራይ ጥቅሞች መጠየቅ ደግሞ የፌደራል መንግስቱን ማስጨነቅ ስለሆነ፥ ለራሳቸው የቡድን ጥቅም ሲሉ የትግራይ ብሔራዊ ጥቅም ለፖለቲካዊ ፍጆታ እየተጠቀሙበት ነው» ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ በቅርቡ በጋራ ለመሥራት ቃል ኪዳን የገቡት ሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ እና ባይቶና በበኩላቸው በትግራይ ክልል ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ሁሉን አካታች ምክርቤት እንዲኖረው ጠይቀዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከወራት በፊት አማካሪ ያለውን ምክርቤት እንደሚያቋቁም አሳውቆ ነበር። ይሁንና ይህ ለረዥም ግዜ አልተፈፀመም። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ሳምንት አድርጎት ከነበረ ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፦ አማካሪ ካውንስል በአስቸኳይ እንዲቋቋም አቅጣጫ ተቀምጧል ብሏል። ይሁንና በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከግዚያዊ አስተዳደር ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስሺ
እሸቴ በቀለ