የትግራይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት ይቋቋም ጥያቄ
ቅዳሜ፣ ጥር 6 2015በስምምነቱ መሰረት በትግራይ የሽግግር አስተዳደር እንዲቋቋም በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ዓረና ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ እንዲሁም ዓሲምባ ዴሞክራስያዊ ፓርቲዎች እንዳሉት በትግራይ የነበረው ክልላዊ መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት መፍረሱ በመጥቀስ አዲስ የሽግግር አስተዳደር እንዲቋቋም፥ ቀጥሎም በምርጫ ሕጋዊ መንግስት ሊመሰረት ይገባል ብለዋል።
በትግራይ በተቃውሞ የፖለቲካ ረድፍ የሚንቀሳቀሱት ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እና ዓሲምባ ዴሞክራስያዊ ፖርቲ የተባሉ ሶስት የፖለቲካ ድርጅቶች በየፊናቸው እንደገለፁት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እንዲሁም ክልሉ የሚያስተዳድር ሕጋዊ አካል አለመኖሩ በመጥቀስ፥ በትግራይ ግዚያዊ የሽግግር አስተዳደር እንዲመሰረት ጥሪ አቅርበዋል። የዓሲምባ ዴሞክራስያዊ ፖርቲ ሊቀመንበር አቶ ሐጎስ ወልዱ ለዶቼቬለ እንደገለፁት፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ "ሕጋዊ አስተዳደር ባለመኖሩ የመንግስት መዋቅር በሚገባ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ አልተፈጠረም ያሉ ሲሆን ይህ ችግር ለመፍታት "በሰላም ስምምነቱ መሰረት በትግራይ የሽግግር አስተዳደር ሊቋቋም ይገባል" ሲሉ ገልፀዋል።የመንግሥትና ህወሓት ድርድርና የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስተያየት
ከዚህ በተጨማሪ በወቅታዊ የትግራይ ሁኔታ ዙርያ መግለጫ የሰጠው የትግራይ ነፃነት ፖርቲ፣ በፕሪቶሪያው ውል መሰረት በትግራይ የነበረው ክልላዊ መንግስት ፈርሷል፣ በምርጫ ሕጋዊ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ ሁሉ አካታች የሽግግር አስተዳደር በትግራይ ሊመሰረት ይገባል ሲል ገልጿል። የትግራይ ነፃነት ፖርቲ ኮምኒኬሽን ሐላፊ ዶክተር ደጀን መዝገቡ "መንግስት መፍረስ ማለት ቀላል አደጋ አይደለም። ህወሓት እየሄደበት ያለው የምስለኔ ልሁን ልመና ደግሞ፥ ወደባሰ አደጋ የሚከተን፣ የትግራይ ብሄራዊ ትግልን ወደ መጥፎ ሁኔታ የሚወስድ ስለሆነ፤ በአፋጣኝ ምርጫ አድርገን ሕጋዊ መንግስት መቋቋም ስላለበት፤ ሁሉም የትግራይ ሐይሎች የሚያቅፍ የሽግግር መንግስት በአፋጣኝ እንዲቋቋም እንደ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ እንጠይቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጥቃቄ
የሁለት ዓመቱ ጦርነት መቆሙ፣ የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱ፣ በሂደት ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ መግባት፣ አገልግሎቶች መከፈት መጀመራቸው ያደነቀው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ በበኩሉ በውሉ መሰረት ያልተፈፀሙ ያላቸው በትግራይ የሽግግር አስተዳደር ማቋቋም ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ሊፈፀሙ ይገባል ብሏል። የዓረናው ከፍተኛ አመራር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ "የኤርትራ ጦር ጨምሮ ሌሎች ታጣቂዎች ከትግራይ ሊወጡ እንጠብቃለን፣ ከዚህ በተጨማሪ የሽግግር መንግስት የማቋቋም ተግባርም ይፈፀማል ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ የገለፁ ሲሆን የሽግግር አስተዳደሩም ሁሉ አካታች እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ