የትግራይና የአማራ ክልሎች ልዩነታቸዉን በዉይይት እንዲፈቱ ነዋሪዎች እየጠየቁ ነው
ዓርብ፣ መጋቢት 20 2016
ሰሞኑን በትግራይና በዐማራ ክልሎች መካከል እንደ አዲስ የተካረረዉ የቃላት “እንካ ሰላንትያ” ያሰጋቸዉ ነዋሪዎች ክልሎቹ ልዩነቶቻቸዉን በውይይት እንዲፈቱ ጠየቁ።በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በትግራይና በዐማራ ክልሎች መስተዳድሮች መካከል የተፈጠረዉ መቃቃር እስካሁን ሁነኛ መፍትሔ አላገኘም።ሰሞኑን ደግሞ ሁለቱ ክልሎች የቃላት አሰጥ አገባ ገጥመዋል።ሁለቱን ክልሎች የሚያዋስኑ አካባቢዎች ነዋሪዎች እንደሚሉት መወቃቀስ መወጋገዙ የከፋ ችግር እንዳያስከትል ዉይይት መደረግ አለበት።
ከነገ ዛሬ የተሻለ የሰላም ሁኔታ ይመጣል ብለው የሚጠብቁ የትግራይና የአማራ ክልል ነዋሪዎች ሰሞኑን በሁለቱ ክልል መንግስታት መካከል እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው የቃላት እንካ ሰላንትያ ግን ደስተኞች አይደሉም፡፡አንድ የዝቋላ ወረዳ ነዋሪ ካሳለው ችግር መማር ካልተቻለና እንደገና ወደ ጦርነት የሚገባ ከሆነ የባሰ ችግር ውስጥ ስገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ ነዋሪው አስተያት፣ የነበረው ጦርነት ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ሳያልፍ ሌላ ግጭት የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች መቆም አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ሌላ የጦርነት ቀውስ በአካባቢው ከተፈጠረ ህብረተሰቡ እንዳይነሳ ሆኖ ይጎዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ህብረተሰቡ እንግልትና ተጨማሪጉስቁልና ሳይደርስበት መንግስት የደቡብ አፍሪካውን ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርግ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን የአዋሳኝ አካባቢ ነዋሪዎች የሚናገሩት፡፡ህብረተሰቡ እስካሁን የከፈለው ዋጋ በቂ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ችግሮቹ ሳይውሉ ሳያድሩ በሰላም የሚቋጩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው ያሳሰቡት፡፡
“የሚፈራው ግጭትና ጦርነት እንዳይመጣ መንግስት ኃላፊነት ወስዶ በስምምነቱ መሰረት (በፕሪቶሪያው) መፈታት አለበት፣ ህብረተሰቡ እስካሁን የከፈለው ዋጋ ከበቂ በላይ ነው፡፡”ብለዋል፡፡
አሁን በሁለቱም ክልሎች መካከል የተጀመረው የቃላት ልውውጥ ባስቸኳይ ካልቆመ ውጤቱ እንደሚከፋ የገለጡልን ሌላ አስተያየት ስጪ ነገሮች በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እንዲቋጩ ጠይቀዋል፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት የሰላም አየር እንድንተነፍስ ምክንት ሆኗል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁንም ባለው የኑሮ ውድነት ላይ ጦርነት ከተጨመረበት ከፍተኛ ማሕበራዊ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም ወደ ሰላም ፊቱን እንዲያዞርና የሰላም ስምምነቱን በዘላቂነት ማስፈፀም ተገቢ እንደሆነነ ነው ያመለከቱት፡፡አማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፋንታው የትግራይና የአማራ ህዝብ በሁሉም ዘርፍ ወንድማማች ህዝብ በመሆኑ ችግሮች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ብቻ መሰረት በማድረግ በሰላማዊ መንገድ ይፈታሉ ብለዋል፡፡
“ህዝባችን ሰላም ወዳድ ነው፣ የትግራይ ህዝብ ወንድም እህታችን ነው፣ ከወንድም እህት ህዝብ ጋር አብረን በሐይማኖት፣ በባህል በጋብቻ፣ በኢኮኖሚ ከተሳሰረው ህዝባችን ጋር ዳግም ወደ ጦርነት አንገባም፣ ስለዚህ (ችግሮች) በሰላማዊ መንገድ እንዲያልቁ እንፈልጋለን፣ በተቀመጠው የፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ጉዳዮቹ መታየት አለባቸው፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ይህን እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፡፡” ነው ያሉት፡፡
ለትግራይ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ኃለፎም ከትናንት ጀምሮ በእጅ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብደውልም መልስ አላገኘሁም፣ ሆኖም ከጥቂት ቀናት በፊት ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት መግለጫ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ችግሮችን በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡“የፕሪቶሪያውን ውል ተከትለን ነው መፈፀም የምንፈልገው፣ ነገር ግን በውሉ መሰረት ደግሞ የኢፌድሪ መንግስት እነሱን (የአማራ ታጣቂዎችን) የማስወጣት ኃላፊነት አለበት፣ እነሱን እንዲያስወጣ ከፌደራል መንግስት ጋር ነው በቀጣይ ንግግር የምናደርገው፣ እነሱ የማደናቀፍ ስራ ነው እየሰሩት ያለው፣ ይህ የሚጠቅም አይመስለኝም” ብለው ነበር፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሰሞኑን “የአማራ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር በመማሪያ መጽሐፍት ላይ የትግራይ ክልል አካል የሆኑ አካባቢዎችን በካርታው ውስጥ አካቶ ማውጣቱ «ጠብ አጫሪነት» ነው” በሚል መግለጫ ያወጣ ሲሆን የአማራ ክልል መንግስት ባወጣው የአፃፋ ምላሽ « የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሀገሪቱ ቋሚ የቀውስ ምንጭ ከሚያደርጉት ተግባራት እንዲታቀብና ከአጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር እንመክራለን» ብሏል።
አለምነዉ መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ