1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

የአላማጣ ከተማ ትምህርት እና የነዋሪዎች አቤቱታ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2017

በአላማጣ ከተማ የመማር ማስተማር ስራው ለወራት ባለመጀመሩ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አለመቻላቸውን የተማሪ ወላጆች ተናገሩ ። በከተማዋ ትምህርት ቤቶች ወደ ጦር ሰፈርነት በመቀየራቸው መምህራን ከስራ ገበታቸው ውጪ እንዲሆኑ ማስገደዱን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው መምህራን ገልጸዋል። በጉዳዩ ከከተማዋ የወታደራዊ ዕዝ መልስ ማግኘት ግን አልተቻለም

https://p.dw.com/p/4oYKl
Äthiopien Konflikt Tigray | Alamata
ምስል DW

የአላማ ከተማ ለማህበራዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮች ተጋልጣለች፤ ነዋሪዎች

 

የአላማጣ ነሪዎች ቅሬታ

በአላማጣ ከተማ የመማር ማስተማር ስራው ለወራት ባለመጀመሩ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አለመቻላቸውን የተማሪ ወላጆች ተናገሩ ። በከተማዋ ትምህርት ቤቶች ወደ ጦር ሰፈርነት በመቀየራቸው መምህራን ከስራ ገበታቸው ውጪ እንዲሆኑ ማስገደዱን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው መምህራን ገልጸዋል። በአላማጣ ከተማ ትምህርት አልተጀመረም መባሉን በተመለከተ ዶቼቬለ ለከተማዋ የወታደራዊ ዕዝ ኃላፊ ቢደውልም ሊያገኛቸው አልቻለም ። በትግራይ ክልል የደቡባዊ ዞን አስተዳደር በበኩሉ በከተማዋ ከጥቂት ትምህርት ቤቶች በስተቀር በርካቶች የመማር ማስተማር ስራዉን እያከናወኑ መሆኑን መረጃ እንዳለው ገልጾ ከተማዋ በወታደራዊ ዕዝ ስር በመሆኗ ለበርካታ ማህበራዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮች ተጋልጣለች ብሏል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የአላማጣ ከተማ ነዋሪ እንዳሉት በአላማጣ ከተማ የ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ አለመጀመር ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ አላስቻለንም ብለዋል።

አማራና ትግራይ የሚወዛገቡባቸው የራያ አካባቢዎች ሰሞናዊ ሁኔታ

ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አልቻልንም

«ባለፈው ሚያዝያ ሰባት መጡ መጡ ሲባል ሁሉም ሸሽቶ ሄዶ ነበር ። ከዚያ በኋላ ተስተካክሎ ከግንቦት 25 አካባቢ ጀምሮ ያ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ተጠናቆ ተማሪዎቹ እንዲያልፉ ተደርጓል። ከዚያ በኋላ መስከረም ነው እንግዲህ አሁን የ2017 ዓ.ም. የመማር ማስተማር ፕሮግራም እንደማንኛውም የኢትዮጵያ አካባባቢ ትምህርት ቤቶች መጀመር ነበረበት ፤ እሱ እንዲጀመር ፍቃደኛ አልሆኑም።  » 

በከተማዋ መምህር እንደሆኑ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው በከተማዋ የመማር ማስተማር ስራው መስተጓጎል በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል ያለው እሰጥ አገባ ያስከተለው  የመማሪያ ቋንቋ ጥያቄ ነው ይላሉ።

«ምንድነው መሰል በሁለቱ ክልሎች እሰጥ አገባ ውስጥ አይደል ቦታው ፤ አሁን ይህ እሰጥ አገባ ድንገት በ,ዚያኛው ክልል በክልል ሶስት ያው በራሴ ላስተምር በራሴ ቋንቋ በሚል አብዛኛው መምህርም ከዚያ ጋር በተያያዘ  ያው ቅሬታ አለ።  መከላከያ ደግሞ አይ አታስተምሩም አንድ ቅሬታ ያለው።»

ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የከተማዋ አስተዳደር አመራር እንደነበሩ የነገሩን ነዋሪ እንዳሉት በከተማዋ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ጥረቶች ቢደረጉም «ሌላ አካል » ፈጠረ ባሉት ችግር አለመሳካቱን ተናግረዋል ።

ከአማራ ወደ ትግራይና ከትግራይ ወደ አማራ ክልል በመመለስ ላይ ያሉ ተፈናቃዮችና ስጋታቸው

«ህብረተሰቡ ልጆቹን ማስተማር ይፈልጋል ። ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አለባቸው። ሌሎቹም ቢሆኑ አልባሌ ቦታ ከሚውሉ ገበታ ላይ ውለው ትምህርት ቀስመው ቢመለሱ መልካም ነው የነበረው ። ትምህርት እንዳይጀመር እየተደረገ ያለው ግን በሌላ አካል ነው። »

አስተያየት ሰጭው እንደሚሉት በተለይ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር ያለባቸው ህጻናትተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ከተማዋን ለሚቆጣጠረው ወታደራዊ ዕዝ ቢያመለክቱም ከቃል ያለፈ ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም ባይ ናቸው ።

የአላማጣ ከተማ
በከተማዋ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ጥረቶች ቢደረጉም «ሌላ አካል » ፈጠረ ባሉት ችግር አለመሳካቱን ተናግረዋል ።ምስል Fikru Eshsiebel

« ህጻናት ደግሞ መማር አለባቸው ። እስካሁን አራት ወር አለፈ እንግዲህ ። ትምህርት መጀመር ከነበረባቸው ። ስለዚህ የህብረተሰቡ ሰፊ የሆነ የህጻናቱን ጥያቄ ስለነበር ትምህርት ለማስጀመር ያው ለአካባቢው ኮማንድ ፖስት አሳወቅን እንድንጀምር ግን የተፈቀደበት ሁኔታ የለም። የተወሰነ አንድ ሁለት ብሎክ እንሰጣለን አሉ ፤ ወደ ተግባር ስንሄድ ደግሞ እሱም ቢሆን ቆመ»

ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ መመለሳቸው

የከተማዋ ወታደራዊ ዕዝ መልስ ማግኘት አልተቻለም

በአላማጣ ከተማ የመማር ማስተማሩ ስራ በተመለከተ ትምህርት አልተጀመረም መባሉን በተመለከተ ከነዋሪው ለቀረበ አቤቱታ መልስ ለመሻት  ለከተማዋ የወታደራዊ ዕዝ ኃላፊ ኮሎኔል አህመድ  በእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ስልካቸው ባለመመለሱ በዘገባው ለማካተት አልተቻለም ።

እንዲያም ሆኖ ግን የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አስተዳደር በአላማጣ ከተማ እና በዙሪያ ከጥቂት ትምህርት ቤቶች በቀር አብዛኞቹ የመማር ማስተማር ስራቸዉን እያከናወኑ መሆኑን አስተዳደሪው አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ተናግረዋል።

« አላማጣ ከተማ 11 ትምህርት ቤቶች ናቸው ያሉት ፤ ከአስራ አንዱ ትምህርት ቤቶች ሁለት ትምህርት ቤቶች ስራ አልጀመሩም። ዝክረ መለስ የሚባል አንድ ሁለተኛ ትምህርት ቤት እና ዕድገት ፋና የሚባል ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እነዚህ አልጀመሩም የተቀሩት ዘጠኙ ግን ትምህርት ጀምረው የመማር ማስተማሩ ስራ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል»

የደሴ አላማጣ መንገድ በፋኖ ትእዛዝ ተዘጋ፦ ኗሪዎች በኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል አሉ

አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የጦር ሰፈር ሆነዋል

በከተማዋ ትምህርት ቤቶች ወደ ወታደራዊ ካምፕነት መቀየራቸው በትምህርት ስራዉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ዶቼ ቬለ ከነዋሪዎች እና ባለስልጣኑ ጠይቆ ተረድቷል።

ከተማዋ የሲቪል አስተዳደር ትሻለች

  ከከተማዋ ነዋሪዎች የተነሳው የትምህርት ስራን ጨምሮ ሌሎች አስተዳደራዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶች በሲቪል አስተዳደር እየተመራ ባለመሆኑ እና አካባቢውን በኃላፊነት የወሰደው የፌዴራል መንግስት በአግባቡ ባለመምራቱ በነዋሪው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን  አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

«መማር ማስተማር ላይ ብቻ አይደለም ችግር ያለው ፤ አጠቃላይ አስተዳደራዊ ችግር ነው ያለበት። እንደዚያም ሆኖ ኃላፊነት የወሰደው የፌዴራል መንግስት በመሆኑ በሰላም ዉሎ በሰላም የመግባቱም ሁኔታ ትንሽ አስቸጋሪ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው። »

በከተማዋ እና ዙሪያ በተፈጠረው እሰጥ አገባ ችግር ውስጥ የገባው የማህበራዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች  መፍትሄ እንደሚሻ ነው ነዋሪዎች የሚጠይቁት ። ለችግሮች ምክንያት ከመፈለግ አፋጣን መፍትሄ መሻቱ ቅድሚያ ሊያገኝ እንደሚገባ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የአስተዳደር ኃላፊዎች አስገንዝበዋል።

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ