የአማራ ክልል ተፈናቃዮች አቤቱታ
ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2016ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ በተለያዩ የአገር ውስጥ መጠለያ ጣቢዎች ከቆዩ በኋላ በዚሁ ዓመት ሚያዝያ ወር ወዲህ ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ የተደረጉ ተፈናቃዮች የተሟላላቸው መሰረታዊ ጉዳይ አለመኖሩን ገልጸው መንግስትን ወቅሰዋል ። ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከቆዩበት የአማራ ክልል መጠለያ ጣቢያዎች ወደ ነባር ቀዬያቸው ኦሮሚያ ክልል ቢመለሱም የቀድሞ ሕይወታቸውን መምራት ተስኗቸዋል ። መንግስት በበኩሉ ተመልሰው ለተቋቋሙ ተፈናቃዮች አቅም በፈቀደ መጠን መሰረታዊ ነገሮችን የሟሟላት ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብሏል ።
የተመላሾቹ ቅሬታ
በ2014 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በደረሰው ጥቃት ምክንያት ተፈናቅለው ደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ልዩ ወረዳ ሰንቀሉ የተፈናቃዮች ካምፕ መቆየታቸውን ገልጸው ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ በተደረገው የመጀመሪየው ዙር ከሁለት መቶ አባወራዎች ጋር በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ወደ ቄዬያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ይላሉ አስተያየታቸውን የሰጡን ተመላሽ ተፈናቃዩ፤ "የሁለቱ ክልሎች መንግስታት መቋቋሚያ ይሰጣችኃል ወደ ቀዬያችሁ ተመለሱ ሰላሙም ተረጋግጧል ብለውን ልወስዱን ሲሉ ኮሚቴዎች ከኛ መሃል ተዋቅረው በዚያች አገር ተወልደን አድገናል ግን ዘር ተኮር ጥቃት የፈጸሙብን ሰዎች ተጠያቂ ሳይሆኑ፣ ሰላሙም ሳይረጋጋ እንዴት ይሆናል ብንል እነዚህን ጥያቄዎች እዛው ሆናችሁ ትጠይቃላችሁ በሚል መለሱን” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ወደዚያ የማይመለስ "ከአመጸኛ እና ከሌሎቹ ጋር ነው” በሚል ሌሎች የማንነት ጥያቄ እና የካሳ ጉዳዮችን ጨምሮ መጠየቅ የሚቻለው በዚያው ነው በሚል እርዳታ እንዳቋረጡባቸውም አስረድተዋል፡፡
የይዞታ መሬታቸው መያዝ
ይሁንና ይላሉ አስተያየት ሰጪው፤ ከተመለሱ በኋላ ግን ያልገመቱት ነገር እንደደጠበቃቸው አስረድተዋል፡፡ "ስንመለስ መሬታችን ተይዟል፡፡ ከሌሎች ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ጭምር የአከባቢው ተወላጆች መሬታችንን በመያዛቸው ባመለክትም የተሰጠን መፍትሄ የለም” ብለዋል፡፡ በይዞታቸው ላይ ሰርተው ሕይወታቸውን ቢመሩ እንደሚደሰቱ የገለጹት ተፈናቃይ ተመላሽ አስተያየት ሰጪው የማቋቋሚም ሆነ ሌሎች የመጠለያ ድጋፎች እየቀረቡ ባለመሆኑም ተቀምጠው በየቀሩ የሚመጣ ያሉትን አነስተኛ እርዳታ ብቻ ለመጠባበቅ መገደዳቸውን አስረድተዋልም፡፡
ሌላው ተፈናቅለው የተመለሱት የአከባቢው ነዋሪ እንደሚሉት፤ "በ2014 ዓ.ም. የደረሰብንን ማንነት ተኮር ግድያ ሸሽተን ወደ አማራ ክልል ሄደን ነበር፡፡ አሁን ለዚህ እንዴት ምፍትሄ ይምጣ በሚለው ጉዳይ አንድም ያወያየን አካል ሳይኖር ካልተመለሳችሁ እርዳታ አትሰጡም ብቻ ብለው ብያመጡን ስንመጣም ምፍትሄ የለም” ብለዋል፡፡
የመንግስት ምላሽ
ተመላሽ ተፈናቃዮቹ የሰነዘሩትን አስተያየት ይዘን ጥያቄውን ያቀረብንላቸው የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ማስተባበሪያ ቢሮ (ቡሳ ጎኖፋ) ኃላፊ አቶ ሞገስ ኢደኤ ግን ወደ ቶሌ ቀበሌ የተመለሱት አባወራዎች ከመጠለያ ካምፕ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ቀዬያቸው ባፋጣኝ መመለሳቸውን ገልጸው፤ ድጋፍም እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ "እርሻ እየታረሰላቸው ነው፡፡ ህዝብ ተባብሮ የተቃጠሉ ቤቶችን መልሶ መገንባት ጨምሮ ቤቶች እየሰራላቸው ነው፡፡ በማስረጃ ያለውም ነገር ነው፡፡ ከየትኛውም አከባቢ በተለዬ ሁኔታ ልጆቻቸው ትምህርት ባስቸኳይ የጀመረም ዚህ አከባቢ ተመላሾች ናቸው፡፡ ክፍተት የነበረው የማዳበሪያ እና ዘር አቅርቦት ላይም በብድር እንዲቀርብላቸው ተወስኗል፡፡ ከፀጥታ ጋርም በተያያዘ ከክልል እስከወረዳ የሚገናኝ ኮሚቴ ተፈናቃዮች የሚመለሱባቸው አከባቢ ፀጥታው የተረጋገጠ መሆኑን በማረጋገጥ ስለሆነ የሚመልሰው እስካሁን ያጋጠመመን ችግር የለም” ነው ያሉት፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው አማራ ክልል በተለያዩ የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ ከነበሩት እስካሁን 12ሺህ ገደማ የሚሆኑት ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸው ተነግሯል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑት በመንግስት አስተባባሪነት ስመለሱ ከ9 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በራሳቸው መመለሳቸው ነው የተገለጸው፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር