የአሜሪካ የአፍሪቃ ልዩ መልክተኛ ከኢትዮጵያዉያን ጋር ተወያዩ
ሰኞ፣ ነሐሴ 16 2014የአሜሪካ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ በአሜሪካ ከሚገኙ የሲቪል ማኀበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ። ልዩ ልዑኩ፣ በኢትዮጵያ በቅርቡ ስላደረጉት ጉብኝት ለድርጅቶቹ ተወካዮች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፣ በጀመሩት የሰላም ጥረት ላይ የተለያዩ ዐሳቦችንም ተቀብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት በሚቻልበት ጥረት ላይ፣ ከልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ማይክ ሐመር ጋር በተካሄደው ውይይት፣ከተገኙ ድርጅቶች መኻከል የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ግንኙነት ጉዳይ ኮሚቴ(ኤፓክ)ይገኝበታል።
ከኤፓክ ያነጋገርናቸው አምባሳደር ፍሰሐ አዱኛ፣ለ26 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።
"ብዙ ጊዜ በብሔር የተደራጁ ድርጅቶችን ነበር ሲጋብዙ የነበረው፤አሁን ደግሞ እኛንም ጋብዘውናል።እኛ የብሔር ድርጅት አይደለንም።አኛ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ለማስጠበቅ የተቋቋምን ከሁሉም ብሔረሰቦች የተውጣጣን ነን።ስለዚህ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ችግሮቿን በሰላማዊ መንገድ እንድትፈታ፣ ያሉት ችግሮች ሁሉ በውይይትና በሰላም እንዲፈቱ ነው የምንፈልገው።ከዚያ ሁሉ ውይይት ደግሞ፣የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጸና ነው እየነገርናቸው ያለነው።"
የዐማራ ማኀበር በአሜሪካ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር አቶ ሆነ ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ከአምባሳደር ሐመር ጋር በተካሄደው ውይይት፣ማኀበራቸው ሁለት ጉዳዮች ላይ አጽንኦት መስጠቱን ነግረውናል።
"በመጀመሪያ የውይይቱ ሂደት ዐማራዎችን ያገለለ መሆኑን እና ይሄ ደግሞ በቀጣናው የሰላም ዕንቅፋትነት አንጻር ተግዳሮት እንደሆነ እና አካሄዱም ስህተት እንደሆነ ገልጸናል።በሌላ በኩል ደግሞ በዐማራ ዘር ጭፍጨፋ በሃገሪቱ ከመቀጠሉ ጋር ተያይዞ፣ ይህን የዘር ጭፍጨፋ ለማስቆም አሜሪካ ግፊቷን አጠናክራ እንድትቀጥል የሚለውን አጽንኦት ሰጥተን ያነሳናቸው ዐሳቦች ናቸው።" የዘር ማጥፋት ቅድመ መከላከል በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ሰናይ ደረጀ ፣ድርጅታቸው ካነሳቸው ጉዳዮች መኻከል ዐበይት ያሉትን ይገልጻሉ።
"ወለጋ ላይ የሚደረገው ግድያ፣በጣም ዕልቂት እንደሆነ በአስፈሪ ሁኔታ ጭፍጨፋ እንዳለ በተለይ ደግሞ ሌሎች ኢትዮጵያንንም በተለይም ተጠቂው የዐማራ ሕዝብ የማይታይ እንደሆነ ስሜት እየተሰማው እንደሆነ፣በዐለም ሕዝብ ምንም ዐይነት ምላሽ አለመሰጠቱ፣ይህ ደግሞ ራሱን የቻለ ፍርሃትና ሌላ የበለጠ ሊመጣ ይችላል በሚል ያለመረጋጋት እንደፈጠረ፣ከተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ ከጭካኔው አልፎ ወለጋ ላይ ከሚደረገው አልፎ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዐማራ ማኀበረሰብ የበለጠ ያልተረጋጋ አድርጎታል የሚለው ፣ሁለተኛው የግድ አክሰስ እንደሚያስፈልግ እነዚህ አካባቢዎች ላይ ስለተከበቡ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው፣ጥበቃም እንዲደረግላቸው ጠይቀናል።"
የሲቪል ድርጅት ተወካዮቹ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ተወካዮች ጋር ያደረጉትን ወይይት ያደራጀው፣በዩናይትድስቴትስ የየጥናትና ምርምር ማዕከል የሆነው የአትላንቲክ ካውንስል ሲሆን ውይይቱን የተከታተሉት የማዕከሉ ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ገብርኤል ንጋቱን አስተያየት ጠይቀናል።
"እንግዲህ አምባሳደር ሐመር፣ከመጡ ያው አጭር ጊዜ ነው።አንዴ ነው ኦፊሻሊ ሄደው የመጡት ወደሪጅኑ፤ይሄኛው ውሏቸው ለማዳመጥ፣ለመስማት ለመማር ነው።አሁን እንግዲህ ተመልሰው መጥተው የሰሙትን አብላልተው እንዴት አድርጎ ወደፊት መሄድ እንደሚቻል፣የሚመካከሩበትና የሚያቅዱበት ጊዜ ነው።እንዳዩት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጥሩ አቀባበል፣ የዐሳብ መገናኘት አለ ይመስለኛል።ህወሓት ጋር በሌላ በኩል ያው የቅድመ ሁኔት የሚሉትን ይሄ አብሮ የሚሄድ ነው እንጂ፣ አንዱ ቅደም አንዱ ተከተል የሚባል አይደለም እናም ይህን ገልጸንላቸዋለን ብለዋል። ስለዚህ ያንን ማሳመንና ወደ ድርድሩ ገበታ እንዲመጡ ማድረግ ላይ ትንሽ ስራ ይጠይቃል።"
አምባሳደር ማይክ ሐመር፣በሰሜን የሃገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር፣በኢትዮጵያ በቅርቡ ባደረጉት ቆይታ ወደ ትግራይም ደርሰው መመለሳቸውም ይታወሳል።
ታሪኩ ኃይሉ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ