1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካው ልዩ ልዑክ ለኢትዮጵያ ሰላም ዘላቂ ሰላም ያመጡ ይሆን?

ዓርብ፣ የካቲት 29 2016

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የፕሪቶሪያ ግጭትን የማስወገድ ዉልን ገቢራዊነት በሚገመግመዉ ስብሰባ ላይ ተካፍለዋል ።የልዩ መልእክተኛው ጉብኝትና ዉይይት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ያስገኝ ይሆን?

https://p.dw.com/p/4dJsY
USA/Äthiopien Mike Hammer US-Sonderbeauftragter am Horn von Afrika
ምስል Seyoum Getu/DW

«ዘላቂ መፍትኄ የሚመጣው ኢትዮጵያውያን ስንግባባ ነው።»

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)የፕሪቶሪያ ላይ የተፈራረሙት ግጭትን የማስወገድ ዉልን ገቢራዊነት በሚገመግመዉ ስብሰባ ላይ መካፈላቸዉ ተዘግቧል። በአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበርነት አዲስ አበባ ዉስጥ በተደረገዉ ስብሰባ ላይ የተካፈሉት ሐመር በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሥለ ሚደረገዉ ግጭት ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩም የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታዉቋል። የልዩ መልእክተኛው ጉብኝትና ዉይይት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ያስገኝ ይሆን? 

የዩናይትድ ስቴትሱ ልዩ መልእክተኛ በኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትኄ ያመጡ ይሆን?

በኢትዮጵያ መንግሥት እና ተባባሪዎቹ እንዲሁም በሕወሓትና አጋሮቹ መካከል የነበረው እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት አብቅቷል ። በአንጻሩ በአማራ ክልል ከፕሪቶሪያው ስምምነት ብዙም ሳይቆይ ውጥረት፤ ግጭት እና ጦርነት ተከስቷል ። በኦሮሚያ ክልልም ለረዥም ዓመታት የዘለቀው ግጭት እና ጦርነት መፍትኄ አላገኘም ። የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር  የፕሪቶሪያው ተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊነት ላይ በአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበርነት በሚያደርገው ግምገማ ለመገኘትና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር  ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዐሳውቋል ። የዩናይትድ ስቴትሱ ዲፕሎማት ተልዕኮ በኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትኄ ያመጣ ይሆን?

«ዘላቂ መፍትኄ ያመጣል የሚል ብቸኛ ሐሳብ አይኖረኝም ።»

የሰብአዊ መብት፤ የሕግ እና የፌዴራሊዝም መምህር ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ ናቸው ። ዘላቂ መፍትኄ እንዲመጣ ልዩ መልእክተኛው የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉም መገመት ይቻላል ሲሉ ጠቁመዋል ። ዶ/ር ሲሳይ፦ ልዩ መልእክተኛው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሕወሓት የፕሪቶሪያው ስምምነት በተገቢው መልኩ አልተፈጸመም ሲል ቅሬታ ካሰማ ከሳምንታት በኋላ መሆኑንም አጽንዖት ሰጥተውበታል ።  በእርግጥ የማይክ ሐመር ኢትዮጵያ መምጣት ዘላቂ መፍትኄ ያመጣ ይሆን? በድጋሚ ጠየቅን ። 

«ዘላቂ ሰላም የሚመጣው ወንድሜ እኛ ኢትዮጵያውያን ስንግባባ ነው ። »

በግጭት አፈታት ዙሪያ ጥናቶችን ያቀረቡት ምሑር ዶ/ር ተክለኢየሱስ ተክሉ ባሕታ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ሣይንስ እና ቋንቋዎች ኮሌጅ መምህር እና ተመራማሪ ናቸው ።  ዶ/ር ተክለኢየሱስ በተለይ በአማራ እና በትግራይ ልሂቃን መካከል «መሠረት የሌለው» ያሉት አለመግባባት ሲፈታ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ፈር ቀዳጅ ይሆናል ሲሉ አስምረውበታል ።

የማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን ምን አንደምታ አለው?

የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበርን ለመገምገም  የማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያ መምጣትንም «እጅግ ጠቃሚ ነው» ብለዋል ። 

የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈራራሚ አካላት ተወካዮች
በፕሪቶሪያ በተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት መሠረት “የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና ብርቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ያሉት ማይክ ሐመር “ይኸን እንዲያደርጉ ግፊታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ቀደም ሲል ገልጸው ነበር ። ፎቶ፦ ከማኅደር ምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

በአፍሪቃ ሕብረት መሪነት የሚደረገዉ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚገመግመዉን የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት ባለስልጣናትን ስብሰባ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤  የአውሮጳ ኅብረት፤ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (IGAD) እና የዩናይትድ ስቴትስ ተወካዮች ይካፈሉበታል ተብሏል ።  

ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮጳ ኅብረትን ጨምሮ የተለያዩ መንግስታትና ማሕበራት የትግራዩ ጦርነት እንዲያበቃ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል ። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ግን ብዙም ጥረት ሲያደርጉ ዐይታይም በሚል ይወቀሳሉ ። ዶ/ር ሲሳይ ለዚህ ሁለት ምክንያቶችን ያነሳሉ ።  አንደኛው ሕወሓት በፌዴራሉ ሥልጣን ቁንጮ ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት ከምዕራባውያን ጋ ጠንካራ ትስስር መፍጠሩ ነው ይላሉ ።

«በዲፕሎማሲው፤ በኢኮኖሚው፤ በሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች በጣም ጠንካራ የሆነ ትስስር ከምዕራባውያን ጋ ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል ። ከዚያም  አልፎ የምስራቅ አፍሪቃ የምዕራባውያን ወኪል ሆኖ አሸባሪዎችን በመታገል ወይንም በማጥፋት ረገድ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል ። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ባለውለታቸው ነው ማለት ይቻላል ።»

ምዕራባውያን ለአማራ እና ለኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶች እና ጦርነቶች የሰጡት ትኩረት

የትግራይ ክልል እንደ ክልል በተደራጀ መልኩ ወደ ውጊያው መግባቱ ያስከተለው መጠነ ሰፊ እልቂት እና ውድመትም ምዕራባውያን በልዩ ሁኔታ ክትትል እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል ብለዋል ። ዶ/ር ተክለኢየሱስም  ከዶ/ር ሲሳይ ጋ በዚህ ይስማማሉ ። የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ጦርነቶች  የሚያደርሱት እልቂት በቀላሉ የማይታይ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል ። ምዕራባውያን የትግራዩ ጦርነት ወደሌሎች አካባቢዎች የመሻገር እና ሀገሪቱንም ቀጣናውንም የማናጋት አቅሙ ብርቱነት በወቅቱ እጅግ አሳስቧቸዋል ሲሉም አክለዋል።  በአንድ ጉዳይ ግን ከዶ/ር ሲሳይ ይለያሉ ።

የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ጦርነቶች የፈጠሩት ምስቅልቅሎች ትኩረት ያሻቸዋል የሚሉ ድምፆች በርካታ ናቸው ።
የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ጦርነቶች የፈጠሩት ሰብአዊ ምስቅልቅል በምዕራባውያን ተገቢውን ትኩረት አላገኙም የሚል ቅሬታ ይቀርባል ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Alemenw Mekonnen/DW

«ተላላኪነት የሚባለው ነገር በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው ። እንዲያውም ወያኔ መወቀስ ያለበት እጅግ በጣም ግትር መሆኑ ነው ። ያ የነበረበትን ማርክሲስት አስተሳሰብ ቀይሮ የእነሱን ፍላጎት የእኛንም ፍላጎት አጣጥሞ ማሻሻል ሲገባው፤ በዛው ደርቆ በመቅረቱ ከምዕራባውያን ጋ በመፋታቱ ነው ይህ ሁሉ ችግር የመጣው ።»

የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ጦርነቶች ተገቢው ትኩረት ያለማግኘታቸው ከምንም በላይ ይላሉ ዶ/ር ሲሳይ ። ከምንም በላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያለው «የተዛባ አመለካከት ነው ።»

ኢትዮጵያውያን ለሰላም መፍትኄ 

«ምዕራባውያን የተዛባ አመለካከት እንዳላቸው፤ ለምሳሌ በአማራ ክልል ላይ የሚካሄዱ ነገሮች በጣም አውዳሚ እና አስቸጋሪ መሆናቸው ዕየታወቀ፤ በሀገር ደረጃም የሚኖራቸው ተጽእኖም ከበድ ያለ እንደሚሆን ዕያወቁ ግን ድምፅ ሲሆኑ አንሰማም ። በፌዴራል መንግሥቱም ላይ ይሁን በሌሎች አካላት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር አይነት ውሳኔ ወይንም ርምጃ ሲወስዱ  አይሰማም ። ለምን ከተባለ? በዚያም አለ በዚህ አማራ እንዲዳከም ይፈለጋል ።»

በትግራዩ ጦርነት የተገደሉ የትግራይ ኃይሎች ተዋጊዎች ቤተሰቦች መርዶ በተነገረበት ወቅት ።
በትግራዩ ጦርነት የተገደሉ የትግራይ ኃይሎች ተዋጊዎች ቤተሰቦች መርዶ በተነገረበት ወቅት ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Million Haileselasie/DW

ዶ/ር ተክለኢየሱስ በትግራዩ ጦርነት ወቅት ምዕራባውያን ከፍተተኛ ትኩረት የሰጡበትን ምክንያት ያብራራሉ ።

«የመጠኑ ስፋት፤ እና የመስዋእትነቱ ብዛት ይመስለኛል ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት ። በወዳጅነት በምናምን የሚባል ነገር ከባድ ነው ። ወዳጅ ቢሆን መጀመሪያ እንዲወድቅ መሠረት አይጥሉም ።»

ሁለቱም ምሑራን በአንድ ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ይስማማሉ ። በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከማይክ ሐመር ኢትዮጵያ መጓዝ ባሻገር፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው ግጭት እና ጦርነት በኢትዮጵያውያን አፋጣኝ መፍትኄ እንደሚያሻው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ