የፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3 2016“ብዙ ሰዎች ወዳጅ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ነው ዛሬ ስርዓተ ቀብራቸው መቂ መሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የተከናወነው፡፡ ያው እንደ በቴ ከዚህ በላይ ብጠበቅም ብዙ ሰው ከሩቅም ከቅርብም መጥተው ስርዓተ ቀብራቸው ላይ ተገኝተው ቤተሰብም ቀብሩን ፈጽመው በሰላም ወደ ቤት ተመልሰዋል፡፡” ይህን አስተያየት የሰጡን ዛሬ በተፈጸመው የፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ስርዓተ ቀብር ላይ ላይ የተገኙት አንድ የቤተሰብ አባል ናቸው፡፡ ዛሬ በትውልድ አከባቢያቸው መቂ ስርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ሌሊት ተገድለው ትናንት ማለዳውን አስከሬናቸው ከመቂ ከተማ ወደ ባቱ መውጫ መንገድ ላይ ተጥሎ መገኘቱ ትናንት ከተዘገበ በኋላ ነው፡፡
የአስከሬን ምርመራ እና የፍትህ ጥያቄ
እኚህ አስተያየት ሰጪ የቤተሰብ አባላቸው ለዶይቼ ቬለ እንደ ተናገሩት የአቶ በቴ አስከሬን ትናንት ጠዋት በአከባቢው ማህበረሰብ እና ቤተሰቦቻቸው ከመንገድ ተነስቶ ወደ ቤት ከተወሰደ በኋላ፤ ዛሬ ጠዋት ወደ አከባቢው ሆስፒታል በመውሰድ የአስከሬን ምርመራ ተደርጎለት ነበር፡፡ “ቤተሰብ እንደ ትልቅ ነገር ያየው አንዴ የሞተውን ልጃቸውን ወስደው በስርዓቱ ቀብሩን መፈጸም ነው፡፡ ዛሬ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ አስከሬኑ እንዲመረመር የሆነው በህግ አዋቂዎች ምክር ነበር፡፡ ፖሊስ አስከሬኑን ወደ ምርመራ ባይወስድም ትናንት ጠዋት መረጃዎችን አሰባስቦ መሄዱንም” እኚህ የቤተሰብ አባል ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡በኦሮሚያ ያለውን ግጭት ተከትሎ ይፈጸማሉ የተባሉ ግድያዎች
እኚህ የቤተሰብ በአስተያየታቸው በአቶ ቤተ አስከሬን የተለያዩ የሰውነት አካል ላይ በርካታ ያሉት ቦታ ላይ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን የሚመላክት ብዙ ቁስሎች በአይናቸው መመልከታቸውንም አስረድተዋል፡፡ የፖለቲከኛውን መገደል ተከትሎ የቤተሰብ ዋነኛ ፍላጎት ፍትህን ማግኘትና እውነቱን ማወቅ ነው ብለዋልም፡፡ “ቤተሰብ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ በፍርድ ሂደት ፍትህ ብገኝ ቤተሰቡንም የአከባቢውንም ማህበረሰብ የሚያረካ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
በፖለቲከኛ በቴ ግድያ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አቋም
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ተከትሎ ተጠያቂነቱን ወደ መንግስት ለማድረግ የሚደረግ ያለው አሉባልታ ተቀባይነት እንደሌለው አስታወቀ፡፡ የክልሉ መንግስት ትናንት ማምሻውን ባወጣው ይፋዊ መግለጫ “በማይታወቅ አካል የተፈጸመ” ያለውን የአቶ በቴ ኡርጌሳን ግድያ እንደሚያወግዝም ገልጾ፤ “የኦነግ ባለስልጣኑ ከመንግስት ጋር ባላቸው የፖለቲካ አቋም ልዩነት ምክኒያት ብቻ ድርጊቱ በመንግስት እንደተፈጸመ ተደርጎ የሚሰራጭ አሉባልታ ተቀባይነት እንደሌለው መንግስት አጥብቆ ያሳስባል” ብሏልም፡፡ የኦነግ አባል ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ “በማይታወቅ አካል ተገድሎ አስከሬናቸው በመቂ ከተማ መገኘቱን” ያሳወቀው የክልሉ መንግስት መግለጫ ድርጊቱ በየትኛውም አካል ብፈጸም በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡ ኪሳራ የደረሰባቸው ያሏቸውንም የፖለቲካ አካላት “የፖለቲካ ስብራታቸውን በዚህ ለመጠገን ስሞክሩ ታይተዋል” ሲል የከሰሰው መግለጫው መንግስት ባለፉት ስድስት ዓመታት የፖለቲካ ምህዳርን ለማስፋት ሰፊ መስዋእትነት እንደከፈለም በማስረዳት፤ በፖለቲካ አቋም ልዩነት ምክኒያት በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ የሚገኝ አካል ላይ እርምጃ የሚወሰድበት ምክኒያት አይኖርም ሲል ገልጿልም፡፡የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ያለፍርድ እየማቀቁ ነው መባሉን
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአቶ በቴ ዑርጌሳ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ወንጀል አጣርቶ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል ያለው መግለጫው ምርመራው በጸጥታ አካላት ተጣርቶ ይፋ እስኪደረግ ተጠያቂነቱን ለየትኛውም አካል ከመስጠጠት መቆጠብ ያስፈልጋል ነው ያለው፡፡
ስለ ፖለቲከኛው ህልፈት የተሰጡ አስተያየቶች
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) የፖለቲከኛውን ግድያ በይፋዊ መግለጫ ከነቀፉት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር እና እውቁ ፖለቲከኛ ጃዋር መሃመድ ለሰላማዊ ትግል ዋጋን የከፈሉ በሚል የገለጹዋቸው የፖለቲከኛው ህልፈት እንደ አንድ ፖለቲከኛ ህልፈት ሳይሆን የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ላይ የተነጣጠረ ትቃት ተደርጎ የሚታይ ብለውታል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ የፖለቲከኛውን መገደል ተከትሎ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ እና ሙሉ የሆነ ምርመራ ተደርጎ ፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ከጠየቁት ናቸው፡፡
የበቴ የፖለቲካ አስተዋጽኦ
ከትናት በስቲያ ማክሰኞ ሚያዚያ 01 ቀን 2016 ዓ.ም. በትውልድ ቀዬያቸው ተገድለው ትናንት ረቡዕ ማለዳውን አስከሬናቸው ከመንገድ መገኘቱ የተገለጸው ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሱ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት አምስት ዓመታት ተጽእኖያቸው ጎልቶ ከተስተዋሉ ፖለቲከኞች ተጠቃሽ ተደርገው ይነሳሉ፡፡ ኦነግ በኦሮሚያ ክልል ለኅብረተሰቡ እንግልት መንግሥትን ተጠያቂ አደረገ
የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ለሚ ገመቹ ፖለቲከኛ በቴን ተናግሮ በማሳመን የፓርቲውን ዓላማ ለማስረዳት የሚታትር ይሏቸዋል፡፡ “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰላማዊ ትግልን በሚያደርግበት ወቅት ጎልቶ የወጣ እቁ” ያሉት ፖለቲከኛው የደርጅቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የተጎተ የትግል ጓዴ ነበሩ ብለዋል፡፡
ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ከዓመታት በፊት እስካሁንም በእስር ላይ ከሚገኙ የኦነግ ከፍተኛ ባለስልታናት ጋር በእስር ቆይተው በኋላም ባጋጠማቸው ከፍተኛ ህመም ምክኒያት ተለቀው ነበር፡፡ በቅርቡም ከፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ጋር በተገኙበት ታስረው በ100 ሺህ ብር ዋስ መለቀቃቸውም አይዘነጋም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ