የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ አዲስ የስደተኞች ሕግ አፀደቀ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3 2016የአውሮፓ ፓርላማ በአውሮፓ ህብረት የፍልሰት እና የጥገኝነት ህጎችን የሚያጠናክር ማሻሻያዎችን ትናንት በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
አዲሱ የአውሮፓ ህብረት የጥገኝነት እና የፍልሰት ስምምነት ወደ ህብረቱ የሚደረገውን ፍልሰት ተፅእኖ ለመቆጣጠር ያለመ ሲሆን፤ተቀባይነት የሌላቸውን የተገን ጥያቄዎች ውድቅ በማድረግ እና የጥገኝነት ጥያቄዎችን የማስተናገድ ሸክም አባል ሀገራቱ በእኩል እንዲጋሩ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።
ህጉ የፀደቀው በወግ አጥባቂ እና በለዘብተኛ ህግ አውጪዎች እንዲሁም በሰሜን እና በደቡብ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካከል ለዓመታት የዘለቀ ከፍተኛ ክርክር ከተረገ በኋላ ነው።
የአውሮፓ መሪዎች ምን አይነት ምላሽ እየሰጡ ነው?
ይህንን ተከትሎ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜሶላ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ x ባሰፈሩት ፅሁፍ .«ታሪክ ተሰራ። በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ስደትን እና ጥገኝነትን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ አቅርበናል» ብለዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን በበኩላቸው ስምምነቱ የጥገኝነት ማመልከቻዎችን የማስተናገድ ቅልጥፍናን ይጨምራል ብለዋል።
ከፍተኛ ስደተኞችን የምትቀበለው የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በጀርመንኛ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ስምምነቱን “ታሪካዊ፣” እርምጃ ሲሉ አወድሰውታል።
ሾልዝ አያይዘውም ስምምነቱ በአውሮፓ መንግስታት መካከል ያለውን ትብብር የሚወክል፣ መደበኛ ያልሆነ ስደትን የሚገድብ እና በተለይ ክፉኛ የተጎዱትን ሀገራት ሸክም የሚያቃልል ነው ሲሉ ፅፈዋል።
የአውሮፓ ህብረት የውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር ዮልቫ ጆንሰን በበኩላቸው ህጉን የሚያኮራ ነው ይሉታል።
«በጣም እኮራለሁ። ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ነው። እኔ ስልጣን በያዝኩበት ወቅት የታዬ ታሪካዊ ክስተት ነው።ከአራት አመት ተኩል በፊት ማለት ነው። በጣም ጥቂቶች ሁለቱንም ፓርላማ እንዲኖረን እናደርጋለን ብለው ያስባሉ። እና አባል ሀገራቱ በአዲሱ አጠቃላይ እና ጠንካራ፣ የስደት እና የጥገኝነት ፖሊሲ ላይ ይስማማሉ።»
ለውጦቹ ምንምን ነገሮችን አካቷል
በአዲሱ አሰራር በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ህብረት የሚገቡ ስደተኞች በሰባት ቀናት ውስጥ የማንነት ፣የጤና እና የፀጥታ ቁጥጥር እንዲሁም የፊት እና የጣት አሻራዎችን የባዮሜትሪክ ምርመራ ያካሂዳሉ።በዚህ ሁኔታ ሂደቱን ቢበዛ በ12 ሳምንታት ውስጥ ለመጨረስ ታቅዷል። ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው የጥገኝነት ጥያቄዎች ደግሞ በእነዚሁ ሳምንታት በግዳጅ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።የኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች መከራ
ይህ የአሰራር ሂደት የትኞቹ ስደተኞች የተፋጠነ ወይም መደበኛ የጥገኝነት ማመልከቻ ሂደት ማግኘት እንዳለባቸው፣የትኞቹስ ወደ ትውልድ አገራቸው ወይም ወደ ሚሸጋገሩበት ሀገር መመለስ እንዳለባቸው የሚለውን ለመወሰን ያለመ ነው ተብሏል።
ልጆች ልዩ እንክብካቤ ሊደረግላቸው የሚገባ ሲሆን፤ሀገሮች የመብቶች መከበርን ለማረጋገጥ ገለልተኛ የክትትል ዘዴዎችን የማድረግ ግዴታ አለባቸው።
የዜጎቻቸው የጥገኝነት ጠያቄ ውድቅ ከተደረገባቸው አገሮች ለምሳሌ እንደ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ እና ባንግላዲሽ ያሉ ፤ በፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ለአውሮፓ ህብረት የውጭ ድንበሮች ቅርብ በሆኑ የማቆያ ማዕከላት ቶሎ እንዲገቡ ይደረጋል።አደገኛው የባሕር ላይ ስደትና እልቂት
በየብስ ድንበሮች፣ ወደቦች እና አየር ማረፊያዎች የሚገኙት አወዛጋቢ ማዕከላት በማንኛውም ጊዜ እስከ 30,000 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት በዓመት እስከ 120,000 ስደተኞች እንዲያልፉ ይጠብቃል።
ተቺዎች ግን እንደዚህ አይነት የድንበር ማቆያዎች ስልታዊ እስራትን ያበረታታሉ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶችን ይጎዳሉ ብለው ይሰጋሉ።
በአውሮፓ ህብረት የጥገኝነት ስርዓት ላይ የተደረጉት ለውጦች ተግባራዊ ከመሆናቸው በፊት፤ በአባል ሃገሮች ሚኒስትሮች መረጋገጥ ያለባቸው ሲሆን፤ህጎቹ በጎርጎሪያኑ 2026 ዓ/ም ማለትም ከሁለት ዓመት በኋላ ተግባራዊ ይሆናሉ።
ኮሚሽነር ዮልቫ ጆንሰን ግን የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ፖሊሲውን ለመተግበር ከአሁኑ ጀምሮ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
«ስለዚህ ምንም እንኳ ሁሉም ነገር ለመተግበር የሁለት አመት ቀነ ገደብ ቢኖረውም ፤ ነገር ግን ተግባራዊነቱን አሁን ለመጀመር ዝግጁ ናቸው። በበኩሌ የኔ አጠቃላይ ትኩረት እዚያ ላይ ይሆናል። በእርግጥ ይህ የወረቀት ነብር ብቻ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሕጉ መሬት ላይ መተግበር አለበት።»
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ የፖላንድ እና የሀንጋሪ መሪዎች ግን ህጉ በሀገራቸው ተፈጻሚነት እንደሌለው እየገለጹ ነው።
የሃንጋሪ እና የፖላንድ ትችት
በማሻሻያውላይ ድምፅ ከተሰጠ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ መንግስታቸው ፖላንድን ስደተኞችን ማዛወር ከሚባለው ዘዴ «ይጠብቃል» ብለዋል። «ምንም እንኳን የስደት ስምምነቱ ባልተለወጠ መልኩ በግድ ተግባራዊ ቢደረግም፤ፖላንድን እድገና ማስፈር ከሚባለው ዘዴ ለመጠበቅ መንገድ እንፈልጋለን።»ሲሉ ቱስክ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የቀድሞ የአውሮፓ ምክር ቤት ሃላፊ የሆኑት ቱስክ እንደገለፁት «ጥምረቶችን ለመፍጠር የተወሰኑ እድሎች አሉኝ። ነገር ግን ስደተኞችን ወደ ሌላ ቦታ የመዛወር ዘዴ ወይም ላለመቀበል ክፍያ መክፈል በእርግጠኝነት በፖላንድ ላይ አይተገበርም» ብለዋል የቀድሞ የአውሮፓ ምክር ቤት ሀላፊ።
የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በቀድሞው ትዊተር በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ይህ ስምምነት ለአውሮፓ ህብረት «በሬሳ ሣጥን ላይ ምስማር እንደመምታት» ነው ብለዋል። ኦርባን «ከዚህ በኋላ ደህንነቱ የተጠበቀ ድንበር የለም።ሃንጋሪ ለጅምላ ፍልሰት ፈፅሞ አትሰጥም» ሲሉ ጽፈዋል።
በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ማሻሻያውን እንዲቃወሙ አሳስበዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ስምምነቱ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ “ከፍተኛ ስቃይ” የሚመራ ሲል አስጠንቅቋል። ኮሚሽነር ጆንሰን ግን በህጉ ተፈፃሚነት ላይ ጥጥርጥር የላቸውም።
«አብላጫ ድምጽ አለን። እናም ፓርላማውም ሆነ አባል ሀገራቱ ሁለቱም ሲስማሙበት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው ብዬ አስባለሁ።በእርግጥ ይህ ተግባራዊ የሚሆን ስምምነት ነው። የፓርላማ አባላቱ አስፈላጊውን ስምምነት ለማድረግ ያላቸውን ውዴታ በማየቴ በጣም ኩራት ይሰማኛል ።»
በስደት ላይ የጋራ ሃላፊነት
አዲሱ ደንብ ድጋፍ እንዲያገኝ ቁልፍ የፖለቲካ ጉዳይ የሆነው የአውሮፓ ህብረት «ዱብሊን III» ተብሎ የሚጠራው ደንብ ማሻሻያ ሲሆን፤ ይህም የትኛውም አባል ሀገር የትኛውንም የግለሰብ የጥገኝነት ጥያቄ የማስተናገድ ሃላፊነት እንዳለበት የሚወስን ነው።
ቀደም ሲል ጥገኝነት ጠያቂዎች መጀመሪያ የመጡባት አውሮፓዊ ሀገር ጉዳያቸውን የማስተናገድ ሃላፊነት ነበረበት።በዚህም እንደ ጣሊያን፣ ግሪክ እና ማልታ ባሉ የደቡብ አውሮፓ ሀገራት ላይ የበለጠ ጫና ያሳድራል።የኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች መከራ
በአዲሱ ደንብ «የመጀመሪያ ሀገር» መርህ ይቀራል። ነገር ግን «አስገዳጅ የአብሮነት ዘዴ» የሚል ተጨማሪ እርምጃዎችን በማስቀመጥ ሌሎች አባል ሀገራት የሸክሙን ትክክለኛ ድርሻ እንዲይዙ ይገደዳሉ። ሌሎች አባል ሀገራት ጉዳያቸው በሂደት ላይ ያሉ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ለማስተናገድ ፍቃደኛ ካልሆኑ ወይም ካልቻሉ በገንዘብ ወይም ተጨማሪ ባለሙያዎችን በማቅረብ መርዳት ይችላሉ።
በዓመት ቢያንስ 30,000 ጥገኝነት ጠያቂዎች በዚህ የማስፈር ሂደት ያልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከማስተናገድ ይልቅ መክፈል ለሚመርጡ ሀገራት ደግሞ የ600 ሚሊዮን ዩሮ (650 ሚሊዮን ዶላር) ዓመታዊ የማካካሻ የገንዘብ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
ይህ ዕቅድ የተነደፈው በጎርጎሪያኑ 2015 ዓ/ም 1.3 ሚሊዮን ሰዎች በተለይም ከሶሪያ እና ኢራቅ ጦርነት ሸሽተው ወደ አውሮፓ ከተጠለሉ በኋላ ነው ።
የአውሮፓ ህብረት የጥገኝነት ጥያቄዎች በ2023 የአውሮፓን ድንበር ያቋረጡ ስደተኞች380 ሺህ ስ ሲሆኑ ከ 2016 ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።
ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ