1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፋር ሶማሌ ግጭትና የደኅንነቶቹ ክስ

ዓርብ፣ ግንቦት 2 2011

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች ላይ ስለተከፈተው ክስ በተመለከተ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ከባድ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ ግለሰቦች ከሰሩት ወንጀል ማምለጥ እንደማይገባቸው ተናግረዋል። ክሱ መንግሥት የውስጥ አስተዳደሩን በቅጡ ማስተናበር ሲሳነው አቅጣጫ ማስቀየሪያ ነው ያሉም አሉ።

https://p.dw.com/p/3IH1R
Äthiopien Journalisten Martin Schibbye und Johan Persson
ምስል AP

ለአንዳንዶች ይህ ስም ከማይዳሰስ መንፈስ ጋር ይዛመዳል

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በቀድሞ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች ላይ የተከፈተው ክስ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችን ትኩረት እጅግ ስቧል። ክሱን አስመልክተው አስተያየት ሰጪዎች ከባድ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ ግለሰቦች ከሰሩት ወንጀል ማምለጥ እንደማይገባቸው ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው ክሱ መንግሥት የውስጥ አስተዳደሩን በቅጡ ማስተናበር ሲሳነው አቅጣጫ ማስቀየሪያ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ሰሞኑን በሦስት የድንበር ከተሞች መነሻነት በአፋር እና ሶማሌ ክልል የተፈጠረው ግጭት እና ውጥረት በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ትንታኔ ተሰጥቶበታል። ጠቅላይ ሚንሥር ዐቢይ አህመድ ከሕክምና ተመራቂ ተለማማጆች ጋር ያደረጉት ውይይት እና ንግግራቸው ከፍተኛ ትኩረት ስቦ ቆይቷል።  

«ጌታቸው አሰፋ»

ለአንዳንዶች ይህ ስም ከማይዳሰስ መንፈስ ጭምር ጋር የሚዛመድ ነው። ለዚያም ይመስላል አንዳንዶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ከስሙ ቀጥሎ ሙሉ ለሙሉ ጽልመት የተላበሰ በኮፍያ የተሸፈነ ባዶ ጥቁር ፎቶ ነገር የሚያሳዩት። ሰውዬው ስማቸው አለ፤ መልካቸው ግን በውል የሚታወቅ አይመስልም። ደሞዝ ገብረ ስላሴ ፌስቡክ ገጹ ላይ፦ «እኔ የሚገርመኝ» ሲል በመጻፍ ይንደረደራል። «ጌታቸው ኣሰፋ እንዲታሰር ሳይሆን መልኩን ለማየት ብቻ የሚፈልግ ሰው እጅግ በጣም ብዙ ነው» ሲል አግራሞቱን ገልጧል።

አንዳንድ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ሰውዬው ላይ እስከዛሬ ክስ ሳይመሰረት አሁን መመስረቱን ከአንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ለማገናኘት ሞክረዋል። ክንፈ ገብርኤል በትዊተር ጽሑፉ፦ «እስካሁን ጭጭ ተብሎ ከኢሃዴግ ስብሰባ በኋላ ሳምንት ባልሞላው ግዜ ክሱ ሲመሰረት ስብሰባው ላይ ህወሐትና ኦዴፓ በመከላቸው ያለው ክፍተት መስፋቱን አመላካች ነው» ብሏል። «አሁን አሁን መሪዎቻችን ግለሰቦችም ይሁኑ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንዴት እንደሚሰሩ በመሃከላቸው ምን እንደተፈጠረ መገመት አይደለም ማሰብ አዳጋች ነው» ያለው ክንፈ ሁኔታውን «በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ...ትርምሥ» ሲል ገልጦታል። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አራት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገለግሎት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተይዘው እንዲቀርቡ ትናንት ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱን የሚመለከተውን ዜና ብዙዎች ተማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ተቀባብለውታል።  እሸቱ ሆማ ቄኖ፦ «አሁን የፌደራል ፓሊስ አቅምና የተወራለት የሕግ የበላይነት ጉዳይ በተግባር ሲፈተን ልናይ ነው፣ ጌታቸው አሰፋ በተገኘበት ታስሮ ይቅረብ ብሏል ፍርድ ቤት» ሲል ትዊተር ላይ በመጻፍ የፈገግታ ምልክት አስፍሯል።

«እኔ የምለው ግን መንግሥት ሰለጌታቻው አስፋ ጉዳይ ብቻ ነው የሚያወራው? ስለተዘረፈ ባንክ ምንም አይነገርም? ማን እንደዘረፈ ምንም አይነት መግለጫ አይነገርም? እንዴት ነው ነገሩ? ጎበዝ» ሲል ጥያቄዎቹን ያከታተለው ሐንድሶ ማንታሶ ነው ፌስቡክ ላይ። ኢዚ ኢዚ በሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ በበኩሉ፦ «18 ቱባንክ ዘራፊዎችና የብር መጠኑም ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ ቢሆን ሲል ጠይቋል።

«እነሱ ከስልጣን ስለወረዱ በወንጀል ሊጠየቁ፤ ስልጣን ላይ ያሉትና የተደመሩት ግና በወንጀል ኣያስጠይቅም ማለት ነው ኣይደልይኸኛው ጥያቄ ደግሞ የዘፈሩ በሪሁ አስተያየት ነው። የማዕረግ ናዝራዊ አስተያየት እንዲህ ይነበባል። «ወንጀል ሰርቶ በውጭ ሀገር የተደበቀ ወንጀለኛ በኢንተር ፖል አማካኝነት ይያዛል፤ አቶ ጌታቸው አሰፋ ግን ክልል ተቀምጦ ያልተያዘበት ምክንያት የፌደራሉ መንግስት አቅም እንደሌለው ያመለክታል በጣም ያሳዝናል»ይላል።

«ውኃ ስንጠይቅ ጌታቸው አሰፋ፤ ዳቦ ብንጠይቅ ጌታቸው አሰፋ፤ ደሞዝ ስንጠይቅ ጌታቸው አሰፋ፤ ጌታቸው እስኪገኝ እኛ የት እንጥፋ የሰሜ በል የፌስቡክ አስተያየት ነው።

ትእግስት በትዊር ገጿ ላይ ያሰፈረችው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። «ትኩሳቱ በተሰማቸው ቊጥር የጌታቸው አሰፋን ካርድ ይጫወታሉ።»

ሕይወት አሳምነውም በእነ ጌታቸው አሰፋ ላይ የተከፈተው ክስ ሌሎች ጉዳዮችን ማስቀየሻ ስልት ነው ከሚሉት ውስጥ ናት። «መንግስት ምን ዓይነት ቅዠት ነው የያዘው» ያለችው ሕይወት፦ «ሁሌ ጌታቸው ኣሰፋ የህዝብ ጥያቄ ላለ መመለስ ኣዲስ ነገር ሲነሳ ጌች ነው የሚሉት ለምድነው ስትል ፌስቡክ ላይ ጥያቄ አስፍራለች።  በዚሁ ወደ ቀጣዩ ርእሰ ጉዳይ እንሸጋገር።

ግጭት በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች

ገርብ ኢሳ፣ እንዱፎ እና አዳይቱ የተባሉት ቀበሌዎች አፋር እና ሶማሌ ክልሎችን ለግጭት ዳርገው በአካባቢው የሰው ሕይወትም ጠፍቷል። ቀበሌዎቹ በታኅሳስ 2007 ዓ.ም በተደረገው ሥምምነት ለአፋር ክልል እንዲሰጡ የተላለፈውን ውሳኔ የሶማሌ ክልል ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም ሲል በካቢኔው በኩል መሻሩ እንደተሰማ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ግጭቱን የፌዴራል መንግሥቱ እና አንዳንድ ክልሎች የእጅ አዙር የኃይል ጉትቻ አድርገው የወሰዱ አስተያየት ሰጪዎች ነበሩ።

Äthiopien Landschaft in Provinz Afar Kamele durch die Wüste
ምስል picture-alliance/dpa

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 28፤ ቀን፣ 2011 ዓም ስብሰባ ማካሄዱን እና አፍታም ሳይቆይ የግጭቱ መጀመር ያስደነቀው መርዕድ፦«ቆይ በቀደም አይደል እንዴ የተሰበሰቡት ሲል ጠይቋል። በስብሰባው ላይ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሀመድም ነበሩ። ከዚህ ጋር በተያያዘም ኃይልዬ በቀለ፦ «ሙስጠፋ ከአብዲ ኢሌ የተቀበለውን ልዩ ኃይል ልኮ ሦስቱን ቀበሌ ከአፋር ተቀብሎታል። ስለ አፋር ኢህአዴግ ከተጨነቀ ይገርመኛል» ሲል አስተያየቱን በትዊተር ሰጥቷል።

ሆመድ ኢስካህ የአፋር እና የሶማሌ ክልል ግጭትን በተመለከተ፦ «የአፋር ክልላዊ መስተዳደር በሶማሌ ክልል ሲወረር የፌዴራል መንግሥቱ ዝምታን አፋሮች ያወግዛሉ» ሲል ትዊተር ላይ አስፍሯል።  

ኖርዌይ መዲና ኦስሎ ውስጥ የሚገኘው የቢዮርክኒስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሠላም እና ግጭት ጥናት ፕሮፌሰሩ ኬቲል ትሮንቮል በአፋር እና በሶማሌ ክልል ያለውን ግጭት፦ «አዲስ አይነት የድንበር ግጭት ማስጠንቀቂያ ምልክት» ብለውታል።

ሙስካብ ካዴ እዛው ትዊተር ላይ ለፕሮፌሰሩ በሰጠው መልስ፦ «እነዚያ ሦስት መንደሮች ወደ አፋር ክልል የተላለፉት ከሶማሌ ሕዝብ ዕውቅና ውጪ» መኾኑን ጠቅሷል። ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ ጎዳና እያመራች ነው ያለው ሙስካብ፦ «መንደሮቹ ወደ ሶማሌ ወንድሞቻቸው መመለስ አለባቸው። ከዚያ አንጻር ይህ ወደ ድንበር ግጭት አያመራም» ሲል ጽፏል።

ጫላ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መልእክት፦ «ግጭት በወንድማማቾች መካከል ጥላቻ እና መቃቃርን ማስፈን አይገባውም፤ ይልቊንስ በሳል መፍትኄ ለመሻት አነቃቂ መኾን አለበት» ብሏል።  «ብርቱ ተግዳሮት የተጋረጠባቸው» ያላቸው አፋር እና ሶማሌ ክልል ነዋሪዎች «ወደግጭት ከሚገቡ ይልቅ ለዘላቂ ሕይወት መፍትኄ መሻት አለባቸው» ሲል መክሯል።

በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ግጭት አስተያየቶች ሲንሸራሸሩ ትናንት አመሻሹ ላይ የወጣ ዜና በፌስቡክ እና ትዊተር ብዙዎች ተቀባብለውታል። ዜናው «የአፋርና ትግራይ ክልል ህዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት በአፋር ክልል በዓብዓላ ከተማ ተካሂዷል» ይላል።

የሕክምና ተመራቂ ተለማማጆች ጥያቄ 

የሕክምና ተመራቂ ተለማማጆች ጥያቄ እና በስብሰባ አዳራሽ የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ መልስ ሌላው የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የመነጋገሪያ ርእስ ነበር። በኢትዮጵያ አንዳንድ የጤና ሳይንስ ኮሌጆች የሚገኙ ተለማማጅ ሀኪሞች ሰሞኑን የተቃዉሞ ሰልፍ አካሂደዉ ነበር። በተቃዉሞ ወቅትም «የሚሰጠዉ ክፍያ ከስራችን ጋር የማይመጣጠን ነዉ፤ ለሞያዉና ለባለሞያዉ የሚሰጠዉ ክብር አነስተኛ ነዉ» ሲሉ ተደምጠዉ ነበር። ጠቅላይ ሚንሥትሩ የህክምና ባለሞያዎችን ባነጋገሩበት ወቅት በህክምናው ዘርፍ ሙስና እና አላግባብ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ ተናግረዋል። ችግሮች ያሏቸውንም የተለያዩ ጉዳዮች አንስተዋል። በውይይቱ መሀልም ታዳሚውን በጋራ ያሳቀ ንግግር አሰምተዋል።

Äthiopien | Ärzte protestieren in Bahir Dar
ምስል DW/A. Mekonnen

«መኪና መንዳት ተራ ነገር ነው።ሁለት ሦስት ሰው መንዳት እንዲችላል አድርጉና በጋራ ተጠቀሙበት። አንድ ቀን አንደኛው ጋር፤ አንድ ቀን አንደኛው ጋር ካደረ እኮ ችግሩ ይፈታል። ዋናው ግቢ በር ላይ ማቆም አይደል መኪናው

ሳቊ ግን ከስብሰባው አዳራሽ ውጪ የቀጠለ አይመስልም። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የተዘዋወሩ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች እንደሚያመለክቱት ከኾነ ሥራ ያቆሙ ተለማማጅ ሐኪሞች እስከ ትናንት ድረስ ወደ ሥራ ገበታቸው ካልተመለሱ ከኮሌጅ ይባረራሉ። 

ፍሬው አሥራት በትዊተር ገጹ፦ «ስንቶቻችው ናችሁ ኢንተር ሃኪሞች የሥራ ማቆም አድማ ላይ እንዳሉ የምታውቁት? ስንቶቻችውስ ናችሁ ዛሬ ግንቦት 1 የመጨረሻው ወደሥራ መመለሻ ቀን መሆኑን የሰማችሁት? ስንቶቻችን ነን ኢንተር ሃኪሞች ከግቢ ሊባረሩ እንደሆነ የምታውቁት ሲል ይነበባል የግንቦት 1 ቀን፤ 2011 ዓ.ም ጽሑፉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ
 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti