1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ዐበይት አጀንዳዎች

ቅዳሜ፣ የካቲት 11 2015

አፍሪቃን ስር የሰደደ የምግብ እጥረት ቀውስ እና የፀጥታ ሥጋት እየናጣት ነው። ኅብረቱ አዲስ አበባ ውስጥ በሚያደርገው ጉባኤ ዋነኛ መነጋገሪያ መሆናቸው ቀደም ሲል ተዘግቧል። በተለይ ከምዕራብ አፍሪቃ የሣኅል ቀጣና አንስቶ እስከ የአፍሪቃው ቀንድ ድረስ የጦር መሣሪያ ግጭቶች፤ ድርቅ እና ጎርፍ በርካቶችን ለኅልፈት እና ለመፈናቀል እየዳረጉ ነው።

https://p.dw.com/p/4NfWv
Äthiopien Addis Abeba | 36. Sitzung des Afrikanischen Union Gipfel
ምስል Solomon Muche/DW

ስር የሰደደ የምግብ እጥረትና የፀጥታ ሥጋት

አፍሪቃን ስር የሰደደ የምግብ እጥረት ቀውስ እና የፀጥታ ሥጋት እየናጣት ነው። እነዚህ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ኅብረቱ አዲስ አበባ ውስጥ በሚያደርገው ጉባኤ ዋነኛ መነጋገሪያ መሆናቸው ቀደም ሲል ተዘግቧል። በተለይ ከምዕራብ አፍሪቃ የሣኅል ቀጣና አንስቶ እስከ የአፍሪቃው ቀንድ ድረስ የጦር መሣሪያ ግጭቶች፤ ድርቅ እና ጎርፍ በርካቶችን ለኅልፈት እና ለመፈናቀል እየዳረጉ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአንድ ወር በፊት ባወጣው ዘገባው 44 ሚሊዮን ሰዎች አፍሪቃ ውስጥ በተጠቀሱት ችግሮች የተነሳ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በዓለም አቀፉ ግጭት ጥናት ተቋም (Crisis Group) የአፍሪቃ ኅብረት ባለሞያ ሊይስል ሎው ቭራውዳን ኅብረቱ በተለይ በግጭቶች የተነሳ የሚደርሱ በደሎች ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። «የአፍሪቃ ኅብረት በ2002 የተፈጠረው በግጭቶች እና ስቃዮች ጣልቃ ያለመግባት ግን ደግሞ ግድ የለሽ ያለመሆን በሚለው መርኅ ነው።»

Äthiopien AU in Addis Abeba
የአፍሪቃ ኅብረት ዓርማ በወርቅ ቅብምስል DW/G. Giorgis

ከግጭት ጦርነቶች ባሻገር ድርቅ እና ረሐብም የአፍሪቃ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተገልጧል። ኢትዮጵያ ውስጥ ቦረናን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ድርቅ እና ግጭት በርካቶችን ለምግብ እጥረት እንደዳረገ በተደጋጋሚ ተዘግቧል። ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች የዝናም እጥረት የገጠማት ጎረቤት ሶማሊያ በድርቅ አፋፍ ላይ ትገኛለች። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿም ብርቱ ጥፋት ሊያስከትል በሚችል ከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው። እንዲህ ያሉ ችግሮች የተጋረጡበት የአፍሪቃ ኅብረት በጋራ ችግሮቹን በፍጥነት ከመፍታት ይልቅ ሃገራት በተናጠል የየራሳቸውን ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። አንዳች የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ሊይስል ሎው ቭራውዳን የድርጅታቸውን ጥናት በማጣቀስ መክረዋል።

Symbolbild | ECOWAS | Westafrikanischer Regionalblock verabschiedet neuen Plan zur Einführung einer einheitlichen Währung im Jahr 2027
የኢኮዋስ አባል ሃገራት ሠንደቅ ዓላማምስል Pius Utomi Ekpei/AFP/Getty Images

«ምናልባት ቀጣናዎች ከአፍሪቃ ኅብረት በተሻለ ቦታ ላይ ይገኙ ይሆን? ግን ደግሞ በአፍሪቃ ኅብረት እና በድርጅቶች ብሎም በራሳቸው በድርጅቶቹ ማለትም በሳዴክ፤ ኢጋድ እና ኤኮዋስ መካከል አንዳች ስምረት እና ተነጻጻሪ ጥቅም ሊኖር ይገባል። እኛም በክራይሲስ ግሩፕ ዘገባችን ላይም ያመለከትነው ይህንኑ ነው። ሊያስቡበት እና ታላቅ ትብብር ሊያደርጉበት የሚገባ ጉዳይ ነው።»

የአፍሪቃ መሪዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው ግፊት ከማድረጋቸውም ባሻገር አፍሪቃን ሊያጠናክር ይችላል የተባለለትን የጋራ ነጻ የንግድ አካባቢ ምሥረታን ሊያቀላጥፉ እንደሚገባ ባለሞያዎች መክረዋል።

«የአፍሪቃ ኅብረት የ2023 ዋነኛ አጀንዳ የአኅጉሪቱ ነጻ ግብይት ትግበራን ማቀላጠፍ ነው። ምክንያቱም አፍሪቃ በዚያ መንገድ በትክክል ከተጓዘች ያ በእርግጥም ታላቅ ለውጥ የሚያመጣ ነው። ግን ነጻ ግብይቱን ማስጀመሩ ላይ ገና ሩቅ መንገድ ላይ ነው። እንደተከታተልነው በድንበሮች መካከል ውጥረቱ አለ፤ የኮቪድ-19 ወረርሺኝም በእነዚህ ውጥረቶች ላይ የራሱን ጥላ አጥልቷል። ስለዚህ፦ የአፍሪቃ የበይነ ንግድ ማስጀመሩ ላይ እየተጓዝን ነው፤ ግን ደግሞ የሰዎች እንቅስቃሴ ስምምነት በሚገባ ስኬታማ ሆኖ ገና ተግባራዊ አልሆነም።»

Fahnen der IGAD-Mitgliedsländer
የኢጋድ አባል ሃገራት ሠንደቅ ዓላማምስል Yohannes G/Eziabhare

ያ በመሆኑ ደግሞ ጥሬ እቃዎችንም ሆነ ሸቀጦችን ከአንዱ ቀጣና ወደ ሌላኛው ቀጣና አለያም ሃገራት ለመላክ ቢቻልም ለሰዎች እንቅስቃሴ ግን ብርቱ ተግዳሮት ደቅኗል። በአኅጉሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥም ደግሞ በግለሰቦች የሚያዝ የንግድ ዘርፍ ጉልኅ ሥፍራ አለው። ይህን ማጣጣም ለአኅጉሪቱ ፈተና እንደሚሆን ባለሞያዋ አክለው ተናግረዋል። ለዚያም ይመስላል አንዳንድ ሃገራት ከቀጣናቸው ውጪም ቢሆን ከወዲሁ በተናጠል ስምምነት ሲያደርጉ የሚስተዋለው። ባለፈው ሳምንት ኤርትራ እና ኬንያ ዜጎቻቸው ያለምንም ቪዛ ከአንደናቸው ሀገር ወደ ሌላኛው መጓዝ እንደሚችሉ ይፋ ያደረጉት እና የቪዛ ጥያቄን ያነሱት።

እነዚህን እና ሌሎች ጉዳዮችን በመመልከት ዛሬ የጀመረው የኅብረቱ ጉባኤ በነገው እለት ይጠናቀቃል። በጉባኤው ከአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ባሻገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እና የአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሻርል ሚሼል ተሳታፊ እንደሆኑ ቀደም ሲል ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti