የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪዎች
ሰኞ፣ ነሐሴ 19 2006የአካባቢዉን ይዞታ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች በበኩላቸዉ እንደተባለዉ በእቅዱ መሠረት ከመሄድ አስቀድሞ ሁለቴ ባለሰብ ይበጃል። ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት በሶማሊያ ጉዳይ የሚመለከታቸዉ አካላት ባካሄዱት ግምገማ M,ሰረት የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር 2016 መጨረሻ ይወጣሉ። የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ልዩ ልዑክ ሊዲያ ዋንዮቶን እና በዑጋንዳ የሶማሊያን አምባሳደር የጠቀሰዉ ዘገባ እንደሚለዉ የሶማሊያ ፌደራላዊ መንግሥት በጦርነት የተዳቀቀችዉን ሀገር ራሱን ችሎ መቆጣጠር የሚችልበት አቅም ይኖረዋል ባይ ናቸዉ። የተመድ ባለፈዉ ዓመት ለAMSISOM የሰጠዉ ሰላም የማስከበር ኃላፊነት በዉሉ መሠረት ከሁለት ዓመታት እንደሚያበቃ ነዉ። ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ የዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ያኪ ሲሊየ የታሰበዉ የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ኃላፊነት ማብቂያ ጊዜ ዳግም መጤን ይገባዋል ነዉ የሚሉት፤
«እንደሚመስለኝ ይህ ሃሳብ ከወራት አስቀድሞ ዳግም ክለሳ ይደረግበታል፤ በተለይ የተመድ ተልዕኮ በገንዘብ ጭምር የሚደግፈዉ የአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ሁኔታዎችከተመቻችተዉ ይህን የሚፈቅዱ ከሆነ ብቻ ነዉ መዉጣት የሚችለዉ። በሶማሊያ ያለዉ ሁኔታ በበቂ ሁኔታ ተረጋግቷል ማለት ከምንችልበት ሁኔታ ላይ ነን ብዬ አላስብም። ሃሳቡ ሊመጣ ይችላል ነገር ግን ገና ሁለት ዓመታት አሉ። እናም በዚህ ጊዜ የሚፈጠሩት በርካታ ለዉጦች የተባለዉን የጊዜ ገደብ ዳግም ለማሰቢያ ጊዜ ይኖራል። ከወዲሁ ሲታይ ግን በጣም አጭር ይመስላል፤ በፍፁም ተጨባጭ አይመስልም።»
ሶማሊያ ዉስጥ በየጊዜዉ አሁንም ያላሰለሰ የአሸባብ ጥቃት መድረሱ ገና አላባራም። ዘገባዉ የጠቀሳቸዉ በዩጋንዳ የሶማሊያ አምባሳደር ሼኽ ሰይድ አህመድ ዳሂር ግን ሶማሊያ ከእንግዲህ ምንም ዓይነት ግጭት አይኖርባትም፤ በወዳጅ ሃገራት ድጋፍም ሁሉንም ለመቆጣጠር ዝግጁ ነን ነዉ የሚሉት። በዚህ በሁለት ዓመታት ዉስጥ እንደተባለዉ የሶማሊያ የራስ ምታት የሆነዉ አሸባብ ጥቃት አከትማል፤ ቡድኑስ የት ይሄዳል ማለት ይቻላል? ያኪ ሲሊየ እንዲህ ያላሉ፤
«AMISOM እዚያ ያለዉ አሸባብን ለመዋጋት ብቻ አይደለም። ተልዕኮዉ እዚያ የሚገኘዉ ሶማሊያ ዉስጥ የመንግሥት ተቋማትን ሁሉ ማቋቋምን ለማመቻቸት ነዉ። በረዥም ጊዜ ጥናት ተቋሙ በአፍሪቃ ያልፀኑ መንግሥታትን አጥንቷል፤ ከእነዚህ መካከልም ሶማሊያ አንዷ ናት፤ እናም ወደድምዳሜዉ ስንመጣ ተገቢ መንግሥታዊ ተቋማትን ሶማሊያ ዉስጥ ለመመሥረት በርካታ አስርት ዓመታትን ይወስዳል። እናም ምንም እንኳን የAMISOM ወታደራዊ ኃላፊነት ቢቀየር እንኳ ሶማሊያ የመንግሥታቱ ድርጅትን ሌላ ተልዕኮ ማግኘቷ አይቀርም። አንቺ ወዳነሳሽዉ ስመጣ የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ አፍሪቃ ዉስጥ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መምጣቱ እየታየ ነዉ። እናም AMISOMን ከወታደራዊ ድጋፍ ሰጪነቱ ወደሲቪል ጉዳዮች የማዞሩ ነገር በቦታዉ ላይ በሚኖረዉ ነባራዊ ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል። ነገር ግን በወቅቱ ያሉ ማሳያዎች አለመረጋጋትና የሽብር ተግባራት መቀነሳቸዉን አይደለም። በተቃራኒዉ አስደንጋጭ ሁኔታ ላይ ነዉ የሚገኘዉ። AMISOM የሶማሊያ መንግሥ ሶማሊያን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ይችል ዘንድ ሁኔታዎችን በቁጥጥሩ ሥር ገና አላደረገም። እናም የተልዕኮዉን ኃላፊነት ገና ጊዜዉ ሳይደር የመቀነሱን ነገር በጥምቃቄ ነዉ በግሌ የምመለከተዉ።»
የሶማሊያ መንግሥት ኃይሎች ሀገሪቱን ከፅንፈኛ ታጣቂዎቹ መከላከል ይችሉ ዘንድ ስልጠናዎችን በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት እየወዱ ነዉ። አምባሳደሩ በተጓዳኞች አማካኝነት ለሶማሊያ ኃይሎች የሚደረገዉን የአቅም ግንባታ ስልጠና ዜጎቻቸዉ ለሀገራቸዉ የተሻለ የፀጥታ ይዞታ ለማምጣት እንዲያዉሉት መማፀናቸዉ ተጠቅሷል። የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደሮች እንደተባለዉ በታቀደዉ ጊዜ ቢወጡ፤ ሀገሪቱን ያለሰላም አስከባሪ ኃይል የሚኖራት ሁኔታ በሀገሪቱ ኃይሎች ፀጥታን ለማስከበር በተፈጠረዉ አቅም ላይ የሚመሠረት ነዉ ባይናቸዉ ሲልየ፤
« ይህ ሁሉ በመቅዲሾ መንግሥት በገነባዉ አቅም ላይ የሚመሠረት ነዉ የሚሆነዉ። ይህ አቅምም ከምንም በላይ እጅግ ወዛጋቢና ሶማሊያ ዉስጥ ዋነኛ ችግር በሆነዉ የቀረጥ ገቢ እና በዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ ላይ የተመሠረተ ነዉ የሚሆነዉ። ሶማሊያ የሚያስፈልጋት ተገቢዉ የፀጥታ መረጋጋትና ዘላቂነት ያለዉ ፀጥታና ደህንነትን ለሕዝቡ ማቅረብ የሚችል አቅም ያለዉ መንግሥት ነዉ። ይህ ደግሞ ጊዜ ይፈጃል። በዓመት ወይ በሁለት ዓመት የሚከናወን ነገር አይደለም ይሄ። እናም ይህ ጥያቄ ቢያንስ በየስድስት ወሩ ሊከለስ ይገባል። እናም በድጋሚ ማስገንዘብ የምፈልገዉ እንዲህ ያለዉ ዉሳኔ የመቅዲሾን የወቅቱን ሁኔታ ሳያገናዝብ ተግባራዊ መደረግ እንደማይኖርበት ነዉ።»
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ