"ፀፀት" እና "ዝምታዬ" በእንግሊዝ አገር
ሐሙስ፣ ኅዳር 6 2016«ትልቅ የሆነ የፌልም ተቋም፤ የፌልም ትምህርት ቤት የለንም። የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ የኤሊ ጉዞ ነዉ የምትጓዘዉ፤ እየተንፏቀቀች ነዉ የምትገኘዉ። በመጀመርያ ደረጃ በአፍሪቃ ታሪክ ፊልም የሰራች አገር ኢትዮጵያ ናት። ዛሬ ግን ኢትዮጵያ በፊልም ኢንዱስትሪዉ መጨረሻ ቦታ ላይ ነዉ የምትገኘዉ።» ያሉት፤ ለፊልም ኢንዱስትሪዉ መነቃቃት የራሱ ድርሻ አለው የተባለለት እና የዛሬ ሰላሣ ዓመት የተሰራዉ ፀፀት የተሰኘዉ ፊልም ደራሲ እና በአዉሮጳ ሃገራት የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶችን በመሰብሰባቸዉ የሚታወቁት አቶ አለባቸው ደሳለኝ ናቸዉ።
ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያን ፊልሞች በተለያዩ የዓለም ሃገራት የሚያስተዋዉቀዉ እና ለእይታ የሚያቀርበዉ «ሐበሻ ቪው» የተሰኘዉ ድርጅት ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በለንደን ፊልም ቤቶች ሁለት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዉያን የተሰሩ ፊልሞችን ለእይታ አቅርቧል። ባለፉት ሳምንታት በለንደኑ ፌስቲቫል ለእይታ የበቃዉ፤ "ፀፀት " የተሰኘው ፊልምና በአስጨናቂ በቀለ የተፃፈው "ዝምታዬ" የተሰኘዉ ፊልምን ወደ ብሪታንያ የፊልም መድረክ ያመጣዉ የሐበሻ ቪው አንዷ መስራችና ስራ አስኪያጅ፣ ወ/ሮ ትእግስት ከበደ ናቸው። ሐበሻ ቪው ከተመሰረተ ወደ ስምንት ዓመት ቢሆነዉም፤ በኮሮና ምክንያት ፊልምን የማስተዋወቁ ስራችን ተቋርጦ ነበር፤ ዘንድሮ ግን ለአራተኛ ጊዜ ሁለት የኢትዮጵያ ፊልሞችን አምጥተን በለንደን የፊልም ፊስቲቫል ለእይታ አቅርበናል ሲሉ ወ/ሮ ትእግስት ከበደ ነግረዉናል።
ወ/ሮ ትእግስት ከበደ እንዳሉት የሚመሩት ድርጅት ሐበሻ ቪዉ ፊልሞችን ወደ ብሪታንያ ማምጣት እና ለእይታ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪዉ እንዲጎለብት የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይም ይገኛል። ኢትዮጵያ በፊልም ስራ፤ ከአፍሪቃ ቀዳሚዋ ነበረች። በአሁኑ ወቅት ከአፍሪቃ ናይጀርያን በፊልም ስራ ደምቃ የወጣች ሃገር ናት ከዝያ በመለጠቅ ኬንያ፤ ዩጋንዳ፤ ኮንጎ ፤ ብሎም ናሚቢያ በጣም ጥሩ በዓለም አቀፍ ተመልካችን ያፈሩ ፊልም ሰሪ ከሆኑ አፍሪቃ ሃገራት የሚጠቀሱ ናቸዉ።
በለንደኑ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የቀረበዉ የፀፀት ፊልም ደራሲ አቶ አለባቸው ደሳለኝ በበኩላቸዉ ፊልሙን የደረሱት ከሰላሳ ዓመት በፊት መሆኑን ገልፀዋል። ቀደም ሲል ፊልሙ የትናየት የሚል ስያሜ እንደነበረዉም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ ፊልሞች ይወጣሉ፤ ግን በአብዛኛዉ በሃገር ዉስጥ ነዉ ተደብቀዉ የሚቀሩት። ፊልሞቻችንን ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖራቸዉ እና የበለጠ ተደራሽ እንዲሆን በተለይ በትርጉም በጽሑፍ ቢሰራ እና የማስተዋወቅ ስራ ቢሰራ የኢትዮጵያን የፊልም ኢንንዱስትሪ ማጎልበት ይቻላl ብለዋል።
ወ/ሮ ትእግስት ከበደ እና አቶ አለባቸው ደሳለኝ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ