የኢትዮጵያ ሃገራዊ መግባቢያ ቋንቋ እና የቀረበ የህግ ጥያቄ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 12 2017የኢትዮጵያ ሃገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ጥያቄ
ኢትዮጵያ አንድ የጋራ የመግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖራት ያደርጋል ያሉትን የትምህርት ህግ እንዳይጸድቅ፣የኢትዮጵያውያን ባለሙያ ድርጅቶች ጥሪ አቀረቡ።
ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ የሆኑ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ድርጅቶች፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማመልከቻ፣ የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ የአገርን ጥቅምና አንድነት አማክሎ መተግበር ይኖርበታል ብለዋል።
ይህንኑ ማመልከቻ ያጸድቁት የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ድርጅቶች፣ኢትዮጵያዊነት፣ፒፕል ቱ ፒፕል፣ግሎባል የኢትዮጵያውያን ኢኒሼቲቭ፣በዲያስፖራ የተቋቋመው የኢትዮጵያውያን ማኀበርና ኢትዮጵያን አድን ፎረም ናቸው።
ለውይይት የቀረበው ረቂቅ ህግ
ድርጅቶቹ፤ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም፣ለዘመናት የኢትዮጵያ መንግስት የስራ ቋንቋ የሆነውንና፣ አሁን ባለው ህገ መንግስት የኢትዮጵያ መንግሥት የስራ ቋንቋ የሆነውን ዐማርኛን፣ ከሃገራዊ መግባቢያነት እንዲወጣ ክፍተት የሚፈጠር አንቀጽ ያለበት ረቂቅ የትምህርት ህግ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት መቅረቡን አመልክተዋል።
የትምህርት አስተዳደርና ምርምር ባለሙያ የሆኑት፣ዶክተር አዳነ ገበያው፣ "ኢትዮጵያዊነት" በተባለው ድርጅት ውስጥ የሚሳተፉ ሲሆን፣ ጉዳዩን በትኩረት እንደሚከታተሉት ለዶቸ ቨለ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
"እንግዲህ አሁን የምናወራው፣ ስለ መማሪያ ቋንቋ ሳይሆን እንደ አንድ የትምህርት ዐይነት ስለሚሰጠው ነው።ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይማራሉ፤ያ ተገቢ ነገር ነው።በቂ ዝግጅት እስከተደረገበት ድረስ፣ በቂ ስልጠና በቂ መጽሐፍት እስከተዘጋጁ ወይም ደጋፊ መጻሕፍት እስካሉ ድረስ፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቢማሩ ጥሩ ነው። ግን እንደ አንድ የትምርት ዐይነት አማርኛን ሊማሩ ይገባል። ምክንያቱም ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ፣ ወደ ፌደራል መንግስቱ መጥተው ሥራ ቢሰሩ፣ ፓርላማ ቢገቡ፣ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የሚጠቀሙበት አንድ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ቋንቋ ያስፈልጋል።"
አነጋጋሪው የዪኒቨርስቲ ተማሪዎች የፖሊሲ ስልጠና
ሕገ መንግሥቱን ይቃረናል
ከመስከረም 2015 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ የዋለው፣ይኸው የትምህርትና የስልጠና ፖሊሲ፣ ሕገ መንግስቱንም ሆነ የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት ምክር ዐሳብ የሚቃረን እንደሆነ፣ ዶክተር አዳነ ተናግረዋል።
"ከጥናቱ ተቃራኒ ነው፣ ከሕገ መንግስቱ ተቃራኒ ነው። ኢትዮጵያኖች ከኖሩበት ባህል፣ የትምህርት ባህል ተቃራኒ ነው።ሃገሪቱን የያዛትን ነገር ማንሳት ነው።
የፌደራል መንግስቱ የሥራ ቋንቋ የሆነው ዐማርኛ፣ ለአገራዊ መግባቢያነት፣በሃገሪቱ ትምህርት ቤቶች ሁሉ እንደ አንድ የትምህርት ዐይነት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ የሚያደርግ ፖሊሲ እንዲወጣ፣ መስራትና መከታተል ከጀመሩ ከሁለት አመት በላይ እንደሆናቸውም፣ የትምህርት ባለሙያው ገልጸውልናል።
የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ፣በዕውቀት ላይ ተመስርቶና የአገርን ጥቅምና አንድነት አማክሎ መቀረጽና መተግበር እንደሚገባው፣የባለሙያ ድርጅቶቹ ባቀረቡት ማመልከቻ የተገለጸ ሲሆን፣ሁሉም ቋንቋዎች እንዲጠናከሩ ምክረ ዐሳቦች ማቅረባቸውን ዶክተር አዳነ አስረድተዋል።
"ሁሉም ቋንቋዎች እንዲጠናከሩ ምክረ ዐሳብ ሰጥተናል እኛ፤ እዚህ ማመልከቻው ላይ በግልጽ አስቀምጠናል።በተቻለ እንደውም የቋንቋ ጥናት ተቋም ሁሉም ቋንቋ የሚዳብሩበትን የሚጠናከሩበት እንደገና ደግሞ በጊዜ ሂደት የሚቀራረቡበት የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋ የሚሆኑበትን ማሳደግ ይቻላል፣ያ መሰራት ያለበት ያለበት ነገር ነው።"
ዶይቸ ቨለ ስለጉዳዩ የትምህርት ሚኒስቴርን አስተያየት ለማካተት፣ ለህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍሉ ጥያቄዎች ብናቀርብም፣እስካሁን ድረስ ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም።
ረቂቅ አዋጁ ምን ይላል?
አገራዊ መግባቢያ ቋንቋን አስመልክቶ፣ፖሊሲው እና ረቂቅ የትምህርት አዋጁ ባሰፈረው ድንጋጌ፣አንድ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ፣ ከፌደራል የስራ ቋንቋዎች መኻከል የተማሪው ወይም የወላጅን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ፣በየደረጃው ባለው የትምህርት መዋቅር ተወስኖ ከሦስተኛ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ የሚሰጥ ይሆናል።" ይላል።
የፌዴራል የስራ ቋንቋ፣እንደ አንድ ትምህርት ዐይነት እንዲሰጥ፣ ለሚነሳው ጥያቄ ከዚህ ቀደም ከትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠ ማብራሪያ ላይ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክልሎች ላይ ጣልቃ በመግባት የሚያስገድደው እንዳልሆነና፣ በራሳቸው የሚወስኑት ጉዳይ እንደሆነ ተመልክቷል።
ታሪኩ ኃይሉ
ታምራት ዲንሳ