የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ - ኮከስ ጥሪ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 11 2017ኮከስ ስለ ወቅታዊ ፓለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ምን አለ
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ኮከስ አዲስ ባወጣው ዘለግ ያለ መግለጫ "ፖለቲካችን የተለመደውን የአፈና እና አግላይነት፣ የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ጠቅላይነት አጠናክሮ ቀጥሏል" ሲል ደምድሟል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም "እንዲገዙ ተፈርዶባቸው" በከፍተኛ ድብርት ውስጥ ናቸው ሲል ምሬቱን አስተጋብቷል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወደ ጦርነት ኢኮኖሚ ተሸጋግሮ፣ የኑሮ ውድነቱ ከሕዝብ አቅም በላይ በመሆኑ "ምሬትና ተስፋ መቁረጥ በአደገኛ ሁኔታ የመሰደድን ምርጫ እያጎላው መጥቷል"፡፡ በማለት ስብስቡ «ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት» ያለውን ተጨባጭ ሁናቴ ገልጿል።
ነባራዊዉ ማኅበራዊ ሕይወትንም "በሥራ አጥነት፣ በመፈናቀል፣ በማኅበራዊ ተቋማት መዳከምና የአገልግሎት መቋረጥ፣ በሠራተኞች ብሶት ታምቆ ይገኛል ብሎታል። ለዚህ አስረጂ ያደረገው ማረጋገጫ "በየአቅጣጫው የሚነሱ" ያላቸው ጥያቄዎች ናቸው። ከኮከሱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ።
"አገራችን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ እጅግ አሳሳቢ፣ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደምንገኝ እና በፖለቲካው፣ በማህበራዊው እና በኢኮኖሚው ያሉ ምስቅልቅል ሁኔታዎች በአገራችን ዘላቂ ሰላም እና ልማት እውን ለማድረግ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር፣ በሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን ጥላቻ እና መቃቃር ለማስቀረት እና ለመቀልበስ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር አለበት" ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተዳክሟል - ኮከስ
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሰብአዊና ምግባረ- ሰናይ ተቋማት ድምጻቸውን የማሰማትና ዓላማቸውን ለማስፈጸም በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ያለው ኮከስ "በሀገሪቱ በጥርጣሬና በጥላቻ መተያየት፣ ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን ለፖለቲካ በማዋል ሕዝብን በመከፋፈል ለተገዢነት ማዘጋጀትና ማመቻቸት "የገዢው ፓርቲ መታወቂያው" ሆኗል ሲልም ወንጅሏል።
መንግሥት ለመወያየትና ለድርድር ቁርጠኛ እንዳልሆነ እና "ከመገዳደል ወደ መደራደር ፖለቲካ" ለመሸጋገር ፍላጎት እንደሌለውም ጠቅሷል። በቅርቡ ይህንን ስብስብ የተቀላቀለው የኢሕአፓ ምክትል ሊቀመንበር ሃይማኖት አብርሃ«መንግሥት የሆነ አካል ሁሉን ችግር በጦርነት፣ በትጥቅ ትግል የሚፈታ አይደለም። በፖለቲካዊ መፍትሔዎች መፍታት ነው የሚገባው። የገዢው ብልጽግናን ፓርቲ ግን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ሁሉን ነገር በጦርነት ነው እየፈታ ያለው" ሲሉ ገልፀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የገዢው ፓርቲ ታዛዥ- ጉዳይ ፈጻሚና አስፈጻሚ እንዲሆን ከፍተኛ ጫና እየተደረገበት ይገኛል ያሉት እነዚህ ፓርቲዎች የጋራ ድምፅ ይሆነናል ያልነው መዋቅር "እንዲኮላሽ ተደርጓል" ሲሉም ገልፀዋል።"ምክር ቤቱንም ሙሉ በሙሉ አኮላሽቶታል «መንግሥት»። በአጠቃላይ ፓርቲዎችም ጭምር አደጋ ውስጥ ናቸው"
የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ ምላሽ
የፓርቲዎች ኮከስ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የዲሞክራሲ አጋሮች መዳከም ገጥማሟቸዋል ብሏል። አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ የውጪ ግንኙነቶች የአገርን ዘላቂ ጥቅም፣ ልማትና ሉዓላዊነት፣ የሕዝብን መብትና ክብር እንዲያገናዝቡ፣ መንግሥትም ለእውነተኛ ውይይትና ምክክር እንዲዘጋጅም ጠይቋል።
ፓርቲዎቹ ላነሱት ብርቱ ቅሬታ ነቀፊታ የመንግሥትን ምላሽ ለመጠየቅ ወደ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም። የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓርቲያቸውንአምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ባደረጉት ንግግር "ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች የተሻለ ዕሳቤ እና ሐሳብ ከማፍለቅ ይልቅ የተሻለ ሴራ መጎንጎንን እንደ ብቃት የወሰዱ ስለሆኑ አላደጉም" ሲሉ መዉቀሳቸው ይታወሳል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ