1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ

ሐሙስ፣ የካቲት 28 2016

ዛሬ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት "የጋዜጠኞችን ደኅንነት በማስጠበቅ ሥራቸውን ከፍርሃት ነፃ ሆነው" የሚሠሩበት እድል እንዲኖር ውትወታ ከማድረግ ባለፈ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ማድረጉን ቢገልጽም ጋዜጠኝነት አሁን ላይ ፈተና ላይ ስለመውደቁ ይታመናል።

https://p.dw.com/p/4dGic
Äthiopien | Versammlung Äthiopischer Medienrat in Addis Abeba
ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ

ምክር ቤቱ በጠቅላላ ጉባኤው ምን አለ ?

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ የፀጥታ መናጋት እና ቀውስ መቀጠሉን ፣ ጦርነት ብሎም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ድንጋጌ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙት ጋዜጠኞች ባለፈ፣ የማህበራዊ መገናኛ ዐውታሮችን ተጠቅመው በመንግሥት ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ፣ በመረጃ ትንተና የሚሳተፉ ግለሰቦች በተደጋጋሚ ሲታፈኑ፣ ሲታሰሩ እና ሲፈቱ ተስተውሏል።82 የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትንና ማህበራትን በአባልነት ማቀፉን ያስታወቀውና ዛሬ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት "የጋዜጠኞችን ደኅንነት በማስጠበቅ ሥራቸውን ከፍርሃት ነፃ ሆነው" የሚሠሩበት እድል እንዲኖር ውትወታ ከማድረግ ባለፈ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት ማድረጉን ቢገልጽም ጋዜጠኝነት አሁን ላይ ፈተና ላይ ስለመውደቁ ይታመናል። የምክር ቤቱ አባል ተቋማትም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እያለፉ መሆናቸውን የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢ ትዕግስት ይልማ ገልፀዋል።

የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ተጠየቀ

"የምክርቤታችን አባላት ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ውስጥ በመግባታቸው ፣ የኅትመት ዋጋ በመናሩ እና መገናኛ ብዙኃን እስከ መዘጋት የሚደርስ ችግር ውስጥ መውደቃቸው እንዲሁም የሳተላይት ክፍያ በመጨመሩ ሳቢያ አብዛኞቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ ይገኛሉ"።የጋዜጠኞች የመታሰር እና የመፈታት ሁኔታ በጎ የመሻሻል አዝማሚያ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም አሁን "እያሽቆለቆለ" እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ዐረጋዊ ገልፀዋል።"እንደሚታወቀው በሀገራችን የፕሬስ ነፃነት ከጥቂት ዓመታት በፊት ወገግ ያለ ተስፋ አሳይቶ እንደገና እያሽቆለቆለ መሆኑ በጣም ያሳስባል"።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ምክር ቤት
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ምክር ቤት ምስል Solomon Muchie/DW

መፍትሔ ያመጣል የተባለው የግልግል ዳኝነት ምን ላይ ደረሰ?

የጋዜጠኞች እና የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች እሥር

በዚህ ወቅት ተጽዕኗቸው ጎልቶ የሚታየው የበይነ መረብ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ትንተናዎች እና ዘገባዎች ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችም ይሁን ድርጅቶች በደረሰባቸው ማስፈራራት፣ ቢሮ ተሰብሮ ዘረፋ ፣ ዛቻ እና መሰል ጉዳዮች ከሙያው የመራቅ፣ የመታሠር አልያም ሀገር ጥሎ ለመሰደድ ፈተና ተጋፍጠዋል።መሠል ችግሮችን ይፈታል ተብሎ እምነት የተጣለበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የፈረመው የግልግል ዳኝነት ተግባራዊ አለመሆኑ አንዱ ችግር አባባሽ ጉዳይ መሆኑን አቶ አማረ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመረጃ ነፃነት ዐዋጅ እንዲፀድቅ ውትወታዎች እንዲቀጥሉ ተጠይቋል። 

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ