1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ

ረቡዕ፣ ሰኔ 29 2014

እሁድ በሜሪላንድ የተጀመረው ዝግጅት እስከ ቅዳሜ ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ የፌዴሬሽኑ ኘሬዚዳንት አቶ ዐቢይ ኑርልኝ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወታቸው ያለአግባብ እዲያልፍ የተደረጉ ፍትሕ እንዲሰጣቸው የጠየቀው ፌዴሬሽኑ ሁኔታው በአስቸኳይ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ በወንጀሉ የተሳተፉ በሕግ እንዲጠየቁ አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/4DlFj
ESFNA 39 Annual sports & culture event
ምስል ESFNA

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ 39ኛ ዓመታዊ ዝግጅት

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ 39ኛው ዓመታዊ ዝግጅት በመካሄድ ላይ ነው። በሜሪላንድ ኮሌጅ ፓርክ ባለፈው እሁድ የተጀመረው ዝግጅት እስከ ቅዳሜ ሐምሌ ሁለት ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ የፌዴሬሽኑ ኘሬዚዳንት አቶ ዐቢይ ኑርልኝ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ህይወታቸው ያላግባብ እየተቀጠፈ ያሉ ፍትሕ እንዲሰጣቸው የጠየቀው ፌዴሬሽኑ ሁኔታው በአስቸኳይ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ በወንጀሉ የተሳተፉ ሁሉ በሕግ እንዲጠየቁ አሳስቧል።

እንደ ጎርግሮሳዊው ዘመን አቆጣጠር በ1984 የተመሠረተው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የባህልና የስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን የበለጸገውን የኢትዮጵያን ባህልና ቅርስ ለማስተዋወቅና አዎንታዊ አስተሳሰብን ለመገንባት የተቋቋመ ድርጅት ነው።

ፌዴሬሽኑ ይህን ተልዕኮውን ለመወጣት፣ ኢትዮጵያውያን  ተገናኝተው እንዲቀራረቡ የንግዱን ማኀበረሰብ ለመደገፍና ወጣቶችን በተለያዩ መንገዶች ለማብቃት በዋነኛነት የእግር ኳስ ውድድሮችንና ሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችንና የባህል ዝግጅቶችን በየዓመቱ ያካሄዳል።

የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ በጣም ያሳሰበው እንደሆነ የገለጸበትን መግለጫ አውጥቷል።የፌዴሬሽኑ ኘሬዚዳንት አቶ ዐቢይ ኑርልኝ ግድያና መፈናቀሉን ፌዴሬሽኑ እንደሚያወግዘው ይናገራሉ።

"በኢትዮጵያ በተደረገውን አሰቃቂ ግድያ ና መፈናቀል የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ ከፍተኛ ሐዘኑን ይገልጻል። በዚህ በያዝነው ሣምንት ውድድሩ በሚካሄድበት ጊዜ፣ በየቀኑ ይህንን ድርጊት በመቃወም ለተጎዱ ወገኖቻችን ሐዘናችንን የምንገልጽበትና መጽናናት እግዚአብሔር እንዲያጎናጽፋቸው የምንለምንበት ጊዜ ይሆናል።" ፌዴሬሽኑ በዚሁ መግለጫው፣ሕይወታቸው አለአግባብ እየተቀጠፈ ያሉ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠይቆ፣ ሁኔታው በአስቸኳይ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ በወንጀሉ የተሳተፉ ሁሉ በሕግ እንዱጠየቁ አሳስቧል።

ESFNA  39 Annual sports & culture event
ምስል ESFNA

የፊታችን ቅዳሜ የሚጠበቀው ዓመታዊ የስፖርትና የባህል ዝግጅቱ፣አእስካሁን በተሣካ ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። "እያዩ ዘነበ እባላለሁ፤የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኜ እየሰራሁ ነው።በአጠቃላይ ለዝግጅታችን ትልቅ ወጪ ነው ያደረግነው።ከሁለት ዓመት በኇላ መምጣታችን ስለሆነ ብዙ ህዝብ እንደሚመጣ ግምት ውስጥ አስገብተን የምናየው ነገር የሚያሳየንም እሱን ነው።የፊታችን ዐርብ ኢትዮጵያ ቀን ትልቁ ቀናችን ነው፤ከሃገር ቤትም እዚህም ያሉ አርቲስቶች የሚሳተፉበት ነው የሚሆነው እና ያን ዕለት የሚቀር ሰው አይኖርም፤ ባህላዊ ዝግጅቶችንም እናቀርባለን።በማግስቱ የመዝጊያው ዝግጅት ነው የሚሆነው፤መዝጊያው የዋንጫ ጨዋታ የሚኖርበት ቀን ነው።"

በኮቪድ በሽታ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው  39ኛው ዓመታዊ ዝግጅት፣ በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት መካሄዱ ተገቢ መሆኑን አስተያየቱን የጠየቅነው ወጣት ዘላለም ይናገራል።

"እኔ የተወሰነና ይሄ የተከሰተው ሁኔታ ከመሆኑ በፊት የታሰበ ስለነበር፣ መተላለፍ ነበረበት የሚለውን ነገር አልስማማበትም።ለስቴዲየምና ለመሳሰሉት ብዙ ወጪ አውጥተውበታል።" አቶ ኤፍሬም አበራ በበኩሉቸው ዝግጅቱ በዚህ ወቅት መካሄድ አልነበረበትም ባይ ናቸው።

"ብዙዎቻችን ያዘንበት ጊዜ ነው።ን ጹሐን ዜጎች ያላግባብ የሚገደሉበት፣ ጦርነት አይደለም ንጹሐን እየተገደሉ አንተ ደስታ አድርገህ ማሳለፍ ነገሩን እንደመደገፍ ይመስለኛል።የሁለት ወር ህፃን ልጅ ስትገደል ምን ማለት ነው?!

ታሪኩ ኃይሉ 
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ