1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ባንኮች ለማጭበርበር ምን ያህል ተጋላጭ ናቸው?

ዓርብ፣ ግንቦት 26 2014

የኢትዮጵያ የፍትኅ ሚኒስቴር በ155 የወንጀል መዛግብት ላይ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ይፋ ሲያደርግ ሚኒስትር ድኤታው ፍቃዱ ጸጋ "ባለፉት አራት አመታት አካባቢ ብቻ ከ1.8 ቢሊዮን [ብር] በላይ የማጭበርበር ሒደቶች ነበሩ" ብለዋል። የኢትዮጵያ ፍትኅ ሚኒስቴር እንደሚለው "በተፈጸሙ ወንጀሎች በዋናነት የባንክ አመራሮች እና ሰራተኞች" ተሳትፈዋል

https://p.dw.com/p/4C9Rv
Äthiopien Commercial Bank of Ethiopia in Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ ባንኮች ለማጭበርበር ምን ያህል ተጋላጭ ናቸው?

ባለፈው ሰኞ የኢትዮጵያ የፍትኅ ሚኒስቴር በ155 የወንጀል መዛግብት ላይ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት ይፋ ሲያደርግ ሚኒስትር ድኤታው ፍቃዱ ጸጋ "ባለፉት አራት አመታት አካባቢ ብቻ ከ1.8 ቢሊዮን [ብር] በላይ የማጭበርበር ሒደቶች ነበሩ" ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ፍቃዱ እንዳሉት ይኸ በኢትዮጵያ ፍትኅ ሚኒስቴር "የምርመራ ሒደት ብቻ" የተደረሰባቸው እና  "ሪፖርት የተደረጉ" ናቸው።  ሚኒስትር ድኤታው "ሁሉንም ጉዳዮች መርምሮ ማስቀጣት ካለመቻሉም በላይ፤ ባስቀጣናቸውም ወንጀሎችም ላይ የተመዘበረውን የህዝብ ሐብት፤ የባንኮች ሐብት ማስመለስ አልተቻለም" ሲሉ ተናግረዋል። በፍትኅ ሚኒስቴር መግለጫ መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ ፣የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሁም ወጋገን ባንክ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመባቸው ናቸው።  

የፍትኅ ሚኒስቴር አደረኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት ባንኮች ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በዋናነት የባንክ አመራሮች እና ሰራተኞች ተጠያቂ አድርጓል። የኢትዮጵያ ባንኮች ከየፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት ለመሸሽ ማስረጃዎችን እንደሚደብቁ፣ ድርድርን እንደሚያስቀድሙ የኢትዮጵያ የፍትኅ ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት እንደደረሰበት ገልጿል። ገለልተኛ ኦዲተር አለመኖር፣ መሠረታዊ የፋይናንስ ተቋማት ሕጎችን መጣስ ወይም በስራ ላይ አለማዋል እንዲሁም የባንኮች ዘመናዊ አሰራርን አለመከተል ሌሎች የተጠቀሱ ችግሮች ናቸው። የደንበኞች ምስጢራዊ መረጃዎችን ምልከታ የሚገድብ አሰራር አለመኖሩ አስተዋጽዖ አንዳበረከተም ተጠቅሷል። የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ በባንኮች ላይ ለሚፈጸመው ማጭበርበር ወጥ የሆነ ብሔራዊ መታወቂያ አለመኖር የራሱ ሚና እንዳለው ሲናገሩ ተደምጠዋል።  

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ገበያ እየተወሳሰበ ሲሔድ ባደጉት አገሮች ጭምር ያሉ ባንኮች ለማጭበርበር ሲጋለጡ ይታያል። በተለይ ባንኮች በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሰጧቸው የኦንላይን የባንክ አገልግሎቶች፣ በተንቀሳቃሽ ስልክ ገንዘብ ማዘዋወር ወይም ሞባይል ባንኪንግን የመሳሰሉት ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት አላቸው የሚባሉት እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች ጭምር ባለፉት አመታት የገንዘብ ተቋማትን ለማጭበርበር እንዳጋለጡሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ ባንኮች ለእንዲህ አይነት ከቴክኖሎጂ ከአገልግሎት መስፋፋት ጋር ለሚያያዝ ማጭበርበር ምን ያክል ተጋላጭ ናቸው? የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ በጉዳዩ ላይ ለዶይቼ ቬለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከአቶ አብዱልመናን ጋር የተደረገውን ቃለመጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ