የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ምን ያሳያል?
ረቡዕ፣ ኅዳር 25 2017የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ጉድለት በ2017 የመጀመሪያ መፈንቅ ከፍተኛ ለውጥ እንደታየበት ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ ይፋ ባደረገው ሁለተኛ የፋይናንሺያል ስቴቢሊቲ ሪፖርት (Financial Stability report) መሠረት የንግድ ሚዛን ጉድለቱ እየቀነሰ በመሔዱ የሀገሪቱ የክፍያ ሚዛን ተሻሽሎ ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ወራት ትርፍ 573 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ይጠቁማል። በሪፖርቱ መሠረት የሀገሪቱ የክፍያ ሚዛን በ2016 ተመሳሳይ ወቅት 1.258 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት ነበረበት።
“…በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ…”
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ማኅረቱ ከሁለት ሣምንታት በፊት ብልጽግና ፓርቲ ከሚቆጣጠረው ፋና ብሮድካስቲናግ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የሀገሪቱ የክፍያ ሚዛን የደረሰበት ደረጃ በኢትዮጵያ ታሪክ “ለመጀመሪያ ጊዜ” እንደሆነ ተናግረው ነበር።
“ባለፈው ዓመት የነበረው ጉድለት ወደ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ነበረ” ያሉት አቶ ማሞ “ዘንድሮ ከ573 ሚሊዮን [ዶላር] በላይ surplus ሆኗል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ለረዥም ዓመታት ከፍተኛ ጉድለት ተሸክሞ የቆየውን የንግድ ሚዛን ማረቅ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ተግባራዊ በሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ ከተካተቱ አላባዎች አንዱ ነው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ የንግድ ሚዛኑ ላይ የታየው ለውጥ ከወጪ ንግድ መሻሻል እና ከገቢ ንግድ መቀዛቀዝ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ የምትሸምተው “በኤኮሚ መቀዛቀዝ” መቀነሱን የሚናገሩት አብዱልመናን ብሔራዊ ባንክ የሚከተለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ እና የኤኮኖሚ እርግጠኝነት ማጣት ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል። “ኤኮኖሚው ወደ ጤናው በሚመለስበት ሰዓት መጨመሩ አይቀርም” የሚል እምነት አላቸው።
የኢትዮጵያ ባንኮች “በአማካኝ በየወሩ ከወጪ ንግድ (Export) ብቻ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር” እንዳገኙ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ተናግረዋል። ባንኮቹ ለደንበኞቻቸው በየወሩ 713 ሚሊዮን ዶላር ሸጠዋል። አቶ ማሞ እንዳሉት ባንኮች ሐዋላን ሳይጨምር “ከሸቀጦች እና አገልግሎት የወጪ ንግድ ባለፉት ሦስት ወራት በአማካኝ ወደ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሪ ገዝተዋል።
“ለደንበኞቻቸው የሸጡት የውጪ ምንዛሪ በአንጻሩ ወደ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ቅዳሜ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት የወጪ ንግድ በ2017 የመጀመሪያ መንፈቅ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ81 በመቶ ጨምሯል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን የወጪ ንግድ የጨመረበት ልክ “ከፍተኛ” እንደሆነ ቢስማሙም ከወጪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ምክንያት የተከሰተ መሻሻል “ዘላቂ ነው” ብሎ መውሰድ እንደማይቻል ያስረዳሉ።
“የውጪ ምንዛሪ ለውጥ ስለመጣ ድንገተኛ እድገት አለ። ከዚያ በኋላ ግን እንደ መጀመሪያው ይሆናል ማለት አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ከአራት ወራት ገደማ በፊት የውጪ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና በፍላጎት እንዲከወን ከተደረገ በኋላ የብር የምንዛሪ ተመን ከ100 በመቶ በላይ ተዳክሟል። በመደበኛው ገበያ በ57 ብር ይመነዘር የነበረው አንድ ዶላር በአሁኑ ወቅት ወደ 125 ብር ከ50 ሣንቲም እንዳሻቀበ የብሔራዊ ባንክ አማካኝ ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን አመልካች ይጠቁማል።
ብር በከፍተኛ ፍጥነት እየተዳከመ ሲሔድ በባንኮች እና በትይዩ ገበያው መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን ልዩነት 5 በመቶ ገደማ እንደደረሰ የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያሳያል። በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው ልዩነት እንዲጠብ መንግሥት ፍራንኮ ቫሉታን ለማቆም ያሳለፈው ውሳኔ እና ባንኮች በውጪ ምንዛሪ መግዣ እና መሸጫ ተመኖቻቸው መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያጠቡ በብሔራዊ ባንክ የተሰጣቸው ትዕዛዝ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ዶክተር አብዱልመናን አስረድተዋል። በብሔራዊ ባንክ በሪፖርት መሠረት በጥቅምት ወር የብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ክምችት በሰኔ ከነበረበት በ240 በመቶ ጨምሯል።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት በገበያው ፍላጎት እንዲከወን ሐምሌ 22 ቀን 2016 ሲወሰን ባንኩ የነበረው የውጪ ምንዛሪ ክምችት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ነበር። በሰኔ 2016 በአንጻሩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበረው የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ ከሦስት ወራት በኋላ የማዕከላዊው ባንክ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ወደ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። በዋንኛነት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተፈራረመው ሥምምነት ያገኘው ገንዘብ ለውጪ ምንዛሪ ክምችቱ ማደግ ቀዳሚ ሚና እንደሚኖረው ዶክተር አብዱልመናን ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ፣ ከሐዋላ፣ ከውጪ ቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ የምታገኘው የውጪ ምንዛሪ ከጨመረ በባንኩ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ላይ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። ዶክተር አብዱልመናን ኤኮኖሚው በመቀዛቀዙ የገቢ ንግድ በመደከሙ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ፍላጎት እንዲቀንስ ስለሚያስገድድ የብሔራዊ ባንክ የክምችት ጥሩ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
የምንዛሪ ግብይት ላይ ለውጥ ሲደረግ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ በሁሉም የነበረው የውጪ ምንዛሪ ከ3.1 ቢሊዮን ዶላር ወደ 5.8 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። የግል ባንኮች በጥቅምት ወር የነበራቸው የውጪ ምንዛሪ ክምችት 2.4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያሳያል። የባንኩ ገዥ አቶ ማሞ እንዳሉት የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ከመደረጉ በፊት የኢትዮጵያ የግል ባንኮች የነበረባቸውን 518 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ከፍለዋል።
የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ ዶላርን በመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች የክፍያ ግዴታ በበነበረባቸው ባንኮች ላይ ያስከተለውን ኪሳራ ግን የብሔራዊ ባንክ ገዥ አልገለጹም።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን የንግድ ባንክ ዕዳ ለመክፈል እና የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ መንግሥት የሚያወጣው የ900 ቢሊዮን ብር ቦንድ ጉዳይ በሪፖርቱ ቢጠቀስም የሚያስከትለው ሥጋት ግን በዝርዝር አልቀረበም።
የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት የሥራ ክንውን (Ooperational Risk) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ አሳይቷል። ሁሉም 28 ባንኮች ሥርቆት እና ማጭበርበር እንደገጠማቸው ሪፖርቱ ያሳያል። የባንኮች ሠራተኞች ጭምር የተሳተፉባቸው ድርጊቶች በሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች፣ ሐሰተኛ ቼኮች፣ ሐሰተኛ የባንክ ማስተማመኛዎች (guarantees)፣ ሐሰተኛ የስልክ ጥሪዎች እና መልዕክቶች በመጠቀም የተፈጸሙ ናቸው። ባንኮቹ በእነዚህ ድርጊቶች 1.3 ቢሊዮን ብር ከስረዋል።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ