የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ጀመረ
ዓርብ፣ መጋቢት 16 2014የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዛሬ ልዩ ልዩ የሃይማኖት ተቋማት የፀሎት ሥነ ሥርዓት እንዲያደርጉ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ደግሞ የሰላም መልእክት እንዲያስተላልፉ በማድረግ ሥራውን ጀምራል። የሃይማኖት መሪ አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ መረጋጋት እና እርቅ እንዲሰፍን ተመኝተዋል።
በአዋጅ ቁጥር 1265/ 2014 ዓ.ም የተቋቋመው ይህ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሕዝብ ከተጠቆሙ 632 ሰዎች መካክል 11 ሰዎችን በኮሚሽነርነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ መሾማቸው ይታወሳል።
የምክክር ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በዛሬው የፀሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የአገር ሽማግሌዎች ለብዙ ዓመታት ተሰሚነት እንዳይኖራቸው የተደከመበት ቢሆንም ኢትዮጵያን ክብዙ መከራና ጥፋት እንደታደጉ ምስክሮች ነን፣ የሀገር ሽማግሎዎች ተሰምተው ቢሆን ኖሮ የሰሜን ኢትዮጵያው ችግር ባልደረሰ ነበር ብለዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን አክለውም ከደቂቅ እስከ ልሂቅ ፣ ወጣት ፣ አዛውንት፣ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለብሔራዊ ምክክር እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል። ኮሚሽኑ የተጣለበትን ከፍተኛ አገራዊ ሃላፊነት እንዲያሳካ ይህ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኮሚሽኑ ሥራ ማመቻቸት ሲሆን ዋናው ተግባርና ውሳኔ ግን የሕዝብ መሆኑ ሊታወቅ ይገበልም በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ ፣ በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ በማድረጉ ማስፈለጉ መገለፁ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያቶችን በመለየት ገለልተኛ ናቸው ተብለው በተሾሙት 11 ሰዎች እየተመራ ጉዳዮቹ ላይ ውይይት እንዲካሄድባቸው ያደርጋል።በዚህም መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ይሰራል በሚል ውጥን ተይዞ መቃቋሙ ይታወሳል።
ሶሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ