የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ሥምምነት የግብጽ ፕሬዝደንት “በቅርብ እየተከታተሉ ነው”
እሑድ፣ ታኅሣሥ 20 2017የግብጽ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት የደረሱበትን ሥምምነት “በቅርብ እየተከታተሉ” እንደሚገኙ መናገራቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ። ፕሬዝደንቱ ሥምምነቱ “በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ጸጥታ እና መረጋጋት ለማስፈን አስተዋጽዖ ያበረክታል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ በአንካራ ተገናኝተው ወደፊት ለመደራደር የደረሱበት ሥምምነት “ከዓለም አቀፍ ሕግ መርኆዎች ጋር የተስማማ ይሆናል” ብለው እንደሚጠብቁ ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ መናገራቸውን በጽህፈት ቤታቸው በኩል የወጣ መግለጫ ይጠቁማል።
አል-ሲሲ በጉዳዩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ አስተያየት የሰጡት ትላንት ቅዳሜ ከፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት ነው። ከአል-ሲሲ በስልክ የተነጋገሩት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ ባለፈው ሣምንት ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መነጋገራቸው አይዘነጋም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ በቱርክ ፕሬዝደንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን አሸማጋይነት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ውጥረት ለመፍታት ወደፊት “ቴክኒካዊ ድርድር” ለማካሔድ የተስማሙት ባለፈው ታኅሳስ 3 ቀን 2017 ነበር።
ሁለቱ መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ መሠረት በቱርክ አመቻቺነት ድርድሩ በመጪው የካቲት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ሀገራቱ ድርድሩን በአራት ወራት ውስጥ አጠናቀው ለመፈራረም ዕቅድ አላቸው።
የአንካራው የጋራ መግለጫ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ሥር የኢትዮጵያ ወታደሮች ለከፈሉት “መስዋዕትነት” ሶማሊያ “እውቅና” የሰጠችበት ጭምር ነበር። ይሁንና በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና ማረጋጋት የሶማሊያ ተልዕኮ (AUSSOM) ውስጥ ግን ኢትዮጵያ ሳትካተት ቀርታለች። ግብጽ በአዲሱ በተልዕኮ ሥር ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ እንደምታዘምት ባለፈው ሰኞ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃለች።
ፕሬዝደንት አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ “በአፍሪካ ቀንድ ጸጥታ እና መረጋጋት እና በግብጽ ብሔራዊ ደሕንነት መካከል ጥብቅ ቁርኝት” መኖሩን ለፈረንሳይ ፕሬዝደንት ተናግረዋል። ግብጽ “በሁለትዮሽ ትብብርም ይሁን በሶማሊያ ጥያቄ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመሳተፍ የሶማሊያን ጸጥታ እና መረጋጋት ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን” ገልጸዋል።
የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ለተልዕኮው ይሁንታ በሰጠበት እና ባለፈው አርብ በተካሔደ ስብሰባ የተሳተፉት በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ “በሶማሊያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና በቀጠናው ምንም ገንቢ ሚና የሌላቸው ተጨማሪ ተዋናዮች ግዴለሽ ጥረታቸውን እንዲተዉ ሊመከሩ ይገባል” ብለው ነበር።
በተልዕኮው የሚሳተፉ ወታደሮች ድልድል በሁለትዮሽ ሥምምነት እንዲወሰን መደረጉን በስብሰው የተገኙት የሶማሊያ ተወካይ ተናግረዋል። እስካሁን ሀገራት 11,000 ወታደሮች ለማዝመት ቃል መግባታቸውንም ለጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ገልጸዋል።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ