የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ለተፈጸሙ ጥሰቶች እውቅና እንዲሰጥ አሜሪካዊ ዲፕሎማት መከሩ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 9 2017የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብአዊ መብቶች “ጥሰት የፈጸሙ በተለይ የሠራዊት አባላትን ሙሉ ምርመራ እስኪደረግ ድረስ በአስተዳደራዊ ፈቃድ ከሥልጣን እንዲያነሳ” አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት ምክረ ሐሳብ አቀረቡ። በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍትኅ አምባሳደር ቤትዝ ቫን ስካክ በሀገሪቱ ለተፈጸሙ በደሎች ከፌድራል መንግሥት እውቅና እንዲሰጥ መክረዋል።
አምባሳደር ቤትዝ ቫን ስካክ ምክረ ሐሳቦቹን ያቀረቡት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የተወሰኑ ሃገራት ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ ዛሬ ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው አምባሳደር ቤትዝ የፍትኅ ሚኒስትር ሐና አርዓያ ሥላሴ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ኮሚሽነር ራኬብ መለሠን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተገናኝተው ነበር። የፍትኅ ሚኒስቴር እና የጸጥታ ጥናት ኢንስቲትዩት ባዘጋጁት እና በኢትዮጵያ ሽግግር ፍትኅ ሒደት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ላይም ተሳትፈዋል።
አሜሪካዊቷ ዲፕሎማት የአፍሪካ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ ዛሬ ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሽግግር ፍትኅ ትግበራ ረገድ “በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሒደት ተበረታተናል” ቢሉም “የሲቪክ ምኅዳሩ መዘጋቱን እና በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የጭካኔ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን የሚጠቁሙ ዘገባዎች መኖራቸውን እናውቃለን” ሲሉ ተናግረዋል።
በድሮን ጥቃቶች በአማራ ክልል የሚገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው
“ይኸ በእርግጠኝነት በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሽግግር ፍትኅን ፈጽሞ የማይቻል እንኳ ባይሆን አስቸጋሪ ያደርገዋል” ያሉት አምባሳደር ቤትዝ ሰዎች እውነቱን ለመናገር ነጻነት ከሌላቸው በፍትኅ ሒደት ውስጥ ሊሳተፉ እንደማይችሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ጠቁመዋል። ዲፕሎማቷ በሁለቱ ክልሎች በመካሔድ ላይ ያሉት ግጭቶች በፖለቲካዊ ውይይቶች ሊፈቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።
“ለረዥም ጊዜ ሲፈጸሙ የቆዩ የጭካኔ ተግባራትን እና በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶችን ለመፍታት ለሚያስችል ለአጠቃላይ የሽግግር ፍትኅ መሠረት ለመጣል ምን ዓይነት እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ከመንግሥት እየጠበቅን ነው” ያሉት አምባሳደር ቤትዝ ሊደረጉ ይገባል ያሏቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
“ጥሰት በመፈጸም የተጠረጠሩ በተለይ የሠራዊት አባላትን ከሥልጣን በማንሳት በወንጀል የተከሰሱትን ሙሉ ምርመራ እስከሚደረግ ድረስ አስተዳደራዊ ፈቃድ መስጠት” ትርጉም ያለው እርምጃ እንደሚሆን ገልጸዋል። “ለተፈጸሙ በደሎች ከፌድራል መንግሥት እውቅና መስጠት” አምባሳደሯ ያቀረቡት ሌላው ምክረ ሐሳብ ነው።
“እነዚህ ሒደቶች ግልጽ፣ አካታች እና ተጎጂዎችን ያማከሉ ከሆኑ አጋር ለመሆን ዝግጁ ነን” ያሉት የአሜሪካ ዲፕሎማት ለሽግግር ፍትኅ አምስት ሕጎች መዘጋጀታቸውን በአዎንታ እንደሚመለከቱት ተናግረዋል። የሕግ ረቂቆቹን መንግሥት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውስጥ ለሚገኙ ባለሙያዎች ትችት እና ጥቆማ ክፍት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑንም በበጎ አንስተዋል።