1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቃለ ምልልስ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር

ሰኞ፣ ኅዳር 23 2017

የኤርትራው ፕሬዝደን በሶማልያ ግብፅና ኤርትራ መካከል የተካሄደውን የሶስትዮሽ ግንኙነት ፀረ ኢትዮጵያ አስመስለው የሚያቀርቡትን የተለመድ መረጃ የማዛባት እና የማደናገር ስራ በማለት አጣጥለውታል። አሁን ኢትዮጵያ በራስዋ ከፍተኛ ችግር ላይ ትገኛለች፥ ይህን አሳሳቢ ሁኔታ ለመፍታት እንሰራለን እንጂ ተጨማሪ ችግር የምንፈጥርበት ፍላጎት የለንም ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4neqj
Ägypten I Präsident Abdel Fattah El-Sisi empfängt den eritreischen Präsidenten Isaias Afwerki im Bundespalast
ምስል Egyptian President Office//APAimages/IMAGO

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቃለ ምልልስ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር

ለሁለት ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ የቆየው እና በዋነኝነት ትኩረቱን በዓለምአቀፍ ፖለቲካ፣ የምስራቅ አፍሪካ ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች የግጭት እና ፖለቲካዊ ውጥረት አጀንዳዎች ያደረገ የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቃለመጠይቅ፥ በኤርትራ ሀገራዊ ቴሌቭዥን ቀጥታ ስርጭት ተብሎ የተላለፈው ቅዳሜ ማታ ነበር። ፕሬዝደንቱ ሁለት ሰዓታት ያክል ስለአሜሪካ ምርጫ እና ውጤቱ፣ የቻይና የኢኮኖሚ እድገት፣ የሱዳን ግጭት እና የውጭ ሐይላት ተሳትፎ፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና ሀገራቸው ከሌሎች የቀጠናው ሀገራት ስላላት ግንኙነት የተናገሩ ሲሆን፥ ቀሪው ሰላሳ ደቂቃ ደግሞ የኤርትራ የውስጥ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ አጀንዳዎች ዳሰውበታል።

የኤርትራ አፋሮች ጥሪና የፖለቲካ ጥያቄ

ከኤሬ ቲቪ ጋዜጠኛ በኩል "የኢትዮጵያ ህዝብ በማያቋርጥ ውስጣዊ ግጭቶች እረፍት አላገኘም። የሶማልያ እና ኢትዮጵያ መሳሳብ ደግሞ ሌላ ችግር ነው። አንዳንዶች በሶማልያ፣ ግብፅ እና ኤርትራ መካከል የተካሄደው የሶስትዮሽ ግንኙነት ፀረ ኢትዮጵያ አስመስለው የሚያቀርቡት አለ። እዚህ ላይ ምን ይላሉ ?" ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የኤርትራው ፕሬዝደን ዘለግ ያለ ምላሽ የሰጡበት ሲሆን፥ የሶስትዮሽ ግንኙነቱ ኢትዮጵያን ለመጉዳት አስመስሎ በተለያዩ አካላት መገለፁን የተለመድ መረጃ የማዛባት እና የማደናገር ስራ በማለት አጣጥለውታል። እንደ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ገለፃ፥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በራስዋ ከፍተኛ ችግር ላይ ትገኛለች፥ ይህ አሳሳቢ ሁኔታ ለመፍታት እንሰራለን እንጂ ተጨማሪ ችግር የምንፈጥርበት ፍላጎት የለንም ብለዋል።

30ኛው የኤርትራ የነጻነት በዓል፤ ኢሳያስ አፈወርቂና ኤርትራውያን
"ግብፅ የራሳቸው አስተሳሰብ እና ምርጫ ሊኖራቸው ይችላል። እኛ ተገናኝተን የምንወያይበት ጉዳይ ግን መልሶ ወደ የእርስ በርስ ፍጥጫ የሚያስገባ አይደለም። ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር የሚያገናኝ ነገር የለውም። የኢትዮጵያ ሁኔታ በራሱ በልዩ ችግር ውስጥ ባለበት፥ የኢትዮጵያ ችግር ለማባባስ ብለህ የምትፈጥረው ግንኙነት የለም። በኢትዮጵያ አሳሳቢ ሁኔታ ካለ፥ ሁላችንም የሚያሳስብ ስለሆነ እንዴት እንፍታው ብለህ ትነጋገራለህ። ይህ ሚስጥር አይደለም" ብለዋል።


በዚህ በተጨማሪ በሱዳን ስላለው ሁኔታ የተናገሩት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፥ የሱዳን ችግር የተወሳሰበ ሆንዋል፥ የሱዳን የውስጥ ጉዳይ ከሱዳናውያን እጅ ወጥቷል፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሁኔታው ከድጡ ወደማጡ ወስዶታል ብለዋል። የሀገሪቱ ፖለቲካ በዋነኝነት በሀገሪቱ የበላይ ሸንጎ መመራት አለበት ብላ ኤርትራ እንደምታምን፥ ይህ ሐሳብ ደግሞ በግንቦት ወር 2022 ለሱዳን መቅረቡ ተናግረዋል። 
ፕሬዝደንቱ ስለትግራዩ ጦርነት ሲናገሩ፥ እርሳቸው 'ማሌሊት' ብለው ሲጠሯቸው ያመሹት የህወሓት መሪዎች ለጦርነት ዝግጅት ላይ እንደነበሩ እና ይህ ተገንዝበውም ለማስቆም ጥረት ማድረጋቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል። ጦርነቱ ያስቆመው የፕሪቶርያ ስምምነት ፕሬዝደንት ኢሳያስ በውጭ ሐይላት የተዘጋጀ ያሉት ሲሆን፥ የሰላም ውሉ ሳይፈፀም ደግሞ ሌላ ጦርነት በአማራ ክልል መለኮሱን አንስተዋል።

ኢሳያስ አፈወርቂ ለጉብኝት ቻይና  ሲገቡ
ኢሳያስ አፈወርቂ ለጉብኝት ቻይና ሲገቡምስል Chen Zhonghao/Xinhua/IMAGO

የኤርትራው ፕሬዝዳንት የቻይና ጉብኝት አንደምታ
ፕሬዝደንት ኢሳያስ "ፕሪቶርያ ለእኛ አይመለከተንም። የፕሪቶርያው ስምምነት እንደግፈዋለን፣ አንደግፈውም ብለን የምንናገርበት ምክንያት የለም። ጦርነት የሚያስቆም ሁኔታ መጣ። እሺ ከፕሪቶርያ በኃላስ ምንድነው ? አጀንዳው የውስጥ ተዋናዮች የሚይዙት ቢሆን ጥሩ ነበር። የፕሪቶርያው ስምምነት ቢተገበር በራሱ ይህ ሁሉ ችግር ባልመጣ ነበረ። ይሁንና እነዚህ የፕሪቶርያ ውል ያዘጋጁ አካላት ውሉ እንዲጣል አደረጉ። የአማራ ጦር መሳርያ ማውረድ ከሁሉ አስቀድሞ መረጡ። ሌላ አዲስ ጦርነት ማወጅ ስለምን አስፈለገ ?" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝደንት ኢሳያስ፥ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ጋር ስለተወያዩባቸው ጉዳዮች፣ ሑመራ ኦምሓጀር ደንበር ሲከፈት ከህወሓቱ መሪ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ስለነበራቸው ንግግር እና ሌሎች ነጥቦች አንስተዋል። 

ስለኤርትራ ውስጣዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮች ያነሱት ፕሬዝደንቱ፥ መንግስታቸው በውሃ፣ መንገድ፣ ቴሌኮምኒኬሽን እና የቤቶች ልማት እቅድ አውጥቶ እየሰራበት መሆኑ፥ በቀጣይ በተያዙ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የኤርትራ ዲያስፖራ ለማሳተፍ እቅድ ስለመያዙ ተናግረዋል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ