የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ፈጸምኩ ያለው የሰላም ስምምነት ዳራ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 3 2017
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ውስጥ በስፋት ስንቀሳቀሱ ከቆዩቱ ከታጣቂዎች ጋር የሰላም ስምምነት አደረኩ ካለ ወዲህ ታጣቂዎች ባለፉት ጢቂት ዓመታት በስፋት ስንቀሳቀሱና ዘርፈ ብዙ ውድመቶችን ስያስከትሉ ከነበሩባቸው ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በርካታ ወረዳዎች በስፋት ከነትጥቃቸው ስመለሱ ታይተዋል፡፡ እንደ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች መረጃ ከሆነ በሳምንቱ መጨረሻ ከሁለቱ ዞኖች በተጨማሪ ከምዕራብ ኦሮሚያው ቀሌም ወለጋ ዞንና ከሰሜን ሸዋ ዞንም ታጣቂዎቹ በብዛት ሰላማዊውን መንገድ ተቀላቅለዋል ነው የተባለው፡፡ሱሉልታ፦ በኦነግ-ኦነሰ አዲስ ጥቃት ያጠላው ስጋት
የታጣቂዎቹ ከነትጥቃቸው መግባት
ባለፉት 30 ኣመታት በተባበሩት መንግስታት ውስጥ በዓለማቀፍ የህግ ባለሙያነት ያገለገሉትና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ ፖለቲካዊና የጸጥታ ጉዳዮችን በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ባይሳ ዋቅዎያ፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከታጣቂዎቹ ጋር አደረኩ ያለውን የሰላም ስምምነት ይዘት በጥልቀት ማየቱ አስፈላጊ ቢሆንም በደፈናው ወደ ሰላም የሚመራ የትኛውም ስምምነት በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ነው ይላሉ፡፡ “እንደ ባለሙያ እንደዚህ አይነት ስምምነቶችን የማየው ድርድር ነበረ፤ በድርድሩ ውስጥ የሆነ ቡድን ሆነ ነገር ሰጥቶ የሆነ ነገር ይቀበላል፡፡ ታጣቂዎቹ ስገቡ ከነመሳሪያቸው መታየታቸውም የውሉ አካል መሆኑ ነው የሚሳየው፡፡ በየቦታው ተኩስ ተሰማ የተባለውም ባይሆን ጥሩ ነበር፡፡ ግን ደግሞ የደስታ መግለጫ ሊሆን እንጂ የአመጽ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ህዝቡም ተደናግጦ ይሆናል እንጂ እኔ አላስገረመኝም፡፡ ግን አንዳንድ ሰዎች እንዴት ከነትጥቃቸው ገቡ ብለው ይጠይቃሉ፤ ነገሩን የሚወስነው ስምምነታቸው ነው፡፡ በርግጥ ያን የሚፈቅድ የስምምነት አንቀጽ ባይኖር ኖሮ እንዲህ አይነት ነገር አንመለከትም ነበር” ነው ያሉት፡፡ ስለመንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም ስምምነት የህዝብ አስተያየት
የሚናፈቀው ዘላቂ እልባት
የዓለማቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ባይሳ እንዳሉት የተወሰኑ አካላት ከነጠመንጃቸው አዲስ አበባ ገብተው ከመንግስት ጋር ተስማሙ ማለት ግን ከመቅጽበት መፍትሄ ያመጣል ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ተደረገ የተባለውን የሰላም ስምምነት ወዲያውኑ የተቃወሙ የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች በመኖራቸው ነው፡፡ እዲህ ያለ ነገር በትጥቅ ትግል ውስጥ የተለመደ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ “ሁል ጊዜም አንደኛው ወገን ከመንግስት ጋር ተስማምቶ ሲገባ ሌላኛው ቡድን ቀርቷል፡፡ ቀደም ሲል ጃል መሮም በዳሬሰላም ከመንግስት ጋር ተስማምቶ ቢሆን ኖሮ በተመሳሳይ ሁኔታ በጫካ የሚቀር አይጠፋምና አሁን በተደረሰው ስምምነት የ100ም የሁን አንድ ሺህ መሳሪያ አፈሙዝ መዘጋት በአዎንታዊ የሚታይ ነው” ብለውታል፡፡
አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የክልሉ ነዋዎች በፊናቸው ሰሞነኛውን የታጣቂዎች እና የመንግስት የሰላም ስምምነትና ያንን ተከትሎ የመጡቱን የሰላም ምልክቶች በተስፋም በስጋትም ነው የሚመለከቱት፡፡ ከምእራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ እና ጮቢ ወረዳ አስተያየታቸው የሰጡን ነዋሪዎችም ይህንኑን አመላክተዋል፡፡ “ብሆን ብሆን ሁሉም በጋራ ብገሙ መልካም ነው፡፡ እኔ እንደግለሰብም ሆነ ማህበረሰቡ የሚለውም ሁሉም ለምን አልገቡም የሚል ጥያቄ በማቅረቡ የሚሰጉ እንዳሉ እነዚህም ስታገሉ ነበርና መግባታቸው መልካም ነው የሚሉ አሉ” ሲሉ ተስፋና ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ አስተያየታቸውን የቀጠሉ የጮቢ ወረዳ ነዋሪም “ስጋት አለ፡፡ አሁን የገቡት ታጣቂዎች ምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ሰሜን ሸዋ አከባቢ እና ወለጋ በተለያዩ ስፍራዎች የሚንቀሳቀሱትም ተወያይተው እስካልገቡ ድረስ ያው ጥርጣሬ አለን” ብለዋል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ የተፈጠሩ ውዝግቦች
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሰላም ስምምነቱን ከአማጺዎቹ ጋር ማኖሩን ተከትሎ ስምምነቱን የገለጸበት መንገድ ሙገሳም ሆነ ትችት አስከትሏል፡፡ በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት ስምምነቱን ከኦነግ-ኦነሰ ጋር አደረኩ ማለቱን አጣጥሎ በመንቀፍ መግለጫ ያወጣውም ወዲያው ነበር፡፡ የዓለማቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ባይሳ ዋቅዎያ ግን ይህ ፖለቲካ በመሆኑ ሁለቱንም አካላት መተቸት አይቻልም ባይ ናቸው፡፡ “መንግስት በዚህ በኩል አንድ ሺህ ታጣቂዎችን ወደ ሰላም ማምጣቱ ጥሩ ነው፡፡ የተቀሩተም እነዚህ ሰዎች ክደው መንግስት ጋ ገቡ ማለታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ ፖለቲካ ስለሆነ ሁሉም እንደሚስማማው ይተረጉመዋል፡፡ የስምምነቱን ዝርዝር ባናውቅም የገቡት አንድ ሺህ ሰዎች የሚገደሉትን ሰዎች የሚቀንስ እንጂ
ዘላቂ ሰላም ያሰፍናል የሚስብል እንዳልሆነ ግን ሊሰመርበት የሚገባው ነው” ሲሉም አስተያየታቸው ሰጥተዋል፡፡የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ጥሪ፣ ተስፋና ስጋቱ
ከሰሞኑ ታጣቂዎቹ በኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሰራዊቱ መለያ ልብስ መታየታቸውን ተከትሎ ስለተፈጠረውም ግራ መጋባትና አጠቃላይ የስምምነቱ አውድ ከመንግስት ባለስልጣናት ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ዛሬም አልተሳካም፡፡ አቶ ባይሳ በዚህም ላይ ባከሉት አስተያየት ግን፤ “የለመሱት ልብስ የሚሳየው ምናልባትም እነዚህ ሰዎች በስምምነቱ በአገር መከላከያ ታቅፈዋል ማለት ነውና ይህ መልካም ነው” ብለው ሂደቱ ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ “ሂደቱ በመጀመሪያ ደረጃ ሁላቸውም ሰላማዊ መሆን አለባቸው፡፡ ካምፕ ገብተው ጊዜ ወስደው እነዚህ ሰዎች መከላከያ ውስጥ መክተት ካስፈለገም ሂደት ውስጥ ማለፍ ነበረበት” በማለት ውጤቱን በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ ለማየት ግን ጊዜ ወስዶ ማየት እንደሚስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር