የኦነሠና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስምምነት፤ የታዬ ደንደኣ መፈታት፤ የኤችአይቪ መድኃኒት
ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2017በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መካከል የሰላም ስምምነት ተደረሰ ከተባለ ጥቂት ቀናት ተቆጠሩ ። የቀድሞው የሰላም ሚንሥቴር አቶ ታዬ ደንደአ ደግሞ ትናንት ከእስር ተለቀቁ ተብሎ ወዲያው ሌላ ዜና ተሰምቷል ። ታዬ ትናንት «የፊት ጭምብል ባደረጉ እና በታጠቁ ሰዎች» ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው በነጋታው ዛሬ ደግሞ መፈታታቸው ተዘግቧል ። አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ስኬታማ በሆነ መንገድ መሞከሩን ተመራማሪዎች ይፋ ማድረጋቸው ከሰሞኑ ተበሥሯል ። የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት ትኩረት ናቸው ።
ኦነሰ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስምምነት
በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መካከል የሰላም ስምምነት ተደረገ መባሉ በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ዘንድ የተለዩ ስሜቶች እንዲንጸባረቁ አድርጓል ። ስምምነቱ መደረሱን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ያሳወቀው እሁድ ዕለት ነበር ። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) በበኩሉ በይፋዊ መግለጫው፦ «መንግስት ከጦሩ የወጡ ግለሰቦች ጋር ያደረገውን ስምምነት ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ስምምነት እንዳደረገ አድርጎ ማቅረቡ አግባብነት የለውም» ብሏል ።
«ከግለሰብ ጋር ስምምነት» ብለውታል አኬል ዳማ ሀገሬ በፌስቡክ አጠር ያለ ጽሑፋቸው ። ብሥራት የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ለሰላም ጊዜው አሁን ነው» ሲሉ በእንግሊዝኛ ጽፈዋል ። አይማን የተባሉ ሌላ ግለሰብ «በስተመጨረሻ ድንቅ ዜና ለኦሮሚያ» ብለዋል በእንግሊዝኛ ጽሑፋቸው ። ሲሣይ ኤም አሞራው ደግሞ፦ «የኦነሰ የጥቃት ዒላማ እና የመከላከያ የድሮን ድብደባ፤ የገፍ እስር ብሎም ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ ፍትህ በሌለበት ኹኔታ አማራን ይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ አድርጎታል» ሲሉ ጽፈዋል ።
ዐሳዬ ደርብ በፌስ ቡክ ጽሑፋቸው፦ «ያን ሁሉ ጭፍጨፋ የፈጸመውና ሸኔ እየተባለ ሲወገዝ የነበረው አሸባሪ ሥሙ ተቀይሮለት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተባለ እኮ» ሲሉ አስፍረዋል ። «እንዳውም አሁን ጥሩ ሆነ ። ምክንያቱም ቀድመውም አልተጣሉም» ይላሉ ነጋ ተመስገን በዛው በፌስቡክ ። የሪያድ ማኅበረሰብ ድምጽ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «በፈለገ መልኩ ቢሆንም ዋናው ሰላም መስፈኑ ነው» ብለዋል ። ዮኒ የሱ የስቡክ ስም ነው፤ ስምምነቱን፦ «የብልጥግና የጊዜ መግዣ ስምምነት ይባላል» ብለውታል ።
የአቶ ታዬ ደንደአ መፈታት
የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ዛሬ ኅዳር 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ከእስር ተለቅቀዉ ከቤተሰባቸዉ ጋር መቀላቀላቸው ተገልጧል ። አቶ ታዬ ትናንት አመሻሹን ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተለቅቀው ቤተሰቦቻቸውን ሳያገኙ ከማረሚያ ቤቱ በራፍ በፀጥታ ኃይሎች ተወስደው እንደነበር ተዘግቧል ። አቶ ታዬ ዛሬ እኩለ ቀን ደግሞ ሜክሲኮ ከሚገኘው የወንጀል ምርመራ ማዕከል ተለቅቀው ቤታቸው መድረሳቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል ። አቶ ታዬ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድን በይፋ እና በብርቱ ከተቹ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ነበር ለእስር የተዳረጉት ።
ጽጌሬዳ መራዊ በፌስቡክ ገጻቸው፦ «መከራዉ የበዛ ሰዉ አቶ ታዬ እንኳን ለቤትህ አበቃህ» ብለዋል ። ትእግስት ኃይለማሪያም በበኩላቸው፦ «እሰይ እንኳን ለቤትህ አበቃህ» የሚል መልእክት አስፍረዋል ። «ንፁሐን የአማራ ፖለቲከኞች ይፈቱ» ያሉት ደግሞ ጌትነት እንዳለው ናቸው ።
አቶ ታዬ ትናንት «የፊት ጭምብል ባደረጉ እና በታጠቁ ሰዎች» ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው እንደተሰማ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል ። «እዚያው ቢቆይ ይሻለው ነበር፤ ፈጣሪ ይጠብቀው ። ፓርላማውና ኢሰመጉ ስለዚህ ምን ይሉን ይሆን?» ሲሉ ጠይቀዋል ናስር ሞሐመድ በፌስቡክ ። ያብሥራ አሰግድ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «አይ ብልፅግና» ብለዋል በአጭሩ ። «ያዘው ልቀቀው» ሲሉ በአጭሩ የጻፉት መርሻ ተሰማ ናቸው ። «ጥበቃ እየተደረገላቸው ይሆናል» ያሉት ደግሞ መስፍን ማርክ ናቸው በፌስቡክ ። አቶ ታዬ ከእስር ተለቀቁ፤ ጭምብል ባደረጉ ሰዎች ተወሰዱ እንዲሁም እቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር ተቀላቀሉ የሚሉት መረጃዎች የተቀያየሩት ሃያ አራት ሰአታት ባልሞሉ ጊዜያት ውስጥ ነው ። ዛሬ ቤታቸው ደርሰው ከቤተሰብ ጋር መቀላቀላቸው መነገሩን በተመለከተ በርካቶች ፦ «እንኳን ለቤትዎ አበቃዎ» ብለዋል ።
የኤችአይቪ/ኤድስ ክትባት ግኝት
ከ40 ዓመታት በፊት በዓለም ላይ ለተከሰተው የኤችአይቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ህክምና እና የመከላከያ መድኃኒት ለማግኘት ዓለም ሌት ተቀን ባትሏል ። ጊሊድ የተባለው የአሜሪካ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ አዲስ ውጤታማ የኤች አይ ቪ መድኃኒት ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል ።
ሌናካፓቪር፤ የተባለው አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ ክትባት ስኬታማ በሆነ መንገድ መሞከሩም ተገልጧል ። ተስፋ ሰጪ የተባለው ይህ መድኃኒት በአውሮፓ ኅብረት ጭምር የኤችአይቪ ህሙማንን ለማከም ፈቃድ አግኝቷል ። በመርፌ መልክ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰጠው ይህ አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት መቶ በመቶ ውጤታማ ነው የመባሉ ዜና የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ዐቢይ መነጋገሪያ ጉዳይ ሁኗል ።
የመድኃኒቱ ወይንም ክትባቱ ተገኘ መባል በጥንቃቄ ረገድ መዘናጋት እንዳይፈጥር ባለሞያዎች መክረዋል ። ሊዲያ አማን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ መዘናጋት መኖሩን የሚያመላክተው ጽሑፋቸው፦ «በሽታውን ከመርሳቴ የተነሳ 'ኤድስ' የሚለውን 'አዲስ' ብዬ ነው ያነበብኩት » በሚል ይነበባል ። «መልካም ዜና መስማት ለተጎጂዎች የምስራች ነው ።» መልእክቱ የሰለሞን ገብረ እግዚአብሔር ነው ።
«በድህነት አዘቅጥ ውስጥ ለምትገኘው ኢትዮጵያ መዲኃኒቱ በመርፌ መሰጠቱ አጣራጣሪ ነው» ብለዋል ዮማን ዮኒ ። ገብረ እግዚአብሔር ትኩ በበኩላቸው፦ «ዜና ሁኖ እንዳይቀር» ብለዋል ። በአጭር ጽሑፋቸው «ማዘናጊያ» ያሉት የማትበገር ኢትዮጵያ በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው ። የኤች አይ ቪ/ኤድስን በመቀነስ ረገድ ባለፉት ዐሥራ አራት ዓመታት እመርታ ካሳዩ ሃገራት ኢትዮጵያም እንደምትገኝበት ይነገራል ። ኤች አይ ቪ/ኤድስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሽቆለቆለ ነው ቢባልም ዛሬም መዘናጋት ሳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ባለሞያዎች ይመክራሉ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ