የኬንያ ጦር ዘመቻ፤አሸባብና ሶማሊያ
ሰኞ፣ ጥቅምት 27 200407 11 11
የሶማሊያ ገዢዎች ሰሜናዊ ግዛትዋን ለመቆጣጠር ሲዝቱ ሲፎክሩባት አልተጋፈጠችም።ትዕግስቷ ላንዳዶች-የፈሪነቷ ምልክት ቢመስልም፥ለአስተዋዮች የብልሕነቷ አብነት ነበር።ኬንያ።መላ ጎረቤቶችዋ በርስ በርስ፣በድንበር፣በተልዕኮ ጦርነት ሲተላለቁ፣ከዩናይትድ ስቴትስ-እስከ ፓኪስታን፣ እስከ ባንግላዴሽ የታደመዉ ጦር አፍንጫዋ ስር ገድሎ ሲፎክር፣ ተገድሎ ሲሸሽ በቅርብ ከመታዘብ ባለፍ እጇን አልዶለችም ነበር።ዛሬ ግን የምስራቅ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ቀንዲል፣የሰላም ደሴት ከእልቂት ፍጅቱ ማሳ ተመሰገች።አሸባብን ለማጥፋት ሶማሊያ ዘመተች።ዘመቻዉ መነሻችን፣ የሶማሊያ ዳራ ማጣቀሻ፣ የአሸባብ ማንነትት መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
የመላዉ ዓለም ፖለቲከኛ ዲፕሎማት ሥለ መላዉ ዓለም ሕዝብ ካንገቱም ሆነ ካንጀቱ የሚለዉን፣ የመላዉ ዓለም የፖለቲካ አዋቂ ለየትኛዉም ሐገር ሠላምና መረጋጋት እንደሚጠቅም ጠዋት ማታ የሚናገረዉን፣ የመላዉ ዓለም ሕዝብ ለየራሱ የሚመኘዉን የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ በቀደም ደገሙት።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ።
የሶማሊያ ሕዝብ ችግር-ችጋር ሲገድል-ሲያነፍር ሲያሰድደዉ የዓለምን ምፅዋት፣ የጎረቤተቹን ድጋፍ ከለላ መጠየቁ-ባይጠይቅ እንኳን መመፅወት መረዳቱ ተገቢ፥ ለመፅዋቹ የሰብአዊ ደግነቱ ልክ መገለጫነቱ አያጠያይቅም።የሶማሊያዉ የርስ በርስ ጦርነት በጋመበት በ1992 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንዲሕ እንዳሁኑ ሶማሊያ የገባዉ ረሐብ ከሰወስት መቶ ሺሕ በላይ ሕዝብ ሲፈጅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለረሐብተኛዉ የሚላከዉን ርዳታ የሚጠብቅ ሠራዊት ለማዝመት ወስኗል።
በዉሳኔዉ መሠረት የሚዘምት ወራዊት ከየሐገራቱ እስኪዋጣ ድረስ ዩናይትድ ስቴትስ የራስዋን ጦር አስቀድማ አዝምታ ነበር።ዉሳኔ-ዘመቻዉ የየአስወሳኝ-አዝማቾቹን ጥቅም ከማስጠበቅ የፀዳ ነዉ ማለት በርግጥ ያሳስታል።ድብቅ ዓላማዉ ምንም ሆነ ምን ዉሳኔ-ዘመቻዉ ለሶማሊያ ሕዝብ ችግር ተገቢ ፈጣን መልስ ሰጪነቱን፣ ከአስወሳኝ-አዝማቾቹ ድብቅ ፍላጎት ይልቅ ደግ-ሩሕሩሕነታቸዉን ማስመስከሩ ቢያንስ ያኔ አንድ-ሁለት አላሰኘም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት UNOSOM -በሚል ምሕፃረ ቃል ለጠራዉ ዘመቻዉ ሠራዊት ለማዝመት ያሳለፈዉን ዉሳኔ፣ዩናይትድ ስቴትስ ዘመቻ ተስፋ መልስ ላለችዉ ተልዕኮ ጦርዋን ማዝመቷን-የሶማሊያ ተፋላሚ ሐይላት በሙሉ ደግፈዉት-ፈቅደዉም ነበር።
ይሁንና የዉጪዉን ጦር ዘመቻ ደገፉ ወይም ፈቀዱ የተባሉት፥- ዓሊ መሕዲ መሐመድ፣ መሐመድ ፋራሕ አይዲድ፣አብዱረሕማን አሕመድ ዓሊ ቱሬ፣ኮሎኔል አሕመድ ዑመር ጄስም ሆኑ ተከታዮቻቸዉ ርዕሠ-ከተማ መቅዲሾን አራት አምስት ሥፍራ ሰነጣጥቀዉ ሕዝባቸዉን በሚፈጁ-በሚያፋጁበት፣በዚያ ወቅት ቀርቶ በጋራ በቆሙበት ዘመን እንኳን የዉጪ ጦር-እንዲገባ እንዲወጣ ለመፍቀድ አንዳችም የሕዝብ ዉክልና አልነበራቸዉም።
የሶማሊያን ሕዝብ የሚያፋጁት ሐይላት ፍቃድ-ሰጪ ነሺነት ሲጠየቅበት፥ የሶማሊያን ረሐብተኛ የማዳን ሰናይ አለማዉ-መጉደፍ ጀመረ።ከጅምሩ የጎደፈዉ ዘመቻ አምባሳደር ዲና «ምትክ የማይገኝለት ያሉት» ሕዝብ በሆነ ደረጃ እንኳን ወኪሎችን እንዲሰይም ከመርዳት ይልቅ ወትሮም ሕዝብ እንደማይወክሉ እየታወቀ ፍቃድ ከተጠየቁት ሐይላት መካከል አንዱን ደግፈዉ ሌላዉን መዉጋታቸዉ ደግሞ የትልቁ በጎ አላማ አጭር ቅጭት።
የኬንያ ጦር የሶማሊያዉን አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን ለመምታት ባለፈዉ ጥቅምት መጀመሪያ ደቡብ ሶማሊያ መዝመቱ በተሰማ በሳምንቱ የሶማሊያ የሽግግር ፕሬዝዳት ሼኽ ሸሪፍ ሼኽ አሕመድ መንግሥታቸዉ ዘመቻዉን አለመፍቀዱን አስታዉቀዉ ነበር።የሸሪፍ መግለጫ ያናደዳቸዉ የኬንያ ምክትል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሪቻርድ ኦንዮንካ ሐቁን አፈጉት።
«ፕሬዝዳንት ሸሪፍ በዚሕ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናል።እኛ እንደምናየዉ እሳቸዉ ራሳቸዉ አሚሶም ባይኖር ኖሮ ሶማሊያ ዉስጥ ሊኖሩ አይችሉም ነበር።እኛ ደግሞ ምንም እንኳን ወታደሮች ባናዘምትም ከአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር ሆነን የምንደማዉ እኛ ነን።እራሳቸዉ ሞቃዶሾ መኖር እንዲችሉ ጦር እንዲዘምት ያደረግ ነዉ እኛ ነን።አሁን ሸሪፍ ሙሉ በሙሉ ተቀይረዉ ኬንያ ጦር ማዝመት አያስፈልጋትም ማለት አልነበረባቸዉም።እኛ እሳቸዉ ፈፅሞ ሊፈቱት ያልቻሉትን ችግራቸዉን ለመፍታት ነዉ-የምንጥረዉ።የአሸባብ አባል ካልሆኑ በስተቀር በኛና በሳቸዉ አቋም መካካል ተቃርኖ አይኖርም።»
በርግጥም የዩጋንዳና የብሩንዲ ጦር ባይኖር ኖሮ ሼክ ሸሪፍ ከቪላ ሞቃዲሾ ከአመታት በፊት በተባረሩ ነበር።ግን የሸሪፍ መንግሥት ሕልዉና በዉጪ ጦር ጥበቃ መቆሙ እርግጥ የመሆኑን ያክል፥ መንግሥቱ የሕልዉናዉን ጠባቂዎች ፍላጎት ከማስፈፀም ባለፍ በሶማሊያ ሕዝብ የተወከለ፣ የሶማሊያንና የሶማሌዎችን ጥቅም የሚያስከብር ነዉ የሚባልበት አመክኗዊ ምክንያት ሊቀርብ አይችልም።
ሸሪፍ የኬንያ ጦር ዘመቻን ያጠያየቁት እንደ ሰዉ፥ በጣሙን እንደማንኛዉም ሶማሌያዊ ስሜት ፈንቅሏቸዉ፥ ወይም እንደ ፖለቲከኛ መንግሥታቸዉ ዘመቻዉን በመፍቀዱ ከሞቃዲሾ ነዋሪዎች የሚገጥመዉን ተቃዉሞ ለማርገብ ዘዴ ብለዉት ሊሆን፥ ላይሆንም ይችላል።ሥልጣን-ክብራቸዉን ለዳጋ የሚያጋልጥ ትልቅ ሥሕተት መስራታቸዉን ለመረዳት ግን ጊዜ አልፈጀባቸዉም።ሸሪፍ ያሉትን ባሉ በዕለታት ልዩነት ጠቅይላይ ሚንስትራቸዉን ወደ ናይሮቢ ልከዉ ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ መሐመድ ዓሊ የኬንያዎችን ቁጣ ካረገቡ በሕዋላ እዚያዉ ናይሮቢ በሰጡት መግለጫ የዘመቻዉን የጋራነት አረጋግጠዉ የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ርዳታ ተማፀኑ።
ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሸሪፍን መንግሥት እንዳቆመ፣ በጦር ሐይል እንዳስጠበቀ ሁሉ የኬንያ ጦር ዘመቻን ለመደገፍ የሸሪፍን ይቅርታ፣ የጠቅላይ ሚንስትራቸዉን ጥሪ መጠበቅ አላስፈለገዉም ነበር። አብዛኛዉ ዓለም በአሸባሪነት የፈረጀዉን አሸባብን ለማጥፋት ኬንያ ጦር ማዝመቷን ከኢጋድ እስከ ዋሽንግተን፥ ከአዲስ አበባ-እስከ ፓሪስ ያሉ ማሕበራትና ሐገራት የደገፉት የሸሪፍ ግራ-አጋቢ መግለጫ ከሞቃዲሾ ከመሰማቱ ብዙ ቀድመዉ መሆኑ ደግሞ የቪላ መቃዲሾዉ መንግሥት ፋይዳን እስከየትነት መስካሪ ነዉ።
የሸሪፍ መንግሥት የሶማሊያ ሕዝብ ዉክልና እንደሌለዉ ሁሉ የኬንያ ጦር ዘመቻም የሶማሊያ ሕዝብ ድጋፍ አለዉ ሊባል አይችልም።
የዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጦር ለማዝመት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔ፣ የሶማሊያ ተፋላሚ ሐይላትን ፍቃድ እንጂ የሶማሊያ ሕዝብ ቀርቶ የጎሳ መሪዎችን ፍቃድ እንኳን መጠየቅ አላስፈለጋቸዉም ነበር።
የሶማሌዎችን ተስፋ ይመልሳል የተባለዉ ሰላሳ-ሰወስት ሺሕ ጦር ግን ሺዎችን ገድሎ፣ ሺዎችን አቁስሎ፣ ሰላሳ ወገኖቹን አስገድሎ፤ ሰማንያ አስቆስሎ ደም-እየጠጣ ደም የሚጠማዉን ምድር በደም አጨቅይቶ-ሌላ የደም ቋት በርግዶ ወደ መጣበት መሔድ ግድ ነበረበት።
በሁለት ሺሕ ስድስት የያኔዉን የሶማሊያ የእስላማዉ ፍርድ ቤቶች ሕብረት ሚሊሻን ለመዉጋት ኢትዮጵያ ጦር ስታዘምት፣ የዋሽንግተን፣ ብራስልሶችን ፍቃድ፣ የባይዶዎችን ይሁንታ እንጂ የሶማሌ ጎሳዎችን ትብብር መጠየቅ አላስፈለጋትም ነበር።ዘመቻዉን በሳምንታት እድሜ እንደሚጠናቀቅ የተነገረለት ጦር ግን የብዙ ኢትዮጵያዉያንን ደም-ከብዙ ሶማሌዎች ደም ቀይጦ በሁለተኛ አመቱ መመለስ ግድ ነበር የሆነበት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንደሚሉት ሶማሊያ ያዘመቱት ጦር የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረትን ደምስሶ፥ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፥ በሰላም ደሕንነቷ ላይ የተጋረጠዉን ሥጋት አስወግዶ ነበር-ሐገሩ የገባዉ።አምባሳደር ዲና በቀደም ደገሙት።
የኢትዮጵያ ጦር መንበሩን ባይደዋ አድርጎ የነበረዉን የኮሎኔል አብዱላሒ ዩስፍ አሕመድን የጦር አበጋዞች ስብስብ መንግሥት ከዉድቀት ማዳኑ በርግጥ አላነጋገረም።የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት የተሰኘዉን ቡድን መበታተኑም እርግጥ ነዉ።ሕብረቱ ሲበታተን የሶማሊያን ታጣቂ ወጣቶች ያሰለፈዉ ፅንፈኛ ተዋጊ ቡድን ጠንክሮ ለመዉጣቱ የኢትዮ̎ጵያ ጦር ዘመቻ አስተዋፅኦ አላደረገም ማለት ግን አይቻልም።
በ1990ዎቹ አዲስ አበባን፥ድሬዳዋና ጂጂጋን በቦምብ በማሸበሩ የሚወነጀለዉን አል-ኢቲሐድ አል-ኢስላሚያን የመሠረቱት ሼኽ ሐሰን ዳሒር አዌስ ፥«ሐረካት አል-ሸባብ አል-ሙጃሒዲን» የተሰኘዉን ተዋጊ ሐይል መመሥረቱ ብዙ አል-ከበዳቸዉም።ሐበር ጊዲር ከተሰኘዉ የሐዉያ ጎሳ የሚወለዱት አዌስ ከዘጠኙ የእስላማዊ ፍርድ ቤት ሕብረት ከፍተኛ መሪዎች አንዱ ሆነዉ ሲመረጡ ወይም ሲሾሙ፥ ለዚያ ቡድን መሪነት ከጎሳቸዉ ከሚወለደዉ ከወጣቱ ተዋጊ ከአደን ሐሺ ፋራሕ አይሮ የተሻለ ሰዉ አላገኙም።
አይሮን ሾሟቸዉ።የኢትዮጵያ ጦር የእስላማዊ ፍርድ ቤት ሚሊሺያን መፈረካከሱ አይሮ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ብዙም የማይታወቀዉን የወጣት ተዋጊዎች ቡድን ለማጠናከር ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረላቸዉ።አይሮ በሁለት ሺሕ ስምንት በዩናይትድ ስቴትስ አብራሪ አልባ አዉሮፕላን ሲገደሉ ሼሕ ሙክታር ሮቦዉ አቡ መንሱር የመሪነቱን ሥልጣን ያዙ።የአሸባብ የመሪነት ሥልጣንም ከአብዛሐዉ የሐዉያ ጎሳ እጅ ወጣ።
መንሱር የራሕንዌይን ጎሳ ተወላጅ ናቸዉ።ብዙ ግን አልቆየም።መንሱር ወደ ቡድኑ ምክትል መሪነትና ቃለ አቀባይነት ዝቅ ብለዉ የመሪነቱን ሼክ ሙክታር ዓሊ ዙቤር ተቆጣጠሩት።ዙቤር የሰሜን ኢሳቅ ጎሳ አባል ናችዉ።ዙቤርን በሁለት ሺሕ አስር የተኳቸዉ ሼክ ኢብራሒም አል-አፍቃኒም የኢሳቅ ጎሳ አባል ናቸዉ።
አይሮ ከተገደሉ በሕላ የአሸባብ መሪዎች በጎሳ፥ በለዘብተኛና በፅንፈኛ መርሐቸዉ፥ ከሌሎች አሸባሪ ቡድናት ጋር ባለቸዉ ግንኘነት፣ የዉጪ ነዉጠኞችን በመቀበል-አለ መቀበል ልዩነት ምክንያት እንደተፋተጉ ነዉ።የመሪዎቹ ሽኩቻ፥በተራዉ ተዋጊና በሚቆጣጠሩት አካባቢ ሕዝብ ላይ የሚደነግጉት ጥብቅ ትዕዛዝና የሚፈፅሙት ጠንካራ ቅጣት ቡድኑ እስከ ሁለት ሺሕ ስምንት ማብቂያ ድረስ የነበረዉን ጥንካሬ ሸርሽሮታል።
በዚሕ ላይ የሽግግር መንግሥቱ ጦር፥ የሽግግር መንግሥቱ ደጋፊ ሚሊሺያዎችና የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ያደረሱበት ጥቃት፥ የገቢ ምንጩ መመናመን ሶማሊያን ከመታዉ ድርቅ ጋር ተዳምሮ የሽምቅ ተዋጊ አቅሙን ያዳከመበት አል-ሽበብ ወደለየለት አሸባሪ ቡድንነት ለዉጦታል።
«አቋማችን በጣም ቀላል ነዉ።የድንበሮቻችንና የሐገራችን ደሕንነትን እስክናረጋግጥ ድረስ ሶማሊያ ዉስጥ እንቆያለን።»
በ1963 ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ወዲሕ አንድም ጦርነት ገጥማ የማታዉቀዉ ኬንያ ሐገርን መከላከል-«ሊንዳ ኒቺ» ባለችዉ ዘመቻዋ ወደ ሁለት ሺሕ የሚጠጋ እግረኛ ጦር አዝምታለች።ታንክ፥ ተዋጊ ጄትና ሔሊኮብተር የታጠቀዉ ጦር የአሸባብ ዋና የገቢ ምንጭ የተሰኘችዉ የኪስማዩ ወደብን መቆጣጠር ግቡ አድርጎ ጁባላንድ በተባለዉ የኬንያ አጎራባች ግዛት ከጦር እንቅስቃሴ እግድ ቀጣና ለመመስረት ነዉ ዓላማዉ።
የኬንያ ጦር ከግብ-ዓላማዉ ለመድረስ አስራ-አራሺሕ ከሚገመተዉ የአሸባብ ሚሊሺያ ጋር መዋጋት አለበት።ብዙዎች እንደሚያምኑት የኬንያ ጦር ወትሮም የተዳከመዉን የአሸባብን ሚሊሺያ ድል ማድረጉ አይገደዉም።ግን መቼና እንዴት ነዉ-ጥያቄዉ።የኬንያ ምክትል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እንደሚሉት ኬንያ ጦር ጠላቱን የሚመታበትን፥ ከሚሻዉ የሚደርስበትን ጊዜ ወሳኙ እራሱ የኬንያ ጦር ነዉ።
ያ ስልታዊ ምድር አረቦች፣ፋርሶች፣ግብፆች ነግደዉ ሲከብሩበት፣ከስረዉ-ተገድለዉ ሲሸሹባት፣ ሮሞች ገድለዉ-ሲያስገብሩባት፣ተገድለዉ ሲሸነፉበት፣ ቱርኮች ድል-አድገዉ ነግሰዉ-ሲያነግሱባት፣ድል ሆነዉ ሲገብሩባት፣ ኢትዮጵያዉያን ገድለዉ ሲፎክሩ-ተገድለዉ ሲያዝኑበት፣ ብሪታንያዎች፥ ጣሊያኖች፥ አሜሪካኖች ገድለዉ ሲገዙ፥ ተሸንፈዉ ሲባረሩበት ትዉልደ-ትዉልድ አልፏል።ዛሬ ተራዉ የኬንያዎች ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ