የኮሮናን ወረርሽኝ እንደ መልካም አጋጣሚ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 12 2013የኮሮና ተሕዋሲ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከሆነ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ወራት ናቸው የቀሩት።በሽታው ከእስያ ወደ ሌላው የዓለም ክፍል በፍጥነት ከተዛመተና ስርጭቱም ከሰፋ በኋላ ሃገራት ልዩ ልዩ የመከላከያ እርምጃዎችን ወስደው ሥርጭቱን ለመግታት ጥረዋል።ከእርምጃዎቹ መካከልም ትምሕርት ቤቶች መዘጋታቸው እንዲሁም ሥራም ከቤት እንዲሰራ መደረጉ ይጠቀሳሉ።በዚህ ወቅት በብዙ ሃገሮች ተማሪዎች በኢንተርኔት አማካይነት ትምህርታቸውን ከቤት እንዲከታተሉ ተደርጓል።ተመሳሳዩ እርምጃ በተወሰደበት በጀርመን ይህን አስጨናቂ ጊዜ ዐዕምሮን የሚይዝ ተጨማሪ ጠቃሚ ትምሕርት በመማር ያሳለፉም አሉ።
በኮሮና ምክንያት ተማሪዎች ቤት በዋሉበት አጋጣሚ፣በደቡብ ጀርመንዋ በኑርንበርግ ከተማ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጽራ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክርስቲያን፣የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኢንተርኔት ለልጆች የሃይማኖት ትምሕርት የፊደል ንባብና የአማርኛ ቋንቋ አስተምራለች።የቤተ ክርስቲያንዋ አስተዳዳሪ መላከ አርያም መሪጌታ ዳዊት ከፍያለው ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ጀርመን ተወልደው ያደጉት እነዚህ ልጆች በተለይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፊደል መቁጠራቸው፣አማርኛ መጻፍ፣ማንበብና መናገር መቻላቸው ቤተክርስቲያኗ ካካሄደቻቸው ሌሎች ተመሳሳይ መርሃ ግብሮች ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ቤተክርስቲያኗ በዚህ መርሃ ግብር ለተካፈሉት ኑርንበርግና እና ሽቱትጋርት ለሚገኙ ጀማሪ ተማሪዎች በየቀኑ የአንድ አንድ ሰዓት ትምህርት ስትሰጥ ቆይታለች።በሦስት ቡድን ተከፍለው በሳምንት ሰባት ቀን ለአንድ ሰዓት ትምሕርቱን የተከታተሉት እነዚሁ ከ5 እስከ 14 ዓመት እድሜ ያላቸው 58 ልጆች ትምህርታቸውን ጨርሰው በቅርቡ ተመርቀዋል።የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ ዲያቆን መታፈሪያ ወልደ ጻዲቅ ከመምህራኑ አንድ ነው።የቤተ ክርስቲያኗ የሰንበት ትምሕርት ቤት የህጻናት ክፍል ሃላፊም ነው። በኮቪድ ምክንያት ልጆች ቤት መቆየታቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ስላዘጋጁት የትምሕርት መርሃ ግብር አጀማመርና ሂደት ያስረዳል። አቶ ፍሬዘር አለማየሁ የትምህርቱን መርሃ ግብርና መማሪያ መጸሀፍም ያዘጋጀ የሰንበት ትምሕርት ቤቱ የህጻናት ክፍል አባል ነው።
የመማሪያ መጸሐፉና ልጆች እንዳይሰለቹ መምህራን የተጠቀሙባቸው ልዩ ልዩ የማስተማሪያ ዘዴዎች ለመርሃግብሩ መሰካት አስተዋጽኦ አድርጓል ይላል ፍሬዘር። ውጭ የተወለዱና ያደጉ ህጻናት የወላጆቻቸውን ቋንቋ ማወቃቸው ዘረፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው መሪጌታ ዳዊት ያስረዳሉ።እርሳቸው እንደሚሉት ቋንቋ ልጆች ማንነታቸውን እንዲያውቁ ይረዳቸዋል።13 ዓመቱ ኖሀ ፈቃዱ የትምሕርቱን መርሃ ግብር ተከታትለው በጥሩ ውጤት ከተመረቁት ተማሪዎች አንዱ ነው።ከኑርንበርግ ወጣ ብላ በምትገኘው በኤርላንገን ከተማ የሚኖረው ኖሀ በተቀላጠፈ አማርኛ ምን እንደተማረና የተማረበትንም ምክንያት ገልጾልኛል።
አፎምያ አዲስ ፀጋዬ ሌላዋ በመርሃግብሩ ተካፍላ የተመረቀች የ12 ዓመት ልጅ ናት።58 ልጆችን ያለማቋረጥ በየቀኑ ለ5 ወራት ዙም በተባለው የኢንተርኔት መገናኛ በማስተማር የተገኘው የዚህ ውጤት ምስጢር በስርዓት መመራት መሆኑን ዲያቆን መታፈሪያ ያስረዳል።
መሪጌታ ዳዊት እንደሚሉት በጀርመን ልጆች በኮሮና ቤት መዋላቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከተካሄደው ከዚህ መርሃግብር የኑርንበርግ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ልምድ ቀስማለች።አቶ ፍሬዘር በበኩሉ ከዚህ ልምድም ሌሎች ትምሕርት ሊወስዱ ይችላሉ ብሏል።ቤተ ክርስቲያኒቱም ወደፊት መሰል አጋጣሚዎችን በመጠቀም ትምሕርቱን አስፋፍቶ የመቀጠል እቅድ አላት። በኑርንበርግ ጽርሃ አርያም ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ልጆች በኮቪድን ምክንያት ቤት መሆናቸውን በመልካም አጋጣሚነት በመጠቀም በተሰጠው የቋንቋና የሃይማኖት ትምሕርት ላይ ያተኮረው የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አብቋቷል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ