የውጪ ባንኮች ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ መፈቀድ እድል ወይስ ፈተና?
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 9 2017የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል። ምክር ቤቱ ትናንት በተቀመጠው መደበኛ ጉባኤው የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ አዋጆቹን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ዘገባና የውሳኔ ሀሳብ አቅርቦ በዝርዝር ጉዳዮቹ ላይ ከተመከረ በኋላ አዋጆቹ በአብዛኛው ድምጽ ፀድቀው ወደ ተግባር ተገብቷል።
በተለይም የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚፈቅደው የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የሚያደርገው የጸደቀው የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ በአዎንታዊውም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ በብዙ አነጋግሯል። ለመሆኑ ቁጥራቸው ከ30 የተሻገረው አብዛኛው የኢትዮጵያ የግል ባንኮች ከውጪ ልመጣ ነው እየተባለ የሚገኘውን ብርቱ ውድድር ለመቋቋም ዝግጁ ናቸው?
የአዋጁ ጭብጥ ጉዳይና ያስፈለገበት ምክንያት
አዲሱ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ በተለይም በአንቀጽ 9 እና 10 የውጪ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ባንክ እንዲከፍቱ፣ወኪል ቢሮ እንዲመሰርቱ አለያም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮችን በሼር መያዝ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ አዋጁ በተለይም በአንቀጽ 10 ስር የውጪ ዜጎች በባንኩ ዘርፍ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ መፈቀዱን በማስመልከት የውጪ ዜጋ ሆነው በባንኮቹ በሥራ አስፈጻሚነት አለያም በከፍተኛ ባለሙያነት ሲቀጠሩ በዓመታት በተወሰነው በኮንትራት መልክ ሊሆን እንደሚገባው በመደንገግ በእነዚህ ባንኮች ሊኖር ስለሚገባው የውጪ አገር ዜጋ ሠራተኞች ብዛትና ባንኮቹ ሊይዙት ስለሚገባው የድርሻ/ሼር/ መጠን ለመወሰን በብሔራዊ ባንክ በሚወጡ ቀጣይ መመሪያዎች እንደሚወሰኑ ያስረዳል።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ ለምክር ቤቱ ዘገባና የውሳኔ ሀሳብ ባቀረቡበት ወቅትም የአዲሱን አዋጅ አስፈላጊነት ተንትነዋል፡፡ “የባንክ ሥራ በአግባቡ ካልተመራ በፋይናንስ ስርዓቱና በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ያለመረጋጋት ሊያስከትል የሚችልበት በመሆኑና ከባንክ ሥራ እውቀት፣ ክህሎት፣ ልምድና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አኳያ የአገር ውስጥ ባንኮች ብዙ የሚቀራቸው ስለሆነ እስካሁን ሲያጋጥሙ የነበሩ በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲረዳና አገራችን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ማዕቀፍ ውስጥ በዋናነትም በባንክ ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል የሚረዳ ከመሆኑም በላይ የውጪ ባንኮች እና ኢንቨስተሮች በዘርፉ ተሰማርተው ለኢኮኖሚው ቀጣይ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል ሕግ መደንገጉ ወሳኝ በመሆኑ ይህ አዋጅ በዝርዝር ታይቶ አስፈላጊነቱ ታምኖበታል» ሲሉም ማሻሻያው ያስፈለገበትን ምክንያት ተንትነዋል።
የውጪ ባንኮችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚፈቅደው ሕግ ያስከተለው ስጋት
ትናንት አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲጸድቅ የውጪ ባንኮችን እና ኢንቨስተሮችን ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ የሚፈቅደው አዲሱ አዋጅ ላይ ጠንከር ያለ ጥያቄን ካነሱ የምክር ቤቱ አባላት መካከል አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ይጠቀሳሉ።
«የውጪ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ስገቡ አገልግሎቱን ከማሻሻል ተወዳዳሪነትን ከማላቅ አኳያ እንዲሁም የውጪ ካፒታል ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ የማድረግ ጥቅሙም የሚታወቅ ነው። ግን ምንድነው በተለይም ለግል ባንኮች በመንግሥት በኩል በቂ ድጋፍ ተደርጓል ብዬ አላስብም» በማለት ውሳኔውን አደገኛ ብለውታል። ዶ/ር ደሳለኝ ለዚህም ማሳያ ብለው ባቀረቡት አስተያየት፤ በቅርቡ የጸደቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያበደረውና ያልተመለሰው እዳ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር የተዘዋወረበትን አሰራር በማንሳት፤ ይህም መንግሥት ባንኩን ለማዳን ያደረገው ጥረት እንደሆነ አንስተዋል።
የውጪ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ቢገቡ የሚፈጥሩት የሥራ እድል እና የቴክኖሎጂ ሽግግሩ እንደበጎ እመርታ ሊነሳ የሚችል ነው በሚል ሃሳብ ያነሱት ሌላው የምክር ቤቱ አባልም «አሁን ግን ጊዜው ነው ወይ?» በማለት ጥያቄ አንስተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ዝግጁነት
ከምክር ቤቱ በተነሱት ጥያቄና ስጋቶች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የብሔራዊ ባንክ ገዢው አቶ ማሞ ምህረቱ የባንክ ዘርፉን ክፍት ማድረግ የብሔራዊ ባንኩን የሕግ ቁጥጥር አቅም የሚያላላ ተደርጎ መወሰድ የለበትም በማለት ሞግተዋል።
«ዘርፉን ከፍተን እንደውም ቁየጥጥር አቅማችንን እናጠናክራለን። መክፈት ሕግ ማላላት ማለት አይደለም። ያለው የቁጥጥር ስርዓት ተጠቅሞ የፋይናንስ ዘርፉን ተሳታፊዎች የአገር ውስጥም ይሁን የውጪውን የመቆጣጠር ሥራ ይሠራል» ነው ያሉት።
ዋና ገዢው አቶ ማሞ ምህረቱ የውጪ ባንኮች መጥተውእንደሁኔታው ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋ ተሻርከው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የብድር እና የውጪ ምንዛሪ ግኝት በማስፋት ምርታማነትን እንዲያነቃቁ ታስቦም ብለዋል። «አዋጁ ወጣው ተጨማሪ አሠራሮች በኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ እንዲመጣ ታስቦ ወጣ ነው» ያሉት ማሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮችም በውድድሩ እንዲበረቱ መታቀዱን እንዲ ፈርሳሉ የሚል እምነት አለመኖሩን አስገንዝበዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች ምልከታ
በዩናይትድ ኪንግደም በፋይናንስ ባለሙያነት የሚያገለግሉት የፋይናንስ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሃመድ የውጪ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገቡ የተከፈተው የፋይንንስ በር እንዲሁ የሚያስበረግግ አይሆንም የሚለውን አስተየታቸውን ነው ያጋሩን። ባለሙያው እንደሚሉት የኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርኣቱ ስከፈት ከተለያዩ ያደጉ አገራት ግዙፎቹ ባንኮች በእድሉ ልሳቡም እንደማይችሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል። «የኢትዮጵያ የባንክ ኢንደስትሪ ክፍት ስለተደረገ ብቻ የውጪ ባንኮች በአንዴ ዘው ብለው ላይገቡ ይችላሉ። አንድ አገር ስገቡ በራሳቸው የሚገመግሟቸው ነገሮች ልኖሩ ይችላሉ። ደግሞም በብዛትም ላይገቡ ይችላሉ። ትላልቆቹ የአውሮጳ ባንኮች ላይገቡ ይችላሉ። በእኔ ግምት የአፍሪካ ባንኮች ናቸው በዚህ ሊሳቡ የሚችሉት። ደግሞም ሲገቡም የእነሱ ትኩረት ልክ እንደ ሌሎች የእኛ ባንኮች ገጠር ድረስ ወርደው ቅርንጫፍ ከፍተው ሳይሆን ግዙፎቹ ተቋማትን መያዝ ላይ ብቻ ነው ልተኩሩ የሚችት» በማለት ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር ብዙም ፈታኝ የገበያ ሽሚያ ውስጥ ላይገቡ እንደማይችሉ አስረድተዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ ግን የውጪ ባንኮቹ ወደፊት በሚወጡት የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች ካልተገደቡ በአገር ውስጥ ባንኮች ላይ ሊያሳርፉ የሚችሉት ጫና ከገበያው እስከማስወጣት ሊደርስ እንደምችል ስጋት አላቸው።
«አቅማቸው ከበድ ስለሚል ያላቸውም የካፒታል የውጪ ምንዛሪ አቅምም ጠንከር ስለሚል እንደማንኛውም የአገር ውስጥ ባንኮች ሁሉም እድል የሚከፈትላቸው ከሆነ የተሻለ ቴክኒዎሎጂ ተጠቃሚ ስለሆኑ ምናልባት የተሻለ ደንበኞችን በመውሰድ የአገር ውስጥ ባንኮችን ሊያዳክሙ ይችላሉ» ብለዋል። አቶ አብዱልመናን መሃመድ ግን፤ «ብሔራዊ ባንክ ባለፉት 30 ዓመታት አቅሙን እያሳደገ መጥቷል። የውጪ ባንክ በሚመጣበት ሰዓት የመቆጣጠር አቅምህ ማደግ አለበት። አዋጁን ሳየው ብዙ ገደቦች አሉት የውጪ ባንኮችን በተመለከተ» በማለት በቁጥጥሩ መያዝ ይችላሉ ባይ ናቸው።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምህረቱ የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት ማድረግ ያስፈለገበትን ሲገልጹ፤ «እያደጉ የመጡ የኢትዮጵያ ባንኮችን የበለጠ ለማጎለበት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነትን ለማረጋገትና ከዓለም አቀፍ አሠራር ጋር የተጣጣመ የባንክ ቁጥጥር አሠራር እንዲሆን ማስቻል ነው» ይላሉ።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ