ደቡብ ሱዳን በስደተኞች ተጨናንቃለች
ደቡብ ሱዳን ፣ በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በተሰደዱ ሱዳናውያን መጨናነቋን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታወቀ።
ድርጅቱ በየቀኑ ከ5,000 በላይ ሱዳናውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚገቡ የገለጸ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሞሽን በበኩሉ በየቀኑ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እስከ 10,000 ይደርሳል ብሏል።
የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የደቡብ ሱዳን የአስቸኳይ ድጋፍ አስተባባሪ ኢማኑኤል ማንቶባዬ በአካባቢው የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ እጅግ አስከፊ እንደሆነ ገልጸዋል። «ደቡብ ሱዳን በስደተኞች ተጨናንቃለች» ያሉት አስተባባሪው ይህን ለማገዝ የሚያስችል በቂ ሰብአዊ ዕርዳታ እንደሌለ አክለዋል። በቅርቡ ከ100 በላይ ክፉኛ የተጎዱ ቁስለኞች ድንበር አቋርጠው ደቡብ ሱዳን ቢደርሱም አስፈላጊ የሕክምና ዕርዳታ ማድረግ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
ኢማኑኤል ማንቶባዬ በአካባቢው የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ «የማስታወስ ችሎታዮን ያጣሁ እስኪመስለኝ ግራ የሚያጋባ ነው» ሲሉ ገልጸውታል።
አብዱላሂ ሁመድ የተባለ ተፈናቃይ በበኩል በታጣቂዎች ቤታቸው ሲቃጠል የቤተሰቡ አባላት በተለያዩ አቅጣጫዎች መሸሻቸውን፤ እሱ ደግሞ በጥይት ቆስሎ ደቡብ ሱዳን መድረሱን ገልጿል። አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ሱዳን ለመመለስ ፍላጎት እንደሌለው በማከል።
ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን በደቡብ ሱዳን ላሉ ሱዳናውያን ስደተኞች ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ አስፈላጊውን የምግብና የሕክምና ዕርዳታ እንዲያደርግ ጥሪ ማድረጉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
በሞዛምቢክ በጣለው ወጀብ የተሞላበት ዝናብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 120 መድረሱን
በሞዛምቢክ በጣለው ከፍተኛ ወጀብ የተሞላበት ዝናብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 120 መድረሱን የሐገሪቱ የአደጋ መከላከል ባለስልጣን አስታወቀ። በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ ወደ 900 ገደማ ተጠግቷል። በአለፈው ሳምንት ሞዛምቢክን የመታው ወጀብ በርካታ የመሰረተ ልማቶችን ያወደመ ሲሆን የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች ቁጥርም ቀደም ሲል ከተነገረው እጅጉን ከፍ ያለ እንደሆነ ነው ባለስልጣናቱ የተናገሩት።
ወጀቡ ወደ 622,000 የሚሆኑ ነዋሪዎችን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ጉዳት አድርሶባቸዋል። ይህ በሰዓት 260 ኪሎሜትሮችን ይወነጨፍ የነበረው ወጀብ 140,000 የሚደርሱ ቤቶችን ማውደሙም ታውቋል። ይኸው ከባድ ወጀብ በማላዊም 13 ሰዎችን ለህልፈት ሲዳርግ ከ30 በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።
ሶሪያ የአሸባሪዎች ገነት መሆን የለባትም ስለመባሉ
ሶሪያ «የአሸባሪዎች ገነት መሆን የለባትም»ስትል ኢራን አሳሰበች። የሶሪያ ሉአላዊነትንና የግዛት አንድነት እንዲከበር እንደምትደግፍም አረጋግጣለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ኢስማኤል ባቓኢ ለጋዜጠኞች፤ «በሶሪያ የምንከተለው መሰረታዊ ዕምነት ግልጽ ነው፤ የሶሪያ የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት እንዲከበር፤ የሶሪያ ሕዝብ ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት መጻኢ ዕድሉን እራሱን እንዲወስን እንፈልጋለን» ብለዋል።
«ሶሪያ የአሸባሪዎች ገነት መሆን የለባትም» ያሉት ቃልአቀባዩ በውጤቱ የአካባቢውን ሐገራት የሚጎዳ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። እስከአሁን ከአዲሱ አስተዳደር ምንም ዓይነት ግኑኝነት እንደሌላቸው በማከል። ከዚህ ቀደም ቴህራን የወደቀውን የበሽር አልአሳድን መንግስት ድጋፍ ታደርግ እንደነበር ይታወሳል ።
በሌላ ዜና የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሶሪያ ጉብኝት አድርገዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አይማን ሳፋዲ ከአዲሱ አስተዳደር መገናኘታቸው ቢነገርም በምን ጉዳዮች እንደተነጋገሩ ግን የተሰጠ ዝርዝር ነገር የለም። የሳውዲ አረቢያ የልኡካን ቡድን፤ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልኡካን፤ እንዲሁም በሩስያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የልኡካን ቡድን ዛሬ ደማስቆ ገብተው ከአዲሱ አስተዳደር ጋር ተወያይተዋል ነው የተባለው።
ሳውድአረቢያ ቀደም ሲል በሽር አል አሳድን ለሚወጉ አማጽያን ድጋፍ ታደርግ የነበረ ቢሆንም ከአለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ጀምሮ ግን ከበሽር አልአሳድ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንደነበራት የዲፕሎማቲክ ምንጮች ያስረዳሉ ሲል የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።
በመኪና አደጋ 9 ሞቱ 13 ቆሰሉ
በኢራን ዛሬ ባጋጠመ የመኪና አደጋ ቢያንስ 9 ሰዎች ሲሞቱ 13 መቁሰላቸውን የሃገሪቱ የቀይ ጨረቃ ባለስልጣናት አስታወቁ። አደጋው የደረሰው በምዕራባዊ የሐገሪቱ ግዛት ዛሄዳን በተባለች ከተማ አቅራቢያ አንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ከነዳጅ ጫኝ ቦቴ ጋር በመጋጨቱ ነው ተብሏል። በኢራን እንዲህ አይነት አደጋ በቀናት ልዩነት ሲደርስ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በአለፈው ቅዳሜ አንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ መንገዱን ስቶ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ 10 ሰዎች መሞታቸውን ይታወሳል። ኢራን ደካማ የመንገድ ደህንነት እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ። በመሆኑም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከመጋቢት 2023 እስከ መጋቢት 2024 ባለው አንድ ዓመት ውስጥ ከ20,000 በላይ ሰዎች ሕይወት በመኪና አደጋ ተቀጥፏል ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በቲክቶክ የዛተ ግለሰብ ዘብጥያ ወረደ
የጀርመን ፖሊስ በቲክቶክ ገጹ በገና ገበያ ላይ ጥቃት እፈጽማለሁ የሚል ዛቻ በማሰራጨት ትናንት ያሰረውን ግለሰብ ዛሬ ለቆታል። ከሃምቡርግ በስተምዕራብ በምትገኘው የወደብ ከተማ ቤርመርሀፈን ከተማ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ በቲክቶክ ገጹ ባሰፈረው የዛቻ መልዕክት ነበር ዘብጥያ የወረደው። ሆኖም ማንነቱ ያልተገለጸው ይኽው የ67 ዓመቱ ሰው ስነ ልቦናዊ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ከእስር መለቀቁን ፖሊስ አስታውቋል። ፖሊስ ግለሰቡን እየመረመረ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
ባለፈው አርብ ምሽት ዜግነቱ ሳውዲ ዐረብያዊ መሆኑ የተነገረ አንድ ግለሰብ ከበርሊን በስተደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው በማግድቡርግ ከተማ የገና ገበያ ውስጥ የያዘውን መኪና በፍጥነት ሲነዳ ለሞቱ ወገኖቻቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ሐዘናቸውን አደጋው በደረሰበት ቦታ አካባቢ በሚገኝ ቤተክርስትያን አበባዎች እያኖሩ ይገኛሉ። ዛሬ ማምሻውንም አማራጭ ለጀርመን በእንግሊዘኛ ምህጻሩ AFD ፤ መጤ ጠል ፅንፈኛ እየተባለ የሚጠራው ፓርቲ የጠራውና ጥቃቱን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአለፈው ቅዳሜ የማግድቡርግ ከተማን ያጠቃው ግለሰብም በማሕበራዊ መገናኛ ገጾቹ ላይ የተለያዩ ዛቻዎች ሲያሰራጭ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ አስቀድሞ በቁጥጥር ሥር ባለማዋሉ ጥቃቱ ሊፈጸም መቻሉን የጀርመን የመገናኛ ብዙሃን እየወቀሱ ነው።
የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በማግድቡርግ የደረሰውን ጥቃት የጸጥታ አካላት አስቀድመው መከላከል አይችሉም ነበር ወይ? የሚለውን እንዲጣራ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ናንሲ ፌዘርና የስለላ ክፍል ሐላፊዎችም በጥቃቱ ላይ ለሐገሪቱ ምክርቤት ማብራሪያ እንዲሰጡ ለፊታችን ጥር መጀመሪያ ቀናት ቀነቀጠሮ መያዙንታውቋል።
ለሩስያ ተደርበው ይዋጉ ነበር የተባሉ ከ1,000 በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መሞታቸውን
ለሩስያ ተደርበው ይዋጉ ነበር የተባሉ ከ1,000 በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መሞታቸውን አልያም መቁሰላቸውን ደቡብ ኮሪያ አስታወቀች። ከስለላ ድርጅቴ አገኘሁት ብላ ደቡብ ኮሪያ ዛሬ ባሰራጨችው መረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰሜን ኮሪያውያን ወታደሮች በዩክሬይን ጦርነት ከሩስያ ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው።
የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት ባሰራጨው መግለጫ በታህሳስ ወር ብቻ 100 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በውግያ ተገድለዋል። በአጠቃላይ ደግሞ 1,100 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ሞተዋል አሊያም ቆስለዋል ነው የተባለው።
ደቡብ ኮሪያ አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች፣ የሚሳይል ማስወንጨፊያዎችና መድፎች ለሩስያ እንደምታቀርብ የገለጸው የስለላ ድርጅቱ፤ ተጨማሪ እግረኛ ወታደሮችን ወደ ሩስያ ለመላክ ዕቅድ እንዳላትም አትቷል።
ሰሜን ኮሪያና ሩስያ በአለፈው ሰኔ ወር የጋራ ወታደራዊ ድጋፍ ስምምነት መፈራረማቸውን ይታወሳል ሲል የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሩስያ በኩል እስከአሁን የተባለ ነገር የለም።
ክየቭ 47 የሩስያ ድሮኖች ጣልኩ አለች
ሩስያ የዩክሬን ዋና ከተማ ክየቭን ጨምሮ በዘጠኝ የዩክሬይን ግዛቶች በፈጸመችው መጠነ ሰፊ በተባለለት የድሮን ጥቃት አንድ ሰው ሲቆስል በስቪል ሕንጻዎች ላይ ውድመት መድረሱን ክዬቭ አስታወቀች። ለጥቃቱ ከተሰማሩት ድሮኖች 47ቱን መትታ መጣሏንም አክላለች።
የዩክሬይን የአየር ኃይል ዛሬ በቴሌግራም ገጹ ባሰራጨው መግለጫ ሩስያ በዘጠኝ የዩክሬይን ዞኖች 72 ድሮኖችን በማሰማራት ድብደባ ፈጽማለች ብሏል። በጥቃቱ አንድ ሰው ሲቆስል በስቪል መኖሪያ ቤቶችና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይም ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ለጥቃቱ ከተሰማሩት ድሮኖች 47ቱን መትቶ መጣሉን የገለጸው የአየር ኃይሉ ሌሎች 25 ድሮኖች ደግሞ ዒላማቸውን ሳይመቱ ተኮላሽተዋል ብሏል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ሂሩት መለሰ