1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 26 2015

በመጭው ነሀሴ በደቡብ አፍሪቃ በሚካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው ፕሬዚዳንት ፑቲን ይገኛሉ መባሉ እያከራከረ ነው። እሳቸው በጉባኤው ከተገኙ ደቡብ አፍሪቃ አሳልፋ የመስጠት ግዴታ አለባት። ያንን ማድረግ ግን አትፈልግም። እናም የዲፕሎማሲውን አጣብቂኝ ለማለፍ አማራጮችን እየፈለገች ነው ።

https://p.dw.com/p/4S9nR
BRICS Treffen in Brasilien/Vladimir Putin und Cyril Ramaphosa
ምስል Mikhail Metzel/ITAR-TASS/IMAGO

ትኩረት በአፍሪቃ 03.06.2023


በመጭው ነሀሴ በደቡብ አፍሪቃ በሚካሄደው የብሪክስ ጉባኤ የሩሲያው ፕሬዚዳንት  ብላድሚር ፑቲን ይገኛሉ መባሉ  እያከራከረ መሆኑ፣ በቻድ የሚገኙ የሱዳን የስደተኞች ቀውስ እንዲሁም በደቡብ አፍሪቃ የዚምባብዌ ስደተኞች የገቡበት አጣብቂኝ የዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት የዳሰሳቸው ጉዳዮች ናቸው። 
ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ያለፈው መጋቢት የእስር ማዘዣ አውጥቷል። ፑቲን በነሀሴ ወር  በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ  አባል በሆኑበት የBRICS ጉባኤ ላይ ከተገኙ ሀገሪቱ በቁጥጥር ስር እንድታውላቸው ይጠበቃል።  ነገር ግን ሀሳቡ በደቡብ አፍሪቃ ዘንድ በምንም አይነት ሁኔታ ተቀበይነት አላገኘም።
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በመጭው ነሀሴ  ጆሃንስበርግ ሊካሄድ በተዘጋጀው የ BRICS ጉባኤ ላይ እንዲገኙ መጋበዛቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል።
የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) በሩሲያ በተያዙ ዩክሬን ግዛቶች ህጻናትን በግዳጅ በማፈናቀል ፑቲንን ከከሰሰ ወዲህ የእሳቸው በጉባኤው መገኘት እያከራከረ ነው።
ደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መሰረታዊ ስምምነት የሆነውን የሮም ስምምነት የፈረመች ሀገር በመሆኗ፤ደግሞ ፑቲን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከገቡ በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ዘሄግ እንድትልክ በስምምነቱ ትገደዳለች።
 የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ መንግስት ግን የዲፕሎማሲውን  እሳት ለማብረድ  ሁሉንም አማራጮች በመሞከር ላይ ነው። 
ከፍተኛ የፖለቲካ ተንታኟ ዚያንዳ ስቱርማን  ሁኔታው  ለደቡብ አፍሪቃ  ውስብስብ ነው ይላሉ።
«በደቡብ አፍሪቃ ቦታ ላይ ያለ ማንኛውም ሀገር እጅግ በጣም አስቸጋሪ ምርጫ ይገጥመዋል፣ ታውቃላችሁ፣ የኒውክሌር ሀይልን  የታጠቁ ፕሬዝዳንትን ማሰር  የልጆች ጨዋታ አይደለም።ታውቃለህ፤ በጣም በጣም ውስብስብ የፖለቲካ ውሳኔ ነው።ከሀገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ ህግ አንዲሁም ከማንኛውም የህግ ግዴታዎች በላይ ነው።» 
ደቡብ አፍሪካ  የሮም ስምምነትን ሳትጥስ ፑቲንን ላለማሰር  የሚያስችል የህግ ክፍተት እንደምትፈልግም አመልክታለች።
ተንታኞች እንደሚሉት  ደቡብ አፍሪካ  የስምምነቱን አንቀጽ 98 ተጠቅማ ሩሲያ የፑቲንን ያለመከሰስ መብት እስካላነሳች ድረስ  ማሰር አንችልም ስትል ለመከራከር ትፈልጋለች። ሆኖም፣ አለም አቀፍ የህግ ባለሙያ አንጄላ ሙዱኩቲ ያ  አይሰራም ብለው ያምናሉ።
«በጣም፣ በጣም የተወሳሰበ እና ረጅም ውይይት የሚጠይቅ ነው። ጠበቆች በራሳቸው ዙሪያ  የሚሽከረከሩበት ነው። ነገር ግን ቀላሉ መልስ አንቀጽ 98 አንድ ሰው እንዲታሰር ያለመከሰስ መብቱ ሊታለፍ እንደሚገባ ይደነግጋል»
ያለፈው ሃሙስ  በተጀመረው የBRICS የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሁለት ቀናት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓንዶር በነሀሴው የመሪዎች ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድም አሳስበዋል።
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ የመገናኛ ብዙሃን እና ተንታኞች የራማፎሳ መንግስት ጉባኤውን ወደ ሌላ BRICS ሀገር ለማዘዋወር እያሰበ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከአምስቱ የBRICS አባላል ሀገራት  መካከል የሮምን ስምምነት ፈራሚ የፈረሙት ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ ብቻ ሲሆኑ ቻይና፣ህንድ እና ሩሲያ ግን አልፈረሙም።የሮይተርስ የዜና ወኪል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የደቡብ አፍሪካን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ጠቅሶ እንደዘገበው ከዲፕሎማሲው ውዥንብር ውስጥ አንዱ መፍትሄ ያለፈውን አመት የ BRICS ሊቀመንበር ቻይናን ጉባኤውን እንድታዘጋጅ መጠየቅ ነው።
ደቡብ አፍሪቃ  ፑቲን በቁጥጥር ስር ላለማዋል ሌላው አማራጯ ባለፉት ሶስት ዓመታት በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት እንደተካሄደው  ስብሰባውን በበይነመረብ ማድረግ ነው። የዲሞክራሲያዊ አሊያንስ መሪ የሆነው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል ግሊኒስ ብራይተንባች በዚህ ሳምንት ለDW  እንደተናገሩት "መንግሥታችን የሚያደርገው ግልፅ ነገር ግብዣውን ማንሳት ነው" ብለዋል።
ነገር ግን በፕሪቶሪያ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዲርክ ኮትዜ ያን ያህል ቀላል አይደለም ይላሉ። ምክንያቱም ልክ እንደ ሀገራት ጉብኝት  የሁለትዮሽ ግንኙነት አይደለም።
«የBRICS ጉባኤ የሁለትዮሽ አይደለም። የፕሬዚዳንት ፑቲን የደቡብ አፍሪካ የተናጠል ጉብኝትም አይደለም። የቡድኑ ተለዋጭ ሊቀመንበር ሆና እየሰራች ያለችውው ደቡብ አፍሪካ ነች። ስለዚህ ጉባኤው የብሪክስ ጉዳይ ነው። በደቡብ አፍሪካ የሚካሄድ የደቡብ አፍሪካ ዝግጅት አይደለም፣ በመሆኑም የቡድኑ አባል ሀገራት ፕሬዚዳንት ፑቲንን አይጋብዙ እንደሁ ወይም የዚህን ጉባኤ ቅርፅ ይቀይሩ እንደሁ በአንድ ላይ መወሰን አለባቸው።»
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ በበኩላቸው ጉባኤው በደቡብ አፍሪካ ይካሄዳል ተብሎ የማይታሰብ ነው ብለዋል ። በህጋዊ ግዴታችን ምክንያት ፕሬዝዳንት ፑቲንን ማሰር አለብን ፣ ግን ያንን ማድረግ አንችልም ።በማለት  ጆሃንስበርግ ውስጥ ለአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ያለፈው ወር መጨረሻ ገልፀዋል።
ደቡብ አፍሪካ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል ይፈለጉ የነበሩትን የሱዳኑን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽርን አሳልፋ ባለመስጠቷ  ለረዥም ጊዜ ስትወቅስ ቆይታለች። በዚህ የተነሳ የፑቲን የእስር ማዘዣ  በገዥው የአፍሪቃ ኮንግረንስ ፓርቲ ውስጥም /ኤኤንሲ/ በሀገሪቱን የፍርድ ቤቱ አባልነት ላይ  እንደገና ክርክር አስነስቷል።
ያም ሆኖ ተንታኞች እንደሚሉት የፑቲንን እስር ለማስቀረት ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አባልነት  መውጣት ከደቡብ አፍሪቃ ከምርጫዎች መካከል አይደለም።
አንጄላ ሙዱኩቲ፣ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ጠበቃ፣ ደቡብ አፍሪካ ለምን ከፍርድ ቤቱ አባልነት  መውጣት እንደማትችል ያብራራሉ።
«ይህ በጣም ቀላል ነው. ምክንያቱም ለፑቲን የእስር ማዘዣ በወጣበት ወቅት ደቡብ አፍሪካ የሮም ስምምነት ፈራሚ የነበረች እና አሁንም ያለች ሀገር ነች። ስለዚህ ጉዳዩ ይህ እስከሆነ ድረስ ወደ ኋላ ተመልሰው ያንን መቀልበስ አይችሉም።» 

Südafrika Treffen der BRICS-Außenminister in Kapstadt
ምስል Foreign Ministry Press Service/ITAR-TASS/IMAGO
BRICS - Außenministertreffen
ምስል Russian Foreign Ministry/dpa/picture alliance

የሱዳን ስደተኞች ቀውስ በቻድ 

ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ሲያደርጉ እና ሲያፈርሱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሀገሪቱን ለቀው መሰደዳቸውን ቀጥለዋል። በተለይ ጥቃት በበዛበት የዳርፉር ክልል የሚኖሩ ሰዎች እርዳታ እና ተስፋም ፍለጋ ወደ ቻድ ይሰደዳሉ።
በሚያዝያ ወር በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የተጀመረውን ጦርነት በመሸሽ 60,000 የሚሆኑ ሱዳናውያን ስደተኞች ወደ ጎረቤት ቻድ ተሰደዋል።ግጭቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በተስፋፋው ግጭትከተሰደዱት መካከል ቦረኖን ክሃሚስ ሃሮን አንዷ ነች። ቦሮታ በምትባል መንደር ውስጥ በሚገኘው  የቻድ መጠለያ ጣቢያ ነው ያለችው።
 «አልጋዬን በጣም ጥሩውን ቤቴን ወደ ኋላ ትቼው ነው የመጣሁት።ጥሩ የሆኑትን ምንጣፎቼንም እንዲሁ።ሁሉንም ወደ ኋላ ተውኳቸው።ወደ ጫካ ከመሸሻችን በፊት ባለቤቴ ተገደለ።የተገደለው ማገዶ ሊፈልግ ሄዶ  ነው።»
ወደ 25,000 የሚጠጉ ሱዳናውያን በቅርቡ ቦሮታ ካምፕ ደርሰዋል በአብዛኛው ሴቶች እና ህፃናት  ናቸው።የእርዳታ ድርጅቶች። በጭነት መኪና እርዳታ ያጓጉዛሉ።ነገር ግን ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ አይደለም።ቦርኖን ክሃሚስ ሃሮን ችግሩን ስፋት እንዲህ ስትል ትገልፃለች።
«ልብስ የለኝም፣ የላስቲክ ኮዳም የለኝም፣ ሳሙና እና ምግብም የለኝም።አብስሎ ለመብላት በቀላሉ ጥራጥሬ እንኳ የለም። በዚህ ካምፕ ውስጥ፣ ለመዘዋወርም  ያለው ቦታ ትንሽ ነው።»
ዘይነባ ማርያም በመጠለያው የምትኖር ሌላዋ የሱዳን ስደተኛ ነች። ልጆችም አሏት ችግሩ እንደጠናባቸው ትገልፃለች።
«ውሃ እና ምግብ የለም.ልጆቹ ያለ ብርድ ልብስ በካርቶን ላይ ይተኛሉ። የሚረዳን ሆስፒታል የለም።በጣም ከባድ ነው። ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም።ሰዎች ሊረዱን ይገባል።»መጠለያ ጣቢያው  በሱዳን ይኖሩ የነበሩ ቻድያውያን መኖሪያ ነው።የተመደቡት እንደ ተመላሾች፣ እንጅ በይፋ የታወቁ  ስደተኞች አይደለም። .በዚህ ምክንያት   ለእነርሱ  ዕርዳታ ማድረስ  ረጅም ጊዜ እየወሰደ ነው።ባቺያካ ሲንጋሬ፣ የዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም  አስተባባሪ፣ ናቸው። እሳቸውም ለእርዳታ የሚሆን በቂ ምግብ የለም ይላሉ። 
«አሁን፣ በቂ የለንም። በቂ አቅርቦቶችን አግኝተን እነሱን እንዴት በጊዜ መርዳት እንድምንችል እንጨነቃለን።»

Tschad Geflüchtete Sudan Flüchtlingslager von Toumtouma
ምስል Blaise Dariustone/DW
Tschad Geflüchtete Sudan Flüchtlingslager von Toumtouma
ምስል Blaise Dariustone/DW

በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ዚምባቢያዊያን ስደተኞች አጣብቂኝ

ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ብዙ የዚምባብዌ ዜጎች አዲስ የመኖሪያ ፍቃድ ባለማግኘታቸው  የደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው እያለቀ ነው።ያም ሆኖ ብዙዎች ወደ ሀገራቸው  ተመልሰው   እንደገና አዲስ ኑሮ  መጀመር ከብዷቸዋል።በመሆኑም  በሀገሪቱ  የሚኖራቸውን ቆይታ ለማራዘም  በፍርድ ቤት ክርክር ጀምረዋል።ክርክሩ ካልተሳካ በሺዎች የሚቆጠሩ የዚምባብዌ ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው ለመውጣት ይገደዳሉ።
በእንግሊዥኛው ምህፃሩ (ZEP) የሚባለው የዚምባብዊያን ነፃ የመኖሪያ ፍቃድ የተቋረጠባቸው  ሰዎች ደቡብ አፍሪካን ለቀው የሚወጡበት ቀነ ገደብ በጎርጎሪያኑ ሰኔ 30  ሲሆን ሊጠናቀቅ ጥቂት ሳምንታት    ቀርተውታል።  በመሆኑም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ወደ 200,000 የሚጠጉ የዚምባብዌ ዜጎች በሀገሪቱ መቆየት ይችሉ  እንደሁ የፍርድ ቤቱን  ውሳኔ ለመስማት በጉጉት  በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
እነዚህ ስደተኞች በደቡብ አፍሪቃ ለመቆየት አማራጭ፣የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ቀነገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት እንዲያመለክቱ ይጠበቃል። ሆኖም ግን መስፈርቱን በቀላሉ የሚያሟሉት  ባለመሆኑ  ይህንን ፈቃድ ማግኘት ለእነሱ ቀላል አይደለም።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች እንዲሁም የዚምባብዌ ነዋሪዎችን የሚወክሉ እና በደቡብ አፍሪካ መብታቸውን ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ዚምባቢያውያን ለአማራጭ የመኖሪያ ፍቃድ ብቁ አለመሆናቸውን እየገለጹ ነው።በዚህ ሳቢያ አብዛኛዎቹ የዚምባብዌ ዜጎች  ማመልከት አይፈለጉም።መሆኑም በአሁኑ ወቅት አስቸጋሪ ፈተና ገጥሟቸዋል።ንብረታቸውን ሸጠው እና ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት አስወጥተው  ሀገሪቱን ለመልቀቅ መዘጋጀት? ወይስ ስለመኖሪያ ፈቃድ ማሰብ?
ዚም ኢምቦኮዶ የተባለው የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት ቪክቶር ማቱቱ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ  መዘግየት አጣብቂኝ ውስጥ ከቶናል ይላሉ።
« አሁን አጣብቂኝ ውስጥ  ገብተናል። ምን ታደርጋለህ? ለመልቀቅ ታመለክታለህ? ወይስ ፍርዱን ትጠባበቃለህ? በእርግጥ ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም። በጣም ከባድ ነው።»
የዜጎች ጥምረት ለለውጥ የሚባለው የዚምባብዌ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ትረስት ንድሎቩ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ መፍጠን አለበት ይላሉ።
«ብዙ ሰዎች ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። በተቻለ መጠን  በፍጥነት ፍርዱ እንዲሰጥ እመኛለሁ።ከዚያም እነዚህ ሰዎች እንዴት ማቀድ እንዳለባቸው አማራጮችን ማየት እንችላለን ።»
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የዚምባብዌ ማህበረሰብ ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት ንጋቡቶ ማብሄና ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው፤ አንዳንድ የደቡብ አፍሪካ ባንኮች የዚምባብዊያኑን የባንክ ሂሳብ እስከ ማገድ እንደሚሄዱ አስታውቀዋል።
«የተመለከትነው ነገር  ባንኮቹ ጊዚያዊ የመኖሪያ ያላቸው ፈቃዳቸውን እንዲያድሱ ደብዳቤ ፅፈዋላቸዋል።ይህንን ካላደረጉ ደግሞ ሒሳባቸው እንዳይነቀሳቀስ እንደሚያግዱት አሳውቀዋቸዋል።»
ጠበቃ ሲምባ ቺታንዶ ፍርድ ቤቱ የዚምባብዌያኑን ፍቃድ የሚያቋርጥ ከሆነ እሱን በመቃወም እስከ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ድረስ ለመከራከር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።
«እኛ ከተሳካልን በፍርዱ  ይግባኝ ጠየቁም አልጠየቁም  መንግስት ውሳኔ መስጠት አለበት። ግልጽ ነው ካልተሳካን እና ጊዚያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለያዙት የማይጠቅም ከሆነ በፍርዱ ላይ ይግባኝ እንደምንጠይቅ ዋስትና መስጠት እችላለሁ።»
በጎርጎሪያኑ 2009 ዓ/ም የደቡብ አፍሪካ መንግስት በህገ-ወጥ መንገድ በሀገሪቱ ውስጥ ለነበሩ የዚምባብዌ ዜጎች «ልዩ የቆይታ ጊዜ» ፈቃድ ሰጥቶ ነበር።ይህ ፖሊሲ በዋናነት በጎርጎሪያኑ 2007 እና 2009 ዓ/ም መካከል ከዚምባብዌ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ሸሽተው የመጡ  በሺዎች የሚቆጠሩ ዚምባቢያውያን  ሁኔታ መደበኛ እንዲሆን ለማድረግ ታስቦ ነበር። ይህ ልዩ  ፈቃድ   እስከ ህዳር 2021 ዓ/ም ድረስ  ተቀባይነት የነበረው ቢሆንም ፤በኋላ ግን  የደቡብ አፍሪቃ   ካቢኔ ከማሻሻል ይልቅ ሙሉ በሙሉ ፈቃዱን ለመሰረዝ ወስኗል።ይህ ውሳኔም ዚምባቢያውያኑን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል።  
ልዩ የመኖሪያ ፈቃድ የያዙ የዚምባብዌ ዜጎች ለዋና ቪዛ እንዲያመለክቱ ወይም ከደቡብ አፍሪቃ እንዲወጡ የ12 ወራት የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። አሁን ብቸኛው ተስፋቸው በዚምባብዌ ነፃ ፍቃድ ማህበር ጠበቆች አማካኝነት በፕሪቶሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ወር የቀረበው ህጋዊ ክስ ነው።

Südafrika | Mann aus Simbabwe mit Reisepass
ምስል Jon Hrusa/dpa/picture alliance

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ