የዳኝነት ክፍያ በኢትዮጵያ
ሐሙስ፣ ሰኔ 15 2015
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያ ደንብ ሊሻሻል ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገዉ ዉይይት ፍርድ ቤቶች ለዜጎች ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው የዳኝነት አግልግሎት እንዲሰጡ፣ ሕጉ ዘመኑ የደረሰበትን ነባራዊ እውነታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ደንቡን ማሻሻል አስፈልጓል ተብሏል።የፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎች ደንብ የወጣዉ ከ70 ዓመት በፊት ነበር።
በጉዳዩ ላይ ዛሬ ውይይት ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የደንቡን መሻሻል ተገቢነት በመግለጽ ይሁንና የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ከጨመረ ከሳሽ ክሱን ወደ ፍርድ ቤት እንዳያመጣ እንቅፋት እንዳይሆን ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ብርቱ ጥንቃቄ ያሻል በሚል የክፍያ ማሻሻያው የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳይጎዳ ተጠይቋል።ለሕጉ መሻሻል ከቀረቡ ማብራሪያዎች አንደኛው በኢትዮጵያ አብዛኛው የፍትሐ ብሔር አለመግባባቶችን ወደ ፍርድ ቤት የሚያመጣቸው የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ዝቅተኛ መሆን የሚል ነው። ይሁንና በአንድ የምክር ቤት አባል የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ መጨመር የፍትሐ ብሔር አለመግባባቶች እንዳይፈቱ እና ፍትሕ በአግባቡ እንዳይገኝ አያደርግም ወይ ተብሎ ጥያቄ ቀርቧል።
ምክር ቤቱ ጉዳዩ በዝርዝር ታይቶ ዳግም ለምክር ቤቱ ለውይይት እንዲቀርብ ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ዐፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በድኦ "ፍርድ ቤቶች ለሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎት ፍትሐዊ እና ተመጣጣኝ የዳኝነት ክፍያ ማስከፈል እንዲችሉ በሥራ ላይ ያለው የ1958 ቱ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ይደነግጋል" በዚህ ምክንያት ተመጣጣኝ ክፍያ ሊያገኙ የተገባ ነው በማለት ደንቡን ማሻሻል ያስፈለገበትን ምክንያት ገልፀዋል።
"አሁን ያለው የዳኝነት ክፍያ ተመኑም ሆነ የአከፋፈል ሥርዓቱ ላለፉት 70 ዓመታት ምንም አይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት እየተሰራበት ይገኛል።
አምስት የምክር ቤት አባላት ዛሬ በነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎ አስተያየት ሰጥተዋል።
"የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ከጨመረ ከሳሽ ክሱን ወደ ፍርድ ቤት እንዳያመጣ ያደርጋል" ማሻሻያ ማድረጉ ተገቢ ነው ። ይሁን እንጂ ቋሚ ኮሚቴው ሲያይ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት ጉዳይ አለ። ዜጎች ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው። መብቶቻቸው እና ጥቅሞቻቸው በተገፉ ጉዜ ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብሽ የማይታለፍ መብታቸው ነው። ይሁን እንጂ በክፍያ መብዛት ምክንያት ዜጎች መብቶቻቸው ቢጎዱ ሳያቀርቡ እንዳይቀሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት" ብለዋል።
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያ መጨመር ፍርድ ቤቶች ለዜጎች ቀልጣፋ ፣ ተደራሽ እና ጥራት ያለው የዳኝነት አግልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ የሚያግዝ ቢሆንም የፍትሐ ብሔር አለመግባባቶች እንዳይፈቱ እንቅፋት እንዳይሆንም ሥጋት አጭሯል።ምክር ቤቱ በዚሀ ላይ በስሱ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
ሰሎሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ