1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጊቤ ወረዳ 12 ቀበሌያት ጥያቄና ያስከተለው የአገልግሎት መስተጓጎል

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 16 2017

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ጊቤ ወረዳ በሚገኙ 12 ቀበሌዎች መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሙሉና በከፊል በመዘጋታቸው መቸገራቸውን ነዋሪዎች አመለከቱ። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የጤና፣ የትምህርት እና የግብር አሰባሰብ ሥራዎች በየአካባቢያቸው እየተከናወኑ አለመሆናቸውንም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4oZaN
ሆሳዕና ከተማ
ሆሳዕና ከተማ ፎቶ ከማኅደር ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የጊቤ ወረዳ 12 ቀበሌያት ጥያቄና ያስከተለው የአገልግሎት መስተጓጎል

 ቀበሌዎቹን በአንድ ወረዳ ለማደራጀት ላለፉት ሃያ ዓመታት በባለሥልጣናት የተገባው ቃል ገቢራዊ አለመሆን በነዋሪዎቹ ላይ ያስከተለው ቅሬታ ለአገልግሎቱ መስተጓጎል ምክንያት ነው ተብሏል። የነዋሪዎቹን የአደረጃጀት ጥያቄ በተደጋጋሚ ለመንግሥት ማቅረባቸውን ለዶቼ ቬለ የገለጹት የአካባቢው የክልል እንደራሴ ምክር ቤት አባል በበኩላቸው ጥያቄው በበጀት እጥረት ምክንያት ተፈጻሚ አለመሆኑ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።   

የጊቤ ወረዳ 12 ቀበሌያት ጥያቄና ያስከተለው የአገልግሎት መስተጓጎል

አቶ ዮሐንስ ኦቶሮ እና አቶ ታጠቅ አብረሃም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ጊቤ ወረዳ የቸቾ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው። የእነሱን ቀበሌ ጨምሮ በወረዳው የሚገኙ 12 ቀበሌያት በአንድ የወረዳ መዋቅር እንዲተዳደሩ ከ20 ዓመት በፊት ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን እንደሚያውቁ አቶ ዮሐንስ ኦቶሮ እና አቶ ታጠቅ አብረሃም ይናገራሉ። በወቅቱ ጥያቄው የተነሳው ቀበሌያቱ ከጊቤ የወረዳ ማዕከል በጣም የራቁ በመሆናቸው መንግሥታዊ አገልግሎቶቹን በቅርበት ለማግኘት ታስቦ እንደነበር የጠቀሱት አስተያያት ሰጪዎቹ «ነገር ግን የጥያቄው አግባብነት ያለውና አሳማኝ መሆኑ በወረዳ ፣ በዞንና በቀድሞው የደቡብ ክልል ታምኖበት ይሁንታን አግኝቶ ቆይቷል። ችግሩ ግን ጥያቄው እስከዛሬ ተፈጻሚ ሊሆን አልቻለም። በየጊዜው የሚመጡ አመራሮች ቃል ቢገቡም ምላሽ ባለመገኘቱ ነዋሪውን ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጓል » ይላሉ።

የመንግሥታዊ አገልግሎቶች መስተጓጎል

በቀበሌዎቹ ከመዋቅር ጥያቄው ጋር በተያያዘ አሁን መደበኛ የጤና፣ የትምህርት እና የግብር አሰባሰብ ሥራዎች እየተከናወኑ አለመሆናቸውን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ልጆች እቤት ለመዋል መገደዳቸውን የተናገሩት የቸቾ ቀበሌ ነዋሪዎቹ አቶ ዮሐንስ እና አቶ ታጠቅ «አብዛኞቹ የጤና ተቋማት ዝግ ናቸው። የተወሰኑትም ቢሆን በውስጣቸው ምንም አይነት መድኀኒት የላቸውም። በተለይ በአካባቢው እየጨመረ በመጣው የወባ በሽታ የተጠቁ ነዋሪዎችም በቂ ህክምና ለማግኘት ተቸግረዋል። በተለይ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በቀበሌዎቹ ግብር እየተሰበሰበ እንዳልሆነ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ «የአካባቢው አስተዳደር የመዋቅር ጥያቄውን ባለመመለሱ የተነሳ ከሕዝቡ ጋር ተለያይቶ ነው ያለው። ሕዝቡ የክልሉ መሪዎች መጥተው ያናግሩን እያለ ነው» ብለዋል።

የግብር ግዴታችሁን እየተወጣችሁ ጥያቄያችሁን ማቅረብ ለምን አልቻላችሁም? ድርጊቱስ አመፅ አያስመስልባችሁም ወይ?በሚል ዶቼ ቬለ ላቀረበላቸው ጥያቄም «ይህ ግብር መከልከልም አይደለም። ግብርና ሌሎች መዋጮዎችንም በእጃችን ይዘናል። ጥያቄው የክልል መንግሥት ብዙ ጊዜ ቃል የገባውን መጥቶ ያናግረን የሚል ነው። እንከፍላለን መንግሥት መጥቶ ያናግረን፣ መጥቶ ግብሩን ይውሰድ እያለን እኮ ነው» ብለዋል።

የአካባቢው የሕዝብ እንደራሴ ምላሽ

ዶቼ ቬለ የቀበሌዎቹን ነዋሪዎች ጥያቄና የተከሰተውን የአገልግሎት መስተጓጎል በሚመለከት ከወረዳ እስከ ክልል የሚገኙ የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም። ያም ሆኖ የቀበሌያቱን ነዋሪዎች በመወከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ሙላቱ ጫኬ ጥቄያው የቆየና ተገቢ ነው ይላሉ።

በወረዳው፣ ሶዳ ፣ ቀቀማ ፣ ሜጋቾ እና ኦሎዋ ቀበሌዎችን ጨምሮ 12 ቀበሌዎች ከወረዳው የአስተዳደር መቀመጫ ከሆነችው ሆመቾ በጣም የራቁ በመሆናቸው ሕዝቡ ለአገልግሎት መቸገሩን የተናገሩት የሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባሉ «ጥያቄውን በተደጋጋሚ በምክር ቤት ጉባኤ ላይ አንስቼያለሁ። ነገር ግን በየጊዜው ቃል ከመግባት ባለፈ ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም። ወረዳውን ለማዋቀር የበጀት እጥረት አለብን የሚል ምክንያት እየተሠጠ ቢገኝም በእኛ በኩል አሁንም ምለሽ እየጠበቅን እንገኛለን» በማለት አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ትምህርትና ጤናን ጨምሮ መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎታቸውን መስጠት በሚችሉበትና የአደረጃጀት ጥያቄውን በተመለከተ ሕዝቡና የአካባቢው አስተዳደር የሚገናኙበት መድረክ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም የምክር ቤት እንደራሴው ጠቁመዋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ  

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ