1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 20 አዎንታዊ እና አሉታዊ ፍሬው ስታወስ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 2016

ዛሬ ግንቦት 20 ሲታወስ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ ከጠዋት ጀምሮ እንደ ወትሮው የስራ ቀናት መንገዶች በተሸከርካሪዎች አልተጨናነቁም፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ስላልሄዱ፣ ሰራተኞችም ወደ መስሪያ ቤታቸው የመሄድ ግዴታ ስላልነበረባቸው በከፊል የበዓል ድባብ ተስተውሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4gO9u
Äthiopien Stadtbild Adis Abeba mit Schriftzug
ምስል Seyoum Getu/DW

የግንቦት 20 አዎንታዊ እና አሉታዊ ፍሬው ስታወስ

ኢትዮጵያውን ብያንስ ለ27 ዓመታት ያስተዳደረው የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ግንባር የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ለ17 ዓመታት በስልጣን ላይ የነበረውን የወታደራዊ አገዛዝ (ደርግ)ን ከስልጣን በማስወገድ የመንግስትነት በትረ ስልጣን የያዘውም ልክ የዛሬ 33 ዓመት ነበር፡፡ 
ኢሕአዴግ በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የበላይነት በሚመራበት በነዚያ 27 ዓመታት ይህ ቀን እንደ ብሔራዊ በዓል ተደርጎ ከመከበሩም ባለፈ እለቱ በተለያዩ የአከባበር ስርዓቶችም ያሸበርቅ ነበር፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታ ግን የበዓሉ ብሔራዊ አከባበር ባይሻርም መዲናዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች መንግስታዊ የበዓሉ አከባበር ከመደብዘዝም አልፎ ምንም አይነት አጀብ የሌለው ሆኗል፡፡

ለመሆኑ የግንቦት 20 ውጤቱ ወይስ ጉዳቱ ይጎላ ኖሯል?
ዛሬ ግንቦት 20 ሲታወስ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ ከጠዋት ጀምሮ እንደ ወትሮው የስራ ቀናት መንገዶች በተሸከርካሪዎች አልተጨናነቁም፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ስላልሄዱ፣ ሰራተኞችም ወደ መስሪያ ቤታቸው የመሄድ ግዴታ ስላልነበረባቸው በከፊል የበዓል ድባብ ተስተውሏል፡፡ ይህ እለት አስቀድሞ ብሔራዊ በዓል ተብሎ ተደንግጓልና፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ዞር ዞር ብለን በተመለከትንባቸው መስሪያ ቤቶችም፤ ባንኮችን ጨምሮ በዝግ ውለዋል፡፡ 
ይሁንና እንደ ወትሮው ከስድስት ኣመታት በፊት የነበረው ግንቦት 20ን በፓናል ውይይቶች እና በየቦታው ተሰባስቦ ቀኑን የማድመቂያ ስነስርዓቶች የትም አልታዩም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ወደ ስልጣን ካመጣው መንግስታዊ ለውጥና በተለይም ከኢህአዱግ መፍረስ በኋላ የዚህ ቀን ብሔራዊ በዓልነት ባይቋረጥም አከባበሩ ግን እጅጉን ደብዝዞ ቆይቷል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ በከፊል
አዲስ አበባ ከተማ በከፊልምስል Seyoum Getu/DW


ለመሆኑ የግንቦት 20 ውጤቱ ወይስ ጉዳቱ ይጎላ ኖሯል?
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ባለስልጣን እና ከልጅነታቸው ጀምሮ በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የፖለቲካ ትግል ሂደት ተሳትፎ እንደነበራቸው የሚገልጹት ፖለቲከኛ መስፍን ደሳለኝ እለቱን የሚያስታውሱት ከአዎንታዊና አሉታዊ ውጤቶቹ ጋር ብሆንም አዎንታዊ ውጤቱ ይጎላባቸዋል፡፡ “ይህ ቀን ሕወሓት ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን አዲስ አበባን የተቆጣጠረበትና አዲስ ምህራፍ የከፈተበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የራሱ ጥሩ ነገር ቢኖረውም ደርግ ስርዓት አፋኝ፣ ጨቋኝና ገዳይ ስርኣት ስለነበር ያ መገርሰሱን እንደ ትልቅ ድል እቆጥረዋለሁ፡፡ ይህ ቀን ብሔሮች የመደራጀት መብትን ጨምሮ በብዙ መልኩ መብታቸው እንዲከበር የረዳ ቀን ነው ብዬ አምናለሁ” ብለዋል፡፡
አቶ መስፍን በህዝብ ትግል መጣ ያሉት የግንቦት 20 ትልቅ ለውጥ አተገባበር ላይ እክል ገጥሞት ሰፋፊ ጉዳቱም አብሮት የሚታወስ ማድረጉን አንስተዋል፡፡ “አተገባበር ላይ የተዛነፈ ይመስለኛል፡፡ ብሔሮች በቋንቋቸው መገልገልልና ባህላቸውን ማሳደግ ትልቅ ውጤት ሆኖ፤ ነገር ግን ብሔሮች እርሰበርሳቸው እንዲጋጩ የሚያደርግ ለከፋፍለህ ግዛ ስርዓት በር የከፈተ፤ ዜጎች ከብሔራቸው ክልል ውጪ ሲኖሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እዲቆጠሩ ያደረገ ስርዓትንም ያስከተለ ቀን ነው ይህ ቀን፡፡ አጠቃቀሙ ላይ ባጋጠመው ክፍተት ወደ አላስፈላጊ ትርክትም ተገብቷል” ነው ያሉት፡፡
አሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለግጭቶች አለማባራት ይህን ቀን ተከትሎ የተዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት ዋነኛ ነቀርሳ ነው በሚል ቀኑን የሚራገሙ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ እለት በተጀመረው የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ እለቱ ያስገኘው ጥቅም ጉልህ ነው ብለው የሚከራከሩ ወገኖች ቁጥርም አይናቅም፡፡ ዛሬ በብሔራዊ ደረጃ ተከብሮ የዋለውን እለቱን በማስመልከት የአሜሪካ መንግስትም አዲስ አበባ ውስጥ ባለው ኤምባሲዉ በኩል እለቱን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ካስተላለፉ ተጠቃሽ ነው፡፡
ለኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና ግን ከዚህ ቀን ጋር ተያይዞ የመጣው ፖለቲካዊ ስርዓት ጥቅሙ ይጎላል ለማለት አያስደፍርም፡፡ “ጥቅሙ ይጎላል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክኒያቱም ያንን የተከተለው ግጭት የታለሙ ውቼቶችን ያመጣ አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ እኔ የመንግስቱ ኃ/ማሪያም ከስልጣን መወገድን ከምደግፉት ውስጥ ነኝ፡፡ አንድ ትውልድ የበላና አብዮትን ያኮላሸ ስርዓት ነበርና ለሱ የሚራራ ልብ የለኝም፡፡ ሆኖም ያንን ተከትሎ የመጣው ሀቀኛ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ፍላጎት ባለማሟላቱ ከስሜት ወጥተን ስናየው ቀኑ መከበር አለበት የሚያስብል ነገር የለውም” ነው ያሉት፡፡
በቅርቡ በረቂቅ ደረጃ ላይ ያለውና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ያልጸደቀው በኢትዮጵያ የብሔራዊ፣ የህዝብ እና የኃይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩባቸውን ቀናት የሚደነግገው አዋጅ ግንቦት 20ን ከብሔራዊ በዓላቱ ዝርዝር ውጪ ማድረጉ ተመላክታል፡፡ አዋጁ እስከ ሚቀጥለው ኣመት ወይም በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ ምናልባትም የዘንድሮው ግንቦት 20 በብሔራዊ በዓልነት ሲከበር የመጨረሻው የመሆን እድል አለ፡፡ 

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ