1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጦርነት ሰለባዎቹ ሴቶች ሰቆቃ

ማክሰኞ፣ መስከረም 10 2015

ባሳለፍነው ዓመት 2014 የመጨረሻ ወር ነሐሴ ላይ ዳግም በሰሜን ኢትዮጵያ ባገረሸው ውጊያ ለጾታዊ ጥቃት የሚጋለጡትን ሴቶች ቁጥር እንዳበራከተው እየተነገረ ነው። በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የሴቶች እና ሕጻናት ጥቃትን የሚከታተለው ዘርፍ አስተባባሪ እንደሚሉት በአሁኑ ጦርነት ደግሞ ሴቶች መደፈር ብቻ ሳይሆን እየተገደሉም ነው።

https://p.dw.com/p/4H7gr
Tigray-Krise in Äthiopien
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP

ጤና እና አካባቢ

በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የሴቶች እና ሕጻናት ጥቃትን የሚከታተለው ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር መዲና ወርቅነህ ውጊያ ባገረሸባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አዋቂ እና አዳጊ ሴት ልጆች አሳሳቢና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ። አዲስ ዓመት ብለን መቁጠር ከጀመርን ገና ጥቂት ቀናት ብቻ ነው። ሆኖም ግን ዘንድሮም በከረመው ችግር እና ባደረገው የጦርነት ጦስ አካላቸው አልፎም ሕይወታቸው ለአደጋ የተጋለጠ እናቶች ፣ ወጣቶች እና አዳጊ ሴቶች ጉዳይ አሳሳቢነቱ ቀጥሏል።

ባለፈው በሰሜን እና ደቡብ ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ወረራ እና ጦርነት ሲካሄድ ተገድደው የተደፈሩ 1050 የሚሆኑ ሰለባዎችን ጉዳይ መመልከታቸውን፤ እነሱንም ለመርዳት መንቀሳቀሳቸውን በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የሴቶች እና ሕጻናት ጥቃትን የሚከታተለው ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር መዲና ወርቅነህ ገልጸውልናል። ባለፈው ዓመት ነሐሴ አጋማሽ ላይ ዳግም በተቀሰቀሰው ውጊያ በራያ ቆቦ በርካታ አካባቢዎች አሁን የሴቶች ስቃይ ቀጥሏል ነው የሚሉት። ጦርነቱም የጦር መሣሪያ ባነገቡት ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ አጽንኦት የሰጡት ሲስተር መዲና ሕጻን አዋቂ ሳይል ሴቶች የበቀል ሰለባ ሆነዋል ይላሉ። 

ካለፈው የወሲብ ጥቃት ሰለባዎች ተሞክሮ የቀሰሙ የመሰሉት እነዚህ ተገድደው የተደፈሩ ሴቶች ተገቢውን የህክምና እርዳታ ፍለጋ መንገድ ሲያገኙ ወደእነ ሲሲተር መዲና መምጣታቸው አንድ ነገር ቢሆንም አሁንም ግን ብዙሃኑ በውጊያው ምክንያት መውጫ እንዳላገኙም ነው የገለጹልን። እሳቸው እንደሚሉትም በሴቶቹ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አሁንም ከመቀጠሉ ሌላ ባለፈው ከታየው የከፋ ነው። 

Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

የህክምና ባለሙያዋ እርዳታ ፍለጋ ወደ እነሱ የሚመጡት የወሲብ ጥቃት ሰለባዎችን በመመልከት ችግራቸውንም በማድመጥ ልባቸው ደክሟል። በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙትን ተገድደው የተደፈሩ ሴት ልጆችን ስቃይ፤ በዕድሜ ጠና ያሉትም ያለፍላጎታቸው ለጥቃት መዳረጋቸው እያንገበገባቸው፤ ኑሯቸው ተናግቶ፤ ተስፋቸው ጨልሞ ለማጽናናት መታገሉ አቅማቸውን የጨረሰው መስሏል። ሁኔታውን ለማብራራት ከእንባ ጋር ታገሉ። እንዲህም ሆኖ ግን አሁንም በውጊያው ቀጣና የሚገኙት ሴቶች እጣ ፈንታ ያብሰለስላቸዋል።

አካባቢው የጦርነት ቀጣና በመሆኑ እንደልብ መንቀሳቀስ የሚታሰብ አይደለም። ቢቻልም እንኳ ለዚህ የሚሆን አምቡላንስ እንደሌላቸውም ገልጸውልኛል። ከባህል አኳያም ተገድደው የተደፈሩት እህቶች እና እናቶች የቀድሞ ኑሯቸውን መቀጠል የማይታሰብ ሆኖባቸው ራሳቸውን ችለው ቀሪ ዘመናቸውን ለመግፋት የሌሎችን ድጋፍ ፈላጊዎች ሆነዋል። ሲሰተር መዲና እንደሚሉት የተኩስ አቁም ብሎም የድርድር ወሬ ሲነገር በመሰንበቱ ኅብረተሰቡ ሌላ ዙር ጦርነት ይከሰታል ብሎ አልጠበቀም ነበር። ሰላም ሲጠብቅ ዳግም ውጊያ ዳግም ወረራ መከሰቱ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል። እናም ይላሉ የህክምና ባለሙያዋ በውጊያው ኑሮው ለተመሰቃቀለው እና ለጥቃት ሰለባ ለሆነው ኅብረተሰብ ሲባል ውጊያ ጦርነቱ ቆሞ ፖለቲከኞች ወደ ሰላም የሚመጡበት መንገድ መፈለግ አለበት።

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ