1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይና የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ግንኙነት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 18 2017

"ቅኝ ገዢዎች ቅኝ የሚገዙትን ቦታ፣ ሀገር እንደ ቅኝ ግዛታቸው ነው የሚያዩት። ፈረንሳይ ግን የራሷ አካል አድርጋ ነው የምታያቸው። ለዚህም ማሳያው ብዙዎቹ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ሀገራት አንደኛ በፈረንሳይ ሕግ ማውጫ ምክር ቤቶች ውክልና ነበራቸው" ተንታኝ

https://p.dw.com/p/4ocZG
MALI-CONFLICT-UNREST-ARMY-TAKUBA
ምስል AFP via Getty Images

የኢማኑኤል ማክሮን የአፍሪካ ቀንድ ሰሞነኛ ጉብኝት

ፈረንሳይ ቅኝ በገዛቻቸው የአፍሪካ ሀገራት ያላት የወታደራዊ እንቅስቃሴ እና ተሳትፎ እየተዳከመ ስለመሆኑ ይነገራል።

ሀገሪቱ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከነበራት ወታደራዊ ተሳትፎ ለመውጣታቸው ልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን ወታደሮቿ በመፈንቅለ መንግሥት ተሳትፎ አላቸው የሚለው ክስ ተጠቃሽ ነው።

ሀገሪቱ እስካሁን ተቀባይነቷ ያልተሟጠጠበት ከሚባሉት የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ መካከል ጥቂት የማይባሉ ኃያላን ሀገራት ወታደራዊ የጦር መንደር የገነቡባት ጅቡቲ ናት። 

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከ1500 በላይ የፈረንሳይ ወታደሮች ወደሚገኙባት ጅቡቲ ባለፈው ሳምንት ጉብኝት 
ያደረጉ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያም ጎራ ብለው ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ እና ቱርክ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን የሻከረ ዲፕሎማሲ ለማሸማገል ያደረገችውን ጥረት እውቅና ሰጥተው ተመልሰዋል።

ፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿን "የራሷ አካል አድርጋ ነው የምታየው" - ተንታኝ 

ፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿከሆኑት ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ሀገር ናት። ሀገሪቱ ከእነዚህ ሀገራት ያላት ግንኙነት "ውስብስብ" ነው የሚሉት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ፈረንሳይ ቅኝ ገዢ በነበረችበት ጊዜ እና ከዚያ በኋላ ቅኝ ከገዛቻቸው ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከሌሎች ቅኝ ገዢዎች ለየት ያለ ነው ብለዋል። እንዴት?

"ቅኝ ገዢዎች ቅኝ የሚገዙትን ቦታ፣ ሀገር እንደ ቅኝ ግዛታቸው ነው የሚያዩት። ፈረንሳይ ግን የራሷ አካል አድርጋ ነው የምታያቸው። ለዚህም ማሳያው ብዙዎቹ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ሀገራት አንደኛ በፈረንሳይ ሕግ ማውጫ ምክር ቤቶች ውክልና ነበራቸው" ብለዋል።

ፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿን "የራሷ አካል አድርጋ ነው የምታየው" - ተንታኝ 
ፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿን "የራሷ አካል አድርጋ ነው የምታየው" - ተንታኝ ምስል Reuters/G. Horcajuelo

የፈረንሳይ እና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ግንኙነት መሻከር 
ፈረንሳይ ከይፋዊው የቅኝ ግዛት ማብቃት በኋላ ቅኝ ከገዛቻቸው ሀገራት "የመረረ ጥላቻ" ታስተናግዳለች የሚሉት እኒሁ ባለሙያ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ በመግባት እስከ መፈንቅለ መንግሥታት ውስጥ ወታደሮቿ ተሳትፈዋል የሚል ወቀሳ ይነሳባታል። 

"አብዛኞቹ መፈንቅለ መንግሥቶች አስተውለን ከሆነ -አፍሪካ ውስጥ የተካሄዱት በወታደሮች የተከናወኑ ናቸው። ብዙው ደግሞ የፈረንሳይ ሀገር ግንኙነት ከሀገራት ወታደራዊ ተቋማት ጋር የበለጠ ጠንከር ያለ ከመሆኑ የተነሳ በእንደዚህ አይነት ነገር ቢታሙ ተፈጥሯዊ ነው" 

ፈረንሳይ እየገጠማት ያለው ብርቱ የግንኙነት መሻከር  ባለሙያው እንደሚሉት ከዚህም ከፍ ያለ ነው።

"የውጤታማነት ጥያቄም ይነሳባቸዋል። ከቦኩሃራም እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ። ከወርቅ ጋር ተያይዞ በሀብት ምዝበራ 
የሚታሙበት አለ፤ ሴቶችን አስገድዶ መድፈር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይቀርብባቸዋል" ሲሉ ዘርዝረዋል።

 

የኢማኑኤል ማክሮን የአፍሪካ ቀንድ ሰሞነኛ ጉብኝት

ዋና ዋና ሃያላን ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴያቸውን እና የንግድ መስመሮችን በተለይም የባበል መንደብ ወሳኝ የባህር ወሽመጥን ለመጠበቅ፣ የባሕር ላይ ውንብድናን ለመከላከል እንዲሁም የቀጣናውን ሰላም ለማስከበር በሚል ወታደራዊ የጦር መንደሮች የገነቡባት ጅቡቲ አሁን ለፈረንሳይ በአፍሪካ የቀረች የወታደሮቿ መገኛ ሀገር ናት። ፕሬዝዳንቷ ኢማኑኤል ማክሮንም ሰሞኑን ወደ ጅቡቲ የመጓዛቸው ምክንያት ይህ ስለመሆኑ ዘገባዎች አመልክተዋል።

ከጅቡቲ መልስ ቅዳሜ ዕለት አዲስ አበባ የገቡት ፕሬዝዳንት ማክሮንከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን እና የጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

የቱርኩ ፕሬዝደንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶኻን ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ለማሸማገል ላደረጉት ጥረትም አድኖቆት ሰጥተዋል። ምንም እንኳን በፖለቲካ ተንታኞች ምልከታ የቱርክ ጥረት ለአፍሪካ ሕብረትም ሆነ ለአውሮፓ ሕብረት እንደ ውድቀት የሚታይ ተደርጎ ቢታይም።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ያላትን ፍላጎት ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር እንደተወያዩበት ገልፀው በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ከፈረንሳይ እና መሪዋ "የሚጨበጥ" ውጤት ይጠብቃሉ ብለዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ