1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ግምገማ

ሐሙስ፣ መጋቢት 5 2016

የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተን እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ ለማዋሃድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለፁት የበለፀጉ ሀገራት በአማራ በኦሮሚያና በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተከሰቱት ቀውሶች በተመሳሳይ ቁርጠኝነት ችግራቸው እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል። ሁለቱ ወገኖች በቂት ወራት ተመሳሳይ ውይይት ለማድረግ ስለመወሰናቸውም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/4dVqs
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የፊርማ ስነ ስርዓት
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የፊርማ ስነ ስርዓትምስል PHILL MAGAKOE/AFP/Getty Images

የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ግምገማ

ለግጭት ማቆም ስምምነቱ የተሰጡ ዐወንታዊ ድጋፎች

በኢትዮጵያ የአውሮጳ ሕብረትን ጨምሮ የሰባት ሀገራት ተልዕኮዎች አፍሪካ ሕብረት ያሰናዳው የመጀመሪያው የፕሪቶሪያ የተኩስ ማቆም ስምምነት አፈፃፀም ግምገማ መጠናቀቅን ተከትሎ ባወጡት የጋራ መግለጫ ቀሪ የአተገባበር ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። በግጭቱ የተጎዱትን መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ ተጎጂዎችን ያማከለ የሽግግር የፍትሕ ሂደት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን  የስምምነቱ ፈራሚዎች መገናኘታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አድርገዋል። የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተን እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ ለማዋሃድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለፁት እነዚህ የበለፀጉ ሀገራት በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተከሰቱት ቀውሶች በተመሳሳይ ቁርጠኝነት ችግሩ እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል። ሁለቱ ተዋናዮች በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ተመሳሳይ ውይይት ለማድረግ ስለመወሰናቸውም ተነግሯል።የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ግምገማ

የዲፕሎማሲ ተንታኝ አስተያየት

በጉዳዩ ላይ ከዚህ ቀደም ዶቼ ቬለ የጠየቃቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ የስምምነቱ አንኳር የሚባሉ ጉዳዮች አሁንም ተግባር የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል። ስለ ውይይቱ ውጤት ከፌዴራል መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ሞክረን ነበር። ለጊዜው ባይሳካም ከሳምንታት በፊት ከዶቼ ቬለ ጋር ቃለ ምልልስ ላደረጉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ የቀድሞ ተዋጊ ታጣቂዎችን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር። ዓመት ስለደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት የፖለቲከኞች አስተያየት

የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ፈራሚዎች ከአደራዳሪዎቹ  ጋር
የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ፈራሚዎች ከአደራዳሪዎቹ ጋር ምስል PHILL MAGAKOE/AFP

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል የስምምነቱን አፈፃፀም በሚመለከት የሚቃረኑ መግለጫዎች ሲወጡ ተስተውሏል። የተፈናቃዮች ተመልሶ ወደ ቀያቸው አለመሄድ፣ የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው ቦታዎች ጉዳይ፣ አሁንም ከትግራይ አልወጡም የሚባሉ የአማራ እና የጎረባት ሀገር ኤርትራ ኃይሎች የመኖራቸው ጉዳይ የዚህ ልዩነት መነሻ ሆነው ይጠቀሳሉ። የዲፕሎማሲ ተንታኙ ልዩነቱ ከምንም በላይ በፖለቲካ ቁርጠኝነት መፈታት ያለበት መሆኑን አፅንዖት ሰጥተውታል።

የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ማሳሰቢያ

የአፍሪካ ሕብረት የፕሪቶርያውን የግጭት ማቆም ስምምነት የሚከታተለው ተቆጣጣሪ ቡድን ሥራውን እንዲያጠናክር ጠይቋል። የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ  ማህመት በውይይቱ መክፈቻ እለት "እስከ አሁን ድረስ የማይካዱ ስኬቶች ቢኖሩም፤ የፖለቲካ ውይይት ሂደት፣ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ መበተንና መልሶ የማዋሃድ ፣ እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ አስቸኳይ ትኩረት የሚሹ" ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀው ነበር።

ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር