1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሪቶርያዉ ስምምነት አፈጻፀምና የትግራይ ፖለቲከኞች ቅሬታ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 1 2015

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና በትግራይ ሀይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የተደረገው ደምአፋሳሽ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ስድስት ወራት አልፈዉታል። በትግራይ የሚገኙ ፖለቲከኞች የስምምነቱን ተግባራዊነት በአዎንታ ቢቀበሉትም በርካታ በፍጥነት መፈፀም ይገባቸው የነበሩ ተግባራት እስካሁን ተዘንግተዋል ሲሉ ይተቻሉ።

https://p.dw.com/p/4R694
Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል PHILL MAGAKOE/AFP

በፍጥነት መፈፀም ይገባቸው የነበሩ ተግባራት ተዘንግተዋል

 

የሁለት ዓመቱ ጦርነት ያስቆመ የፕሪቶርያ ስምምነት ከተፈረመ ስድስት ወራት አልፈውታል። የፕሪቶርያው ውል ትግበራ ዙርያ የትግራይ ፖለቲከኞች ምን ይላሉ ?

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የተደረገው ደምአፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ስድስት ወራት አልፈዉታል። በስምምነቱ መሰረት በጦር መሳርያ ይደረግ የነበረ ተኩስ ወድያው ቆሟል፣ በሂደት በትግራይ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች እየተመለሰ ነዉ፣ ትጥቅ የመፍታት እና ሌሎች ተግባራት ሲከውኑ ተስተውሏል። የሁለቱ የቀድሞ ተፋላሚ ሐይሎች መቀራረብ የሚያሳዩ ግንኙነቶች እና ውይይቶችም በመቐለ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የታዩ ሲሆን፣ ይህም የሰላም ሂደቱ እድገት አመላካች ተደርጎ ይቀርባል። በሌላ በኩል የሰላም ስምምነቱ ትግበራዎች በሙሉነት አለመፈፀም እንዲሁም ጦርነቱ ያስከተላቸው ችግሮች አለመፈታት፥ በተለይም በትግራይ ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ እንዲቀጥል አድርጎት እንዳለ ፖለቲከኞች ይገልፃሉ። በስምምነቱ አፈፃፀም ዙርያ የጠየቅናቸው የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሐጎስ ወልዱ፣ የታዩ ኘ

አወንታዊ ለውጦች የሚበረታቱ ቢሆንም በርካታ በፍጥነት መፈፀም ይገባቸው የነበሩ ተግባራት እስካሁን ተዘንግተዋል ባይ ናቸው። " ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው አልተመለሱም፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች በሙሉእነት አልተከፈቱም፣ እርዳታ የለም" የሚሉት አቶ ሐጎስ ወልዱ በዚህ ምክንያት ህዝብ አሁንም እየተቸገረ መሆኑ ያነሳሉ።

ሌላው አስተያየት የሰጡን የዓረና ትግራይ ከፍተኛ አመራር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፣ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት አሁንም ያልተፈፀሙ፥ ቢፈፀሙም በተባለው መሰረት ያልሆኑ ተግባራት ባለፉት ስድስት ወራት መታየታቸው ይጠቁማሉ። እንደ አቶ ዓምዶም ገለፃ "በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት በትግራይ ሁሉ አካታች ግዚያዊ አስተዳደር ሊቋቋም ቢገባም፣ ህወሓት እና ደጋፊዎቹ ብቻ የሚሳተፉበት አስተዳደር ተቋቁሟል" በማለት ይነቅፋሉ። ሌላው ተቃዋሚ ፖርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በበኩሉ ከሰለም ስምምነቱ በኃላ የትግራይ ሰብአዊ ቀውስ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ዘንግቶታል ይላል። በሰላም ስምምነቱ የስድስት ወራት አተገባበር ዙርያ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ማብራርያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም።

 

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ