ደቡብ ወሎ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሮሮ
ረቡዕ፣ ሰኔ 19 2016ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ የምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች ተፈናቅለው አሁን ላይ አማራ ክልል ደቡብ ወሎ የአገር ውስጥ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ባለው የምግብና መጠጥ አቅርቦት መቸገራቸውን አስታወቁ፡፡ ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት መሰል የአቅርቦት እጥረት የተባባሰው በተለይም መንግስት ተፈናቃዮችን ወደ ነባር ቀዬያቸው ለመመለስ ግፊት ማድረግ ከጀመረ ወዲህ ነው፡፡ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የደቡብ ወሎ ቃሎ ወረዳ ቻይና ተፈናቃዮች ካምፕ ነዋሪ ከምእራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ከተፈናቀሉ ድፍን ሶስት ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ይገልጻሉ፡፡ አስተያየት ሰጪ ተፈናቃዩ በዚህ የተፈናቃዮች ካምፕ ካሉት 190 አባወራዎች አንዱ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለተፈናቃዮቹ የሚቀርበው የእርዳታ አቅርቦት መጠን ማሽቆልቆሉን አስረድተዋል፡፡በሐይቅ የሚገኙ ተፈናቃዮች የእርዳታ ተማፅዕኖ
የተፈናቃዮች እርዳታ አቅርቦት መቀነስ
“በሶስት ወር ነው 15 ኪሎ የእርዳታ እህ የሚከፋፈልልን፡፡ አሁን ደግሞ ባለፈው ወር የመጣልን ያቺው እርዳታም ተቀንሳ 12 ኪሎ ነው የደረሰን፡፡ ከሁሉ በላይ ግን አሁን አስቸጋሪው ውሃ ተቋርጦብን እጅጉን መቸገገራችን ነው” ይላሉ፡፡ አስተያየት ሰጪው አሁን ለተፈናቃዮች እጅጉን ፈታኝ የሆነው ጉዳይ የውሃ አቅርቦት ከተፈናቃዮቹ ካምፕ መቋረጡን አስረድተው፤ የውሃው መቋረጥ ምክንያት ምን እንደሆነ ግን እንደማያውቁትም ይግልጻሉ፡፡ “ውሃው ለመጥፋቱ ምክንያቱ ድርቅ ነው ይሉናል፡፡ ከተማው ላይ ግን ውሃ አይጠፋም፤ እና ጋር ብቻ ነው ውሃ የሌለው፡፡ ያው ከዚህ ተነሳ ከተማ ለከተማ እየዞርን ነው ውሃ ፍላጋ የምንከራተተው” ብለዋልም፡፡ ለደህንነታው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እኚው ተፈናቃይ ለውሃው መቋረጥም ሆነ ለእርዳታው መመናመን ምክንያት ያሉትንም ሲያስረዱ፡ “መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ወደ ነባር ቀዬያቸው እንድመለሱ ግፊት ማዱረጉን ብቀጥልም ተፈናቃዮች በዚያ ባለው ያልተቀረፈው የጸጥታ ስጋት የተነሳ ወደዚያ ለመመለስ ዝግጁነት የላቸውም” ነው ያሉት፡፡
የምግብና ውሃ አቅርቦት መመናመን
ሌላው በ2013 ዓ.ም. በዚያው ከሆሮ ጉዱሩ ዞን ሻምቡ ወረዳ ተፈናቅለው በዚሁ መጠለያ ካምፕ የሚገኙት የአገር ውስጥ ተፈናቃይ፤ የተፈናቃዩ ችግር ዛሬ ላይ የምግብና መጠጥ አቅርቦት እጥረት ነው ይላሉ፡፡ “ዛሬ ላይ ትልቁ ችግራችን ውሃ እና ምግብ እጦት ነው” የሚሉት እኒህ አስተያየት ሰጪ፤ በነፍስ ወከፍ ይሰጥ የነበረው የምግብ እርዳታ ወደ ከ15 ወደ 12 ኪሎ ግራም መውረዱንም ገልጸዋል፡፡ ይህም የሚሰጠው በሶስት ወር አንዴ ነው የሚሉት ተፈናቃዩ አብሮት ይሰጥ የነበረው ዘይትና ጨውም አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ከሁሉም የከፋው ደግሞ የውሃ አቅርቦት እጥረቱ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ እጅግ እሩቅ ስፍራ ላይ ካለው ወንዝ ህደው ውሃ ለመቅዳት እንደሚቸገሩና ለመጠጥ ውሃም ብሆን ከተማን ለማሰስ እንደሚገደዱ ነው የገለጹት፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪው የመልሶ ማቋቋምን በተመለከተም፡ “ባንድ ወቅት በተለይም ጥር ወር አከባቢ መንግስት እመልሳለሁ በሚል እንቅስቃሴ ብጀምርም አሁንም ድረስ ያልተረጋጉ አከባቢ የሆነውን ለጊዜው ትተውናል” ነው ያሉት፡፡ “የመመለስ ጉዳይ በተለይም ከሆሮ ጉዱሩ ለተፈናቀልነው አሁንም በዚያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስጊ ስለሆነ የእኛ እንደሚዘጌ ነው፡፡ አሁን እየተመለሱ ሉት ከነቀምት ዙሪያ ምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉና ወደ ባኮ አከባቢ የሆኑት ናቸው” ብለዋል፡፡በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ሮሮ
የተፈናቃዮች ችግር ስፋትና የመንግሥት አቅጣጫ
በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ግጭቶች በአማራ ክልል ከአንድ ሚሊየን የላቀ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተለያዩ የመጠለያ ካምፖች እና ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዳሉ ይነገራል፡፡ ስለነዚህ ተፈናቃዮች የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ለአማራ ክልል አደጋ ስጋትና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ቢሮ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ የኦሮሚያ ክልለ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን (ቡሳ ጎኖፋ) ኃላፊ አቶ ሞገስ ኢደኤ ከዚህ በፊት ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ግን በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ መርህ ብቻ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ስራ በክልሉ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡የፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ አታለል አቦሃይ እደሚሉት ግን፡ “ተፈናቃዮችን ለመርዳት ሁሉም ክልሎች የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩና በዚያ ያለው ችግር ገዝፎ ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር በራስ አቅም ምላሽ እንዲሰጡ እንደ አገር አቅጣጫ መቀመጡን” አስረድተዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ