ድርቅ + ግጭት + የዋጋ ውድነት = የኮንሶ ፈተና
ረቡዕ፣ ሰኔ 29 2014የኮንሶው ገበሬ የአቶ በርሻ ባቻ የበቆሎ እና የበሎቄ ሰብል ለአበባ ሳይደርስ ድርቅ ተጭኖታል። የአምስት ልጆች አባት የሆኑት በርሻ የቀበሌያቸው አስተዳዳሪ ጭምር ናቸው። አቶ በርሻ ባቻ "በአካባቢያችን ኃይለኛ ድርቅ ነው ያለው። ሰብሉ ከመሬት በቅሎ አበባ ሳያወጣ ነው የደረቀው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ማሳቸው ያለበትን ሁናቴ ያስረዳሉ። በዞኑ የባዓይቴ ቀበሌ ገበሬዎችም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል። የቀበሌው አስተዳዳሪ አቶ አስረስ ገቢኖ "ዘሩን ዘርተናል። ነገር ግን የዝናብ እጥረት ስለበዛ የበቀለ ነገር የለም እንዳለ ደርቋል። " በማለት የገጠማቸውን ተመሳሳይ ፈተና ይገልጹታል። "ከብቶችም የሚበሉት ነገር [የለም።] የሰው ልጅ በጣም ጉዳት ላይ ነው" የሚሉት አቶ አስረስ ሥጋት ተጭኗቸዋል።
አቶ በርሻ እና አቶ አስረስ በሚያስተዳድሯቸው ቀበሌዎች የበረታው ድርቅ በኮንሶ ዞን ሥር የሚገኙ ሁሉንም አካባቢዎች ያዳረሰ ነው። በኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌዴኖ ከወይታ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በዞኑ የሶስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በመክሸፋቸው በቂ ምርት አልተገኘም። ከቦረና ዞን የሚጎራበቱ የኮንሶ ቀበሌዎች ብርቱ ድርቅ የተከሰተባቸው ናቸው። በዞኑ አምራች የሚባሉ ቀበሌዎች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንደገጠማቸው አቶ ጌዴኖ አስረድተዋል።
የበልግ ዝናብ "የካቲት 15 ጀምሮ ነበር መጣል የነበረበት። አንድ ወር ቆይቶ መጋቢት አስራ አራት ነው የጀመረው። ከዚያ አንድ ወር ብቻ ዘንቦ ወደ ግንቦት ሳይገባ ሚያዝያ 23 አካባቢ ነው የተቋረጠው" የሚሉት አቶ ጌዴኖ ከወይታ ዞኑ በዓመቱ ባቀደው የግብርና ምርት ላይ ጭምር ተጽዕኖ እንዳሳደረ ገልጸዋል።
በኃላፊው ማብራሪያ መሠረት በኮንሶ ዞን "በበልግ ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት" ይገኛል ተብሎ ቢታቀድም የሚሳካ አይመስልም። "አሁን የሰራንው ጥናት በድርቁ ሁኔታ ወደ 478 ሺሕ ኩንታል ምርት ብቻ እንደሚገኝ ያሳያል" ይላሉ በዞኑ ግብርና መምሪያ ሥር የሚገኘውን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት በኃላፊነት የሚመሩት አቶ ጌዴኖ። ይኸ 478 ሺሕ ኩንታል ግን መመገብ የሚችለው ኃላፊው እንደሚሉት ከዞኑ ነዋሪ 30 በመቶው ብቻ ነው። በዚህ ሳቢያ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት 70 በመቶ የኮንሶ ነዋሪ የምግብ ዋስናት እጦት ይገጥመዋል።
ከኮንሶ በተጨማሪ በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በአጠቃላይ 7.2 ሚሊዮን ሰዎች መራባቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለፈው ሚያዝያ አስታውቋል። በድርጅቱ መረጃ መሠረት ድርቅ በተከሰተባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቀንድ ከብት አልቋል። በ40 ዓመታት ከታየው ሁሉ የከፋ የተባለው ድርቅ የውኃ ምንጮች አድርቋል፤ ሰብልም ወድሟል።
በኮንሶ የበልግ ዝናብ አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር የተቆራረጠ እንደነበር የኮንሶ ልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽብሩ ሲካ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይኸ የአርሶ አደሩ ሰብል "ሙሉ በሙሉ" ማውደሙን የገለጹት አቶ ሽብሩ "በኮንሶ ዞን ሶስት ወረዳ፣ አንድ ክላስተር እና አንድ የከተማ አስተዳደር ነው ያለው። በሁሉም ቦታ ላይ ከፍተኛ ድርቅ ተከስቷል" ሲሉ አስረድተዋል።
ከኮንሶ አርሶ አደር 90 በመቶው የዝናብ ጥገኛ ነው። አቶ ጌዴኖ ከወይታ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ማሽላ፣ በቆሎ እና ጤፍ የኮንሶ ገበሬ ዋንኛ ሰብሎች ሲሆኑ 70 በመቶ ምርት የሚገኘው ከበልግ ነበር። በዞኑ "ወደ 106 ሺሕ ሔክታር መሬት ይታረሳል ብለን አቅደን ነበር" የሚሉት ኃላፊው የታረሰው ግን ወደ 96 ሺሕ ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ጌዴኖ "ከዚያ ከ96 ሺሕ ሔክታር መሬት ወደ 30 ሺሕ ሔክታር መሬት የተዘራበት ሰብል ሳይበቅል [ቀርቷል።] የበቀለውም ከበቀለ በኋላ በዝናብ ምክንያት የጠፋ አለ። በዚህ ምክንያት ብቻ ወደ 63 ሺሕ ህዝብ ይጎዳል" ሲሉ በዞኑ የምግብ ዋስትና ላይ ብርቱ ፈተና መጋረጡን አስረድተዋል።
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ከ190 ሺሕ በላይ የኮንሶ ነዋሪ ዕርዳታ ይፈልጋል
ከኮንሶ ልማት ማኅበር ለዶይቼ ቬለ በደረሱ ምስሎች በዝናብ እጦት በማሳ የደረቀ የጤፍ፣ ማሽላ እና በቆሎ ሰብል ይታያል። የዘሩት ሰብል የደረቀባቸው አርሶ አደሮች እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት የገጠማቸው ሕጻናትን ምስሎች የድርቁን ክፋት ያሳያሉ።
"ሰው በጣም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ገጥሞታል። ብዙ ሕጻናት በምግብ እጥረት እየተጎዱ ነው" የሚሉት አቶ ጌዴኖ "በዚህ አስር ወራት ውስጥ ወደ አስራ ሶስት ሕጻናት በምግብ እጥረት ምክንያት ሞተዋል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የኮንሶ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ተስፋዬ ጫሬ በተመሳሳይ በድርቁ ምክንያት አስራ ሶስት ሕጻናት መሞታቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።
የኮንሶ ዞን አስተዳደር በሰራው ጥናት በአጠቃላይ 190 ሺሕ 828 ሰዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እንዳረጋገጠ ባለሥልጣናቱ ይናገራሉ። ከዚህ ውስጥ ወደ 122 ሺሕ የሚሆኑት በድርቅ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሲሆን ወደ 53 ሺሕ 400 አካባቢ ደግሞ በአካባቢው በነበረ ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ናቸው።
"ሐብታሙም ደሐውም አርሶ አደር ምግቡን ከገበያ ነው እየሸመተ ያለው" የሚሉት አቶ ጌዴኖ የዋጋ ውድነት ሌላው የኮንሶን ነዋሪ የተፈታተነ ጉዳይ መሆኑን የበቆሎን ዋጋ በምሳሌነት ጠቅሰው ያስረዳሉ። "ባለፈው ዓመት አንድ ኩንታል በቆሎ 1 ሺሕ 500 ብር ነበር። አሁን 3 ሺሕ 500 ብር ነው" ሲሉ ተናግረዋል። የዞኑ ገበሬዎች የቀንድ ከብቶቻቸውን በመሸጥ የገጠማቸውን ተግዳሮት ለመቋቋም የሚያደርጉት ጥረትም ቢሆን መልሶ በድርቁ ዳፋ እየተሰናከለ ነው። "የድርቁ ወራት በጣም ስለተራዘመ መኖ የለም፤ ከብቶችም በጣም ነው የተጎዱት፤ ሰውነታቸው በጣም ቀንሷል። ገበያ ሲወጡ ዋጋቸው በጣም ቀንሷል" ሲሉ አቶ ጌዴኖ ተናግረዋል።
ድርቅ + ግጭት
የኮንሶዎችን ፈተና የሚያበረታው አካባቢው ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከገጠመው ደም አፋሳሽ ግጭት በቅጡ ሳያገግም፣ የተፈናቀሉ ገበሬዎችም ወደ እርሻ ማሳቸው ሳይመለሱ ከድርቅ መጋፈጡ ነው። በአካባቢው በተደጋጋሚ የተካሔደ የአወቃቀር ለውጥ ግጭቶች እየቀሰቀሰ በርካታ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፣ ንብረት ወደሟል። በ2013 ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት ከፋጬጫ ቀበሌ ያስተረፈው "ትንሽ ቀጠና" ብቻ እንደሆነ አቶ በርሻ ባቻ ያስታውሳሉ። በዚህ ዓመት በአካባቢው የተከሰተ ግጭት ወደ ቀበሌዋ ዘልቆ ባይገባም በርሻ እንደሚሉት አርሶ አደሮችን መረጋጋት ነጥቋቸዋል።
በግጭቱ ምክንያት የማጓጓዣ አገልግሎት በመቋረጡ እነ አቶ በርሻ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ገበያዎች እክል ገጥሟቸዋል። የአርባ ምንጭ ፍራፍሬ እና ደራሼን ከመሳሰሉ አካባቢዎች የሚቀርብ እህል ይሸምቱባቸው የነበሩ በአቅራቢያቸው የሚገኙ ገበያዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት እንደተስተጓጎሉ በርሻ ያስረዳሉ። "የጸጥታ ችግሩ ሲከሰት ገበያው እንደቆመ ነው። እስካሁን አልተከፈተም" ብለዋል።
በዞኑ 10 ሺሕ ሔክታር ገደማ የእርሻ ማሳ በዚሁ በጸጥታ ችግር ምክንያት ሳይታረስ እንደቀረ አቶ ጌዴኖ ከወይታ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኃላፊው እንደሚሉት በአንዳንድ ቀበሌዎች አርሶ አደሮች ጭርሱን ወደ ማሳቸው ማምራት አይችሉም።
"ሰገን ዙሪያ ወረዳ ላይ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ 44 ሺሕ ሕዝብ ከሰባት ቀበሌ ተፈናቅሏል" የሚሉት አቶ ጌዴኖ በዚህ ምክንያት ገበሬው "ማሳውን በአግባቡ አላረሰም" በማለት በግብርና ሥራ ላይ ያሳደረውን ጫና ይገልጹታል።
"ተፈናቃዮች ሁለት ተደራራቢ ችግሮች [ተጋርጠውባቸዋል።] አንደኛ ከቤቱ ተፈናቅሏል፤ ሸራ ውስጥ ነው ያለው። ሁለተኛ ደግሞ ድርቅ መጣበት። በዚያ ላይ የኑሮ ውድነት ሲጨመርበት ከፍተኛ ችግር ላይ ነው" የሚሉት የግብርና መምሪያው ባልደረባ ግጭቱ ረገብ ብሎ የተዘጉ መንገዶች ቢከፈቱም ለተፈናቀሉ ገበሬዎች ኹነኛ መፍትሔ እንዳልተገኘ ይጠቅሳሉ። "አርሶ አደሩ ቀጥታ ወደ ማሳው ሔዶ መጀመሪያ ሲሰራ የነበረውን መሥራት አልቻለም፤ ትንሽም ብትሆን የተገኘችውንም ምርት በአግባቡ መሰብሰብ አልቻለም" ብለዋል።
የኮንሶ ዞን አስተዳደር እጅ ላይ ምን አለ?
ባለፈው ዓመት የመኸር ምርት በበቂ ሁኔታ ሳይገኝ በመቅረቱ ምክንያት የኮንሶ ዞን ለ126 ሺህ የዞኑ ነዋሪዎች ዕርዳታ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቦ ለ34 ሺሕ ሰዎች ከደቡብ ክልል ማግኘቱን አቶ ጌዴኖ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሴፍቲ ኔት መርሐ-ግብር ችግር ለጠናባቸው የሚደረግ ዕገዛ ቢኖርም ከቀውሱ ብርታት አኳያ በቂ አልሆነም።
የኮንሶ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ተስፋዬ ጫሬ "አካባቢው ላይ ያለው የጸጥታ ችግር፤ አሁን የተከሰተው ረሐብ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በመሆኑ እንደ ዞን መንግሥት ይኸንን ሕዝብ መደገፍ እየቻልን አይደለም" ሲሉ ከአካባቢው አስተዳደር አቅም በላይ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት የኮንሶ ዞን አስተዳደር የሰራውን ከ190 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ለመጪዎቹ ስድስት ወራት ዕርዳታ እንደሚያሻቸው የሚያሳስብ ጥናት ለደቡብ ክልል፣ ለፌድራል መንግሥት እና ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች በማቅረብ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። "ከዚያ ውጪ እንደ ዞን መንግሥት እኛ ምንም እጃችን ላይ ያለ ነገር የለም" ሲሉ አቶ ተስፋዬ ጫሬ ገልጸዋል።
ድርቅ እና የግጭት ዳፋ የበረታባቸው የኮንሶ ነዋሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ዕርዳታ የማግኘታቸው ጉዳይ የኮንሶ ልማት ማኅበርን የሚመሩት አቶ ሽብሩ ሲካን የሚያሳስብ ነው። "አሁን ባለው ደረጃ በምግብ እጥረት እስከ ሞት ድረስ እየሔዱ ያሉ ወገኖች አሉ። ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ በርካታ ሕጻናት በጤና ተቋማት ውስጥ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። እነሱም ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ የመሞት ዕድላቸው ሰፊ ነው" ሲሉ አቶ ሽብሩ ሲካ ሥጋት የተጫነው አስተያየት ሰጥተዋል። አቶ ሽብሩ "ነፍሰ ጡር እና አጥቢ እናቶች፣ አረጋውያን እና አቅም የሌላቸው ወገኖች ሰለባ እየሆኑ ነው። መንግሥት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቶሎ ካልደረሱ ያ ህብረተሰብ ለወደፊት የሚገጥመው አደጋ ቀላል አይሆንም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ