1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካእስያ

ጀርመን አካባቢውን ለማረጋጋት የግብጽን ድጋፍ ትሻለች

ሐሙስ፣ ጥቅምት 8 2016

የጀርመን መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ የታገቱ እሥራኤላውያን ስለሚለቀቁበት እና ፍልስጥኤማውያን ሰብአዊ ድጋፍ ስለሚያገኙበት ጉዳይም ከግብጽ ፕሬዚደንት አል-ሲሲ ጋ መክረዋል ። ጋዛ ሠርጥ ውስጥ ግዙፍ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ ሕይወታቸውን ላጡ ጥልቅ ሐዘናቸውን ገልጸው ክስተቱ በሚገባ እንደሚመረመር ገልጸዋል ።

https://p.dw.com/p/4Xirc
የጀርመን መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ የግብጽ ፕሬዚደንት አል-ሲሲ ጋ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ የእሥራኤል ሐማስ ጦርነትን ስለሚረግብበት ጉዳይ በተመለከተ ከግብጽ ፕሬዚደንት አል-ሲሲ ጋ መክረዋል ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ዖላፍ ሾልትስ ከቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋርም ተወያይተዋል

በእሥራኤል እና በሐማስ መካከል ያለውን ግጭት ለማርገብ ጀርመን የግብጽ ድጋፍን እንደምትሻ መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ ዐስታውቀዋል ። መራኄ መንግሥቱ ጋዛ ሠርጥ ውስጥ ግዙፍ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ ሕይወታቸውን ላጡ ጥልቅ ሐዘናቸውን ገልጸው ክስተቱ በሚገባ እንደሚመረመር ገልጸዋል ። የታገቱ እሥራኤላውያን ስለሚለቀቁበት እና ፍልስጥኤማውያን ሰብአዊ ድጋፍ ስለሚያገኙበት ጉዳይም ከግብጽ ፕሬዚደንት አል-ሲሲ ጋ መክረዋል ። እሥራኤል በጋዛ በኩል ግብጽ የተወሰነ ሰብአዊ ድጋፍ እንድታጓጉዝ ፈቅዳለች ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የእሥራኤል ጦር የፍልስጥኤም ይዞታዎችን መደብደቡን እንደቀጠለ ነው ።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ በእሥራኤል እና ጋዛ ስላለው ሁኔታ ለመምከር ግብጽ ያቀኑት ትናንት ነበር ። እዚያም ከግብጽ ፕሬዚደንት አል-ሲሲ ጋ በጉዳዩ ተወያይተዋል ። ማክሰኞ ማምሻውን በጋዛ ግዙፍ ሆስፒታል ላይ የደረሰው ፍንዳታ የበርካቶችን ሕይወት በመቅጠፉ ከልብ ማዘናቸውን፤ ጥልቅ ምርመራ እንደሚደረግም ተናግረዋል ።

«ጋዛ ሰርጥ ውስጥ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እጅግ አስደንጋጭ ፍንዳታ ግዙፍ ሆስፒታል ላይ የመከሰቱን ዜና ትናንት ሰምተናል በትክክል ምን እንደሆነ እስካሁን ዐላወቅንም ይህ ክስተት በጥልቀት እንደሚመረመር ማወቁ ጠቃሚ ነው ለጉዳቱ ሰለቦች ቤተሰቦች እና የመቁሰል አደጋ ለደረሰባቸው ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን ሕይወታቸውን ስላጡት ሁሉ ጥልቅ ሐዘን ይሰማናል »

በአሜሪካ፣ በአውሮጳ ኅብረት፣ በጀርመን እና በሌሎች «አሸባሪ ድርጅት» በሚል የተሰየመው ሐማስ እና እሥራኤል በማክሰኞው ፍንዳታ እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ነው ። በአካባቢው ለደረሰው ምስቅልቅል ሁኔታ ተጠያቂው ሐማስ መሆኑንም መራኄ መንግስቱ አስረግጠው ተናግረዋል ።

«ሆኖም ይህ ክስተት ግልጽ ያደረገው የነበረው፦ ሐማስ በመስከረም 26 በፈጸመው ሰቅጣጭ የሽብር ጥቃት በእሥራኤል ዜጎች ላይ ብርቱ ስቃይ መድረሱ፤ በውጤቱም በጋዛ ነዋሪዎች የበለጠ መከራ መከተሉ ነበር »

ጥቃቱን በመቃወም በተለያዩ ሃገራት ሰልፎች ተካሂደዋል። በግብጽ የተለያዩ ከተሞች፤ እንዲሁም በዮርዳኖስ እና በቱኒዚያ በእስራኤል ኤምባሲ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፎች መደረጋቸውን፤ በፍልስጤም በምዕራባዊ የዮርዳኖስ ዳርቻም እንዲሁ በርካቶች ለተቃውሞ ሰልፍ መውጣታቸው ተዘግቧል።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ የግብጽ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ጋ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ ግብጽ ውስጥ ከ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ጋ መግለጫ ሲሰጡምስል Michael Kappeler/dpa/picrture alliance

መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ፦ ግብጽ በአካባቢው በእሥራኤል እና በሐማስ መካከል ያየለውን ውጥረት በማርገብ ረገድ ጥረቷን ጀርመን እንደምትፈልግ ተናግረዋል ።

«አሁንም በድጋሚ ግጭቱን ለማርገብ እና ለማወያየት እናንት ግብጻውያን እየጣራችሁ ነው በዚህ ረገድ ጀርመን ልትደግፋችሁ ትሻለች ጥረቱ በሐማስ ተጠልፈው ስለታገቱት እጣ ፈንታ ጭምር የሚመለከት ነው የመለቀቃቸውን ጉዳይ አስተማማኝ ለማድረግ በተቻለ መጠን እየጣርን ነው በዚህ ጉዳይም ተነጋግረናል »

መራኄ መንግሥቱ ትናንት ከግብጽ አቻቸው አል ሲሲ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፦በጋዛ ስላለው ሰብአዊ ሁኔታም መክረዋል ።  በተቻለ ፍጥነትም በግብጽ በኩል የሰብአዊ ርዳታ መተላለፊያ እንዲከፈት ጠይቀዋል ። አል ሲሲ በበኩላቸው ግብፅ በራፋህ በኩል ያለውን ድንበሯን አለመዝጋቷን ዐስታውቀዋል ። በዚህ ድንበር በኩል ሰሞኑን የተሽከርካሪ ቅፍለቶች ማለፍ ያልቻሉት አካባቢው በቦንብ ስለተደበደበ ነው ብለዋል። ፍልስጥኤማውያን ከጋዛ ተባረው ወደ ሲናይ በረሃ መላክ የለባቸውም ሲሊም ፕሬዚደንቱ አክለዋል ። እንዲያ ከሆነ አካባቢው በምድር እሥራኤል ላይ «የሽብር ጥቃት» የሚወነጨፍበት ሊሆንም ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል ። ግጭቱ እስኪረግብ ድረስም እሥራኤል ፍልስጥኤማውያንን ወደ ኔጌቭ በረሃ ልታጓጉዝ ትችላለች ብለዋል ።

የግብጽ እና ጋዛ ድንበር አካባቢ
የግብጽ እና ጋዛ ድንበር አካባቢ የርዳታ ተሽከርካሪዎች ተደርድረው ሠራተኞች በተጠንቀቅ እንደቆሙምስል REUTERS

«እሥራኤል ውስጥ የኔጌቭ በረሀ አለ እነሱ [እሥራኤሎች]ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ሐማስ ወይንም ሌሎች ቡድኖች ላይ የሚፈልጉትን ወታደራዊ ዘመቻ እስኪተገብሩና [ፍልስጥኤማውያን] እስኪመለሱ ድረስ ፍልስጥኤማውያን ወደ ኔጌቭ በረሀ ሊጓጓዙ ይችላሉ »

መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ ወደ ግብጽ ከማቅናታቸው አስቀድሞ እሥራኤል በመገኘት ከጠቅላይ ሚንሥትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋር ተወያይተዋል ።  በሐማስ የተሰነዘረውን የሽብር ጥቃትም አውግዘዋል ። «እሥራኤል ራሷን ከዚህ የሽብር ጥቃት ለመከላከልም መብት አላት » ብለዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti