1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችሰሜን አሜሪካ

ፕሬዚዳንት ባይደን ለአሜሪካውያን ያደረጉት ንግግርና የትራምፕ መልዕክት

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2016

ፕሬዚደንት ጆሴፍ ባይደን፣ አሜሪካዊያን በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዚደንቱ ትናንት ከነጩ ቤተመንግሥት ጽሕፈት ቤታቸው ለሕዝቡ ባደረጉት ንግግር፣ የፖለቲካ ልዩነት ወደ ጥላቻ ማምራት እንደሌለበት አስገንዝበዋል። ከግድያ ሙከራ የተረፉት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፣ በማኀበራዊ መገናኛ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

https://p.dw.com/p/4iJcA
የዩናይትድ ስቱትስ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ባይደን
የዩናይትድ ስቱትስ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ባይደንምስል Erin Schaff/REUTERS

የትራንፕ የግድያ ሙከራና አሜሪካ

 

በቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተካሄደውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ፣ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን ከነጩ ቤተመንግሥት ቢሯቸው ትናንት ማታ ለአሜሪካዊያን ንግግር አድርገዋል።

የደህንነት ተቋሙ ምርመራ 

ፕሬዚዳንት ባይደን በዚሁ ንግግራቸው፣ የግድያ ሙከራውን በተመለከተ፣ የሀገሪቱ የደህንነት ተቋም ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የግድያ ሙከራውን በድጋሚ ያወገዙት ባይደን፣ ሀገራዊ አንድነት እንዲኖር ጠይቀዋል። « ዛሬ ማታ ልነግራችሁ የምፈልገው፣ በፖለቲካችን ውስጥ ያለውን መጋጋል ማብረድ እንዳለብንና ባንስማማ እንኳን ጠላቶች አለመሆናችንን እንድናስታውስ ነው፤ በአንድነት መቆም አለብን።»

ፕሬዚዳንቱ፣ትራምፕ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም፣እንደ ሀገር ያለን ማንነት አይደለም ብለዋል።

የምርጫ ሳጥን ፖለቲካ

«አሜሪካ ውስጥ ልዩነታችንን የምንፈታው በጥይት ሳይሆን በምርጫ ሳጥን ነው። እንደእዛ ነው የምናደርገው፣ አሜሪካን የመለወጥ ኀይል ሁልጊዜ በሰዎች እጅ መቀመጥ አለበት እንጂ በነፍሰ ገዳይ መሆን የለበትም።»

ይሁንና፣ ፕሬዝዳንቱ በትናንት ምሽት ንግግራቸው ወቅት፣ በቅርብ ጊዜ እየፈጸሙ ያሉትን ስህተቶች እና የንግግር መደነቃቀፍ በመድገም፣ የምርጫ ሣጥን የሚለውን የጦርነት ሣጥን በማለት ሁለት ጊዜ ሲጠሩት ተደምጠዋል።

በጉዳዮች ላይ የሚካሄድ ክርክር ሁልጊዜ ሰላማዊ መሆን እንዳለበት ያሳስቡት ፕሬዚዳንቱ፣ ፖለቲካ በፍጹም የጦር አውድማ ወይም የግድያ ሜዳ መሆን የለበትም ብለዋል።

ዶናልድ ትራንፕ
ከግድያ ጥቃት የተረፉት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንትና የዘንድሮው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዋነኛ ተፎካካሪ ዶናልድ ትራንፕምስል Evan Vucci/AP Photos/picture alliance

የትራምፕ የማኀበራዊ ሚዲያ መልዕክት

 የፕሬዚደንቱ ንግግር ከተጠናቀቀ ከሦስት ደቂቃ በኋላ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ«ሶሻል ትሩዝ» በተባለው የማኀበራዊ መገናኛ ገጻቸው ከባይደን ጋር የሚመሳሰል መልዕክት አጋርተዋል።ትራምፕ፣ «በአሁኑ ጊዜ በአንድነት መቆም እና እውነተኛ ባህሪያችንን እንደ አሜሪካዊያን ማሳየት ይገባናል።» ነው ያሉት። አክለውም፣ «ጠንካራ እና ቆራጥ ሆነን መቆየታችንና ክፋት እንዲያሸንፍ አለመፍቀድ፣ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው።»ሲሉ ጽፈዋል።

ስለግድያ ሙከራው የተሰጡ ምላሾች

ትራምፕ፣ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ የተፈፀመባቸውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ፣ እዚህ አሜሪካ፣ከሪፐብሊካንና ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪዎችና አባላት አንስቶ እስከ ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ፣ ስለ ድርጊቱ አስደንጋጭነት እንዲሁም ትራምፕ ከጥቃቱ በመትረፋቸው የተረማቸውን እፎይታ እየገለጹ ነው። የሁለቱም ፓርቲ ሕግ አውጪዎች በጥቃቱ ላይ አጠቃላይ ምርመራ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።

 የቀድሞዎቹ ፕሬዝዳንቶች፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እና ባራክ ኦባማን ጨምሮ፣ የቀድሞ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ባለሥልጣናት፣ የጸጥታና የደኅንነት መሥሪያ ቤቶችን ፈጣን እርምጃ አድንቀዋል። የትራምፕ የበኩር ልጅ የሆነው፣ ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር፣ አባቱን በስልክ ማነጋገሩንና በጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ እና የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በበኩላቸው፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ፈጥነው እንዲያገግሙ ተመኝተውላቸዋል።

ታሪኩ ኃይሉ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ