ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ድጋፍ
ረቡዕ፣ ሰኔ 21 2015ሰዎች ለሰዎች ድርጅት (Menschen fuer Menschen) በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአፋር እና አማራ ክልሎች ውድመት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የሚሆን የ 60 ሚሊዮን ብር የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። በጀርመን እና ኦስትሪያ ሕዝቦችና መንግሥታት የሚደገፈው ሰዎች ለሰዎች ግብረ ሠናይ ድርጅት የሰጠው ድጋፍ በአፋር እና አማራ ክልሎች ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የሚያገለግሉ የጽኑእ ሕሙማን ማከሚያ ማሽኖችን ጨምሮ የማዋለጃ መሣሪያዎችን፣ የህሙማን መመርመርያ ቁሳቁሶችን እና የቤተ ሙከራ እቃዎችንም ያካተተ ነው ተብሏል ።
ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ፣ በደቡብ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ድርቅ ላስከተሉት ሁሉን አቀፍ ቀውስ ምላሽ የሚሆን የ250 ሚሊዮን ብር የዕለት ደራሽ እርዳታ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ማገዙን አስታውቋል።
የዛሬውም ድጋፍ የወደሙ የጤና ተቋማት ሕዝብን በተሻለ እንዲያገለግሉ የሚያስችሉ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ልያ ታደሰ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ዐዎር የዛሬው ድጋፍ የጀርመን ፌዴራል መንግስት እና ነፃው የባቫርያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ጠንካራ ድጋፍ ጥሩ ዐብነት ነው ብለዋል።
"የዛሬው የርክክብ ሥነ ሥርዓት የጀርመን ፌዴራላዊ መንግሥት እና የነፃው የባቫሪ ግዛት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የማያወላዳ ቁርጠኛ ድጋፍ ጠንካራ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የማገገም እና የተሻሻለ የጤና አገልግሎት ለመገንበት መንገድ ሲጀምር እኛ እርዳታ እና ድጋፍ በማድረግ በጠንካራ አጋርነት ቆመናል።"
የህክምና ቁሳቁሶችን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር፣ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው የጀርመን መንግሥት የልማት እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊ እንዲሁም የባቫሪያ ግዛት ተወካዮች ለኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ልያ ታደሰ ዛሬ ያስረከቡ ሲሆን ድጋፉ ለትግራይ ክልልም ይቀጥላል ተብሏል። የሰዎች ለሰዎች ድርጅት አምባሳደር አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እቃዎቹ ለብክነትም ሆነ ለሌላ ዙር ጉዳት እንዳይጋለጡ አደራ ብሏል።
በበጎ አድራጊው ካርል ኸንዝ በም ከ 41 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ሰዎች ለሰዎች ድርጅት እስካሁን በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ውስጥ የ 8.5 ቢሊዮን ብር የልማት ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል።በበጎ አድራጊው ካርል ኸንዝ በም ከ 41 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ሰዎች ለሰዎች ድርጅት እስካሁን በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ውስጥ የ 8.5 ቢሊዮን ብር የልማት ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ