በራስ ሀገር ዜጎች የሚደርስ በደል በሳዑዲ አረቢያ
ዓርብ፣ ሐምሌ 28 2015«በወገኖቼ ላይ እየደረሰ ያለው ነገር በጣም ያሳዝነኛል። ስሜታዊ ያደርገኛል» ትላለች ሣባ ገብረ ሥላሴ ። በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ የምትኖር በጎ ፍቃደኛ ናት። በተለይ ሴት ኢትዮጵያውን ላይ ስለሚፈፀም በደል በቅርበት ከተጎጂዎቹ ጋር ትወያያለች፣ ትረዳቸዋለች። « ከኢትዮጵያ ተነስተው እዚህ እስኪደርሱ ነገሮችን የሚጨርሱት በደላላ ነው። እነዚህ እህቶቻችን ምንም አይነት መረጃ የላቸውም። ችግር በሚደርስባቸው ሰዓት ግን ማንም የሚረዳቸው ሰው የለም። በቅርብ ጊዜ እንኳን የካንሰር፣ የኩላሊት በሽተኛ፣ የHIV በሽተኛ በእጃችን አሉ። » በማለት አሳሳቢነቱን ታብራራለች።
ከምንም በላይ ሣባን የሚያሳዝናት ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ በገዛ ወገኖቻቸው በደል ስለሚፈፀምባቸው ነው። « እኔ አሁን ባለፈው ሳምንት የደረሰኝ ጎረቤት የሆነ ሰው ነው ምንም የማታውቅ ልጅ አፍኖ የደፈራት። ወንድሞቻችን ናቸው የገዛ እህቶቻችንን እየጎዱ ያሉት። ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እህቶቻችን እየጠፉ ነው። አስጠፊዎቹም የራሳችን ወንድሞች ናቸው። የሳዑዲ ህግ ማስረጃ ይዞ የሚያቀርበው ነገር ለኃላፊዎቻችን አንገት የሚያስደፋ ነው። »
እነዚህ ደላሎች ለየትኛው የሕግ አካል ነው የሚቀርቡት?
እንደ ሣባ አገላለጽ ሕግን አክብረው ለሚንቀሳቀሱ ሳዑዲ አረቢያ በተለይ ለሴቶች ክብር ያላት ሀገር ናት። ስለሆነም እነዚህን ሰዎች ለሳዑዲ አሳልፎ ቢሰጥ ርምጃ ይወሰድባቸው ነገር። ግን ሣባን አንድ የሚረብሻት ነገር አለ። « ዜጋን አሳልፎ መስጠት ይሆናል። ኤምባሲው ግን ይህንን ነገር ተከታትሎ በሀገራቸው የሚቀጡበት መንገድ ቢደረግ፤ አንድ ሁሉት ሶስት ላይ ጠንከር ያለ ርምጃ ቢወሰድ ማንም ወደዛ ደግሞ አይሰማራም ነበር። » በማለት ሣባ በቅርብ ጊዜ የሆነ ምሳሌ ትጠቅሳለች።
በሳኡዲ የኢትዮጵያውያን ስሞታ
ላለፉት 12 ዓመታት በበጎ ፍቃደኝነት የምትሰራው ሣባ መፍትሔ ነው የምትለው ማኅበረሰቡ እንዲጠናከር ሲደረግ እና እንደ የሴቶች እና ወጣቶች የመሣሰሉ ማኅበራት ሲቋቋሙ ነው። ያኔም እንደ ሣባ ያሉ በጎ ፍቃደኞች ተጠናክረው የበለጠ መሥራት እንደሚችሉ ሣባ ታምናለች።« ህብረተሰቡ ደግ ነው። ማህበራዊ ኑሮውን እዚህም አልተወውም። ገንዘብ ያዋጣሉ። » ችግሩ ግን እሷ እንደምትለው በመሀል የሚገቡ ደላሎች ማህበረሰቡን ይጠቀምበታል።
ሣባ ይህንን የምትሠራው በትርፍ ሰዓቷ ነው። ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ ያገለግላል ትላለች። ይሁንና ተረጂዎቹ የእነዚህ በጎ ፍቃደኞች ሰዓት እስኪመቻች መጠበቅ ግድ « እነዛ በሽተኞች ከስራ እስክምመለስ ጠብቀው ማታ ነው ወደ ሆስፒታል የምንወስዳቸው። እኛ የምናግዘው ከመቶ 1 ቢሆን ነው እኛ የምናግዘው። ይህንን እያደረግን ይዝቱብናል። ሂጅና ለጀርመን ሬዲዮ ተናገሪ፤ ሚዲያ ላይ አውጪው እያሉ የሚዝቱብኝ አሉ። ከዲፕሎማት ደረጃ እንደዚህ አይነት ዛቻ መጥቶብኛል።» ትላለች።
ሣባ በምታነሳቸው እና ኤምባሲውን በሚመለከቱ ወቀሳዎች ላይ ሳዑዲ አረቢያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም። ለጉዳይ እስር ቤት እንደሚገኙ እና መልሰን ቆየት ብለን እንድንደውል የነገሩን የኤምባሲው ጉዳይ አስፈፃሚ አቶ አህመድ ሙክታር በነገሩን መሠረት ደጋግመን ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።
ሣባ ረቡዕ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ ጉዳይ ተወካዮችን አግኝታ መወያየቷን እና ችግሩን እንዳስረዳቻቸው ገልፃልናለች። በውይይቱም ላይ የተገኘሁ ብቸኛ ሴት እኔ ነበርኩ ትላለች። « ይኼንን መቅረፍ የሚቻለው ሴት እህቶቻችን ምን ያህል ናቸው ? የት ነው የሚኖሩት? እነ ማን ናቸው የሚለው በሰፊው ኤምባሲው መስራት የሚችለው ነገር ነው። »
ሌላው በርካቶች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መግባታቸው እና የተማሩ አለመሆናቸው ችግራቸውን ኤምባሲ ቀርበው እንዳይፈቱ ያለ ሌላ ፈተና ነው። ስለሆነም ልናግዛቸው ይገባል ትላለች ሣባ።« ችግራቸውን እንኳን በማመልከቻ ፅፈው መግባት የማይችሉ ናቸው። ከሳምንት በፊት የገጠመችኝ አንዲት እህት ኤምባሲ ስትገባ እጇ ይንቀጠቀጥ ነበር» በማለት ሣባ ፈተናዎቹን ታብራራለች።
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ