1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት ውሎ እና የቀረቡ አዳዲስ ረቂቅ ሕጎች

ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2016

ረቂቅ አዋጁ "ሽብርተኝነትን እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የኢኮኖሚ ደህንነት ሥጋት ብቻ ሳይሆን፤ የፋይናንስ ሥርዓቱን የሚያናጋ ወንጀል በመሆኑ" ይህንን ለመከላከል መዘጋጀቱ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4gvQT
ምክር ቤቱ ዛሬ የሕዝብና የኃይማኖታዊ በዓላት አከባበር ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገዉ መደበኛ ሥብሰባዉ በተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተነጋግሯልምስል Solomon Muchie/DW

የምክር ቤት ውሎ እና የቀረቡ አዳዲስ ረቂቅ ሕጎች

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ" ረቂቅ አዋጅ ለውይይት ቀርቧል።ረቂቅ አዋጁ "ሽብርተኝነትን እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የኢኮኖሚ ደህንነት ሥጋት ብቻ ሳይሆን የፋይናንስ ሥርዓቱን የሚያናጋ ወንጀል በመሆኑ" ያንን ታሳቢ ተደርጎ መቅረቡ ተገልጿል።

ምክር ቤቱ "የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን እና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል" የተባለለት ሌላ "የንብረት ማስመለስ አዋጅ" ረቂቅም ቀርቦለት ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፣ ለ2017 በጀት ዓመት 971.2 ቢሊዮን ብር ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውን የበጀት መግለጫም አድምጦ ውይይት አድርጓል።//

ለምክር ቤቱ የቀረቡለት አዳዲስ ረቂቅ አዋጆች

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በዋለው መደበኛ ጉባኤው ከተመለከታቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል "በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ አዋጅ" አንደኛው ነው። ረቂቅ አዋጁ "ሽብርተኝነትን እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የኢኮኖሚ ደህንነት ሥጋት ብቻ ሳይሆን፤ የፋይናንስ ሥርዓቱን የሚያናጋ ወንጀል በመሆኑ" ይህንን ለመከላከል መዘጋጀቱ ተገልጿል። የመሰል ወንጀሎችን ምርመራ በተመለከተ ረቂቅ አዋጁ "አስቸኳይ ሁኔታ ባጋጠመ ጊዜ መርማሪው አካል የዐቃቤ ሕግ የበላይ ኃላፊ ሲፈቅድ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የወንጀል ፍሬን ተከታትሎ ለመለየት በባንክ ሒሳቦች እና በሌሎች ተመሳሳይ ሒሳቦች ላይ ክትትል ለማድረግ፣ የኮምፒውተር መረቦችን እና ሰርቨሮችን ለመለየት፣ መገናኛዎችን በክትትል ሥር ለማዋል ወይም ለመጥለፍ ፣ የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ እና ለመያዝ" እንዲችል መርማሪ ተብሎ ለተገለፀው አካል ሥልጣን ይሰጣል።

ለምክር ቤቱ የቀረበው ሌላኛው ረቂቅ አዋጅ "የንብረት ማስመለስ አዋጅ" ሲሆን ይሄው አዋጁ "የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን እና ገንዘቦችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመያዝ፣ ለማገድ፣ ለመውረስ ወይም ለማስተዳደር የሚያስችል ግልጽ እና ዝርዝር የሕግ ማእቀፍ በማበጀት፤ ማንም ሰው ከሕገ ወጥ ድርጊት ማናቸውንም አይነት የኢኮኖሚ ጥቅም እንዳያገኝ ለማድረግ" ያለመ ሆኖ የተዘጋጀ ነው ተብሏል። እነዚህ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታችፕው ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርተዋል።

የሕዝብ በዓላት አከባበር አዋጅ 

 

ምክር ቤቱ ሌላው መርምሮ ያፀደቀው የሕዝብ በዓላትን ተከብረው እና ታስበው የሚውሉ በሚል የከፈለበት እንዲሁም ሃይማኖታዊ በዓላትን ያተተበት አዋጅ ነው። ተከብረው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት መደበኛ ሥራ ዝግ የሚሆንባቸው ቀናት ሲሆን እነዚህም የዘመን መለወጫ - እንቁጣጣሽ፣ የአድዋ ድል፣ የሠራተኞች እንዲሁም የአርበኞች የድል ቀን ናቸው። የየካቲት 12ቱ የሰማዕታት ቀን፣ ሕዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሥራ ሳይዘጋ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ታስበው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት ሆነው ፀድቋል።

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የሕዝብና የኃይማኖታዊ በዓላት አከባበርን የሚደነግግ አዋጅ አፅድቋል
የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስብሰባ ላይ-አዲስ አበባምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

ከቅርብ አመታት ወዲህ በአድዋ ድል አከባበር ከሚያዙ ሰንደቅ አላማዎች፣ አርማዎች፣ የበዓሉ ማክበሪያ ቦታዎች ጋር ተያይዞ ውዝግቦች እየተነሱ ሰዎችን ለሞት ፣ ለአካል ጉዳትና ለእሥር የዳረጉ ውዝግቦች ተስተውለዋል።

ምንም እንኳን በሕግ የተደገፈ ባይሆንም ሥራም ሆነ መደበኛ ትምህርት ዝግ ሆኖ በድምቀት ሲከበር የነበረው ግንቦት 20፣ በፀደቀው አዋጅየሚከበርም ሆነ የሚታሰብ በዓላት ዝርዝር ውጭ ሆኗል። የአዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ የጤና ፣ ማህበራዊ ልማት ፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ገልፀዋል።

ሃይማኖትን በተመለከተው የአዋጁ ድንጋጌ ውስጥ አምስት የክርስትና እንዲሁም ሦስት የእስልምና እምነት ክብረ በዓላት ተካትተዋል። መስቀል፣ ገና ፣ ጥምቀት፣ ስቅለት እና ትንሳኤ ወይም ፋሲካ በአዋጁ የተካተቱ የክርስትና እምነት በዓላት ሲሆኑ የኢድ-አልአድሃ ወይም አረፋ፣ የመውሊድ እና የኢድ-አልፈጥር በዓላት ከእሥልምና ሃይማኖት የተካተቱ በዓላት ናቸው። 

ክብረ በዓላቱ በውጭ ሀገር የሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ወይም ቆንስላዎች ውስጥም እንደሚያከሩ ተደንግጓል።

 

2017 . በጀት

በሌላ በኩል ለ2017 ዓ. ም የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት በጀት የበጀት መግለጫ በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ከቀትር በኃላ ቀርቧል። 971.2 ቢሊዮን ብር ሆኖ የቀረበው በጀት ውስጥ 612 ቢሊዮን ብር ከግብር እና ግብር ነክ ካልሆኑ ምንጮች የሚሰበሰብ ሲሆን 358 ቢሊዮን ብር ያህሉ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በሚገኝ ብድር የሚሸፈን የበጀት ጉድለት ያለው ነው። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በ2017 ዓ. ም 8.4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚኖር ገልፀዋል። የውጭ እዳ ክምችት መቀነሱ፣ ሆኖም ግን ሥጋትነቱ መቀጠሉ ተገልጿል። 20 ቢሊዮን ብር በጦርነት የወደሙትን መልሶ ለመገንባት እንደሚውል ተብራርቷል።

የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ከተደረገ ረጅም አመታት የተቆጠረባት ኢትዮጵያ በአዲስ የበጀት ድልድል ውስጥ የገቡ ሁለት ክልሎች የፌደሬሽኑ አካል ሆነው ድልድሉ ውስጥ ተካተዋል። ከአንድ የምክር ቤት አባል ይህ የበጀት ድልድል "በየትኛው ቀመር የተሰራ ነው"፣ በምን ተጨባጭ ሁኔታ የተጠና እና የታየ ነው? የሚሉ ጥያቃዎች ቀርበዋል።በጀቱ በቀጣዩ አንድ ወር ውይይት ከተደረገበት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙበት የምክር ቤቱ ጉባኤ  ይፀድቃል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ