1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

ረመዳን በጦርነት በታመሰችው ሱዳን

ቅዳሜ፣ መጋቢት 21 2016

ወቅቱ የጾም ነው። በዚህ ዓመት የአብዛኛው ቤተእምነት ጾም ገጥሟል። እንደ ዐብይ ጾም እና ረመዳን። ለ30 ቀናት የሚዘልቀው የሙስሊሞች ጾም በጦርነት ውስጥ ከገባች ዓመት ሊሞላት ቀናት በቀሯት ሱዳን ለአብዛኞቹ ፈታኝ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/4eGLT
ሱዳን ዑምዱማን
በሱዳን ጦርነት ያደበዘዘው የረመዳን ጾም ምስል ohamed Khidir/Xinhua/picture alliance

ረመዳን በሱዳን

 

በመንግሥት ወታደሮች እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል ባለፈው ዓመት ረመዳን ወቅት የተቀሰቀሰው ውጊያ እስካሁን ከ8,5 ሚሊየን በላይ ሕዝብን ከቤት ንብረቱ አፈናቅሏል። በአሁኑ ጊዜም በሱዳን 18 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ ለከፋ ረሃብ መጋለጡ እየተነገረ ነው። በዚህም ምክንያት የዘንድሮውን የረመዳን ወቅት ከዚህ በፊት ኅብረተሰቡ በለመደው መልኩ ጾሙን እየጾመና እያፈጠረ እንዳልሆነ ነው በጦርነቱ ምክንያት ያላቸውን አጥተው የሰው እጅ ለመመልከት የተገደዱት ሱዳናውያንየሚገልጹት። የእርስ በእርስ ጦርነቱ ካፈናቀላቸው አንዱ የፊልም ዳይሬክተር የሆኑት መሀመድ አሊ ናቸው።

«ረመዳን ፍጹም ተለውጧል ማለት እንችላለን፤ የሕዝቡ ስነልቡና ውቅር ተለውጧል። የኖርንበት ልማድ ሁሉ፤ አመጋገባችን፤ የምንጠጣው፤ በረመዳን ሰዎችን ማግኘቱ፤ እንዲሁም ለረመዳን ማቀድ ሁሉ አሁን የለም። ገቢ ለማግኘት ከቀናት በአንዱ ሥራ እንደምንሠራው ረመዳንንም ከአለፍ አገደም እኖርነው ነው፤ ሆኖም ይህ አያስቸግርም። ችግሩ፤ በፊት ለብዙ ሰዎች እንደርስ ነበር፤ እንጠይቃቸው ነበር፤ ያለን ትንሽ እንኳ ቢሆን ለሌሎች እናጋራ እንሰጥ ነበር፤ አሁን እኛ እራሳችን እርዳታ ፈላጊ ሆነናል።»

የረመዳን አጥር 

መሀመድ አሊ አሁን የሚገኙበት ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ነው የሚገልጹት። ዕጣ ፈንታቸውንም ፈጣሪ ላይ ከመጣል እና ተስፋ ከማድረግ ባለፈ የሚገኙበት ሁኔታ እንደወትሮው አይደለም ነው የሚሉት። ረመዳን በተጀመረበት ዕለት ብዙዎቹ በያሉበት አካባቢ በመሰባሰብ በጋራ አፍጥረዋል። አሁን እሳቸውም ሆኑ ሌሎች በሚሊየኖች የሚቆጠሩት ሱዳናውያን በበጎ ፈቃድ ለጾም መፍቻ የሚያቀርቡላቸውን ምግብ ከመጠበቅ የተለየ አማራጭ የላቸውም። ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰው ጦርነት የሱዳናውያንን ደግነት እና እንግዳ ተቀባይነት በእጅጉ ፈትኖታል።  ምንም እንኳን ጦርነቱ ጥሪታቸውን ቢያሟጥጠውም አሁንም በሮቻቸውን በሌሎች ላይ ለመዝጋት ያቃታቸውና ከልገሳቸው ያልተገቱ እንዳሉ ነው የዑንዱርማን ከተማው ኢማም ሸክ ካህሊድ አብዱራህማም የሚናገሩት። ምንም እንኳን ጦርነቱ አንዳንዶቹ ከአካባቢው ቢሰደዱም ውጊያውን ተቋቁመው በአካባቢው የቀሩት ለጎደለባቸው ወገኖቻቸው ያላቸውን ለማካፈል በሰሞኑ የጾም ቀናት በየጎዳናው የጋራ የአፍጥር መርሃግብር እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን አዳሪፍ የስደተኞች መጠለያ
በመንግሥት ወታደሮች እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል ባለፈው ዓመት ረመዳን ወቅት የተቀሰቀሰው ውጊያ እስካሁን ከ8,5 ሚሊየን በላይ ሕዝብን ከቤት ንብረቱ አፈናቅሏል። ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን አዳሪፍ የስደተኞች መጠለያምስል -/AFP/Getty Images

ጦርነቱ በሁሉም ኑሮ ላይ ጫና ቢያሳድርም በዚሁ ምክንያት ከቤት ንብረቷ የተፈናቀለችው ሱዳናዊት ተዋናይ አሚር ኢድሪስ ለመጪው ረመዳን የተሻለ ጊዜ ይመጣል በሚል ተስፋ የዘንድሮውን በለጋሾች ድጋፍ እየጾመች ነው።

«ለሚመጣው ረመዳን ወደ ቤታችን እንመለሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እርግጥ ነው በረመዳን ጊዜ በፊት የለመድናቸውን ብዙ ነገሮች አጥተናል፤ ግን ፈጣሪ ይመስገን፤ የእርዳታ ድርጅቶች አሉ። በ30 ዎቹ የረመዳን ቀናት ለእኛ የአፍጥር ምግብ መድበውልናል። ጥሩ ምግብ ለአፍጥር ያቀርቡልናል አገልግሎታቸውም ግሩም ነው። በዚህ ደስተኛ ነኝ በዚህ ሁኑታ ውስጥ እኛን ስለረዱን እናመሰግናቸዋለን። ምስጋና ይድረሳቸው።»

ተስፋ ያጣው የተኩስ አቁም ስምምነት

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች አንዳቸው በሌላቸው ላይ የበላይነት ለማግኘት በውጊያው ቀጥለዋል። የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት በረመዳን ወቅት ተኩስ እንዲያቆሙ አሳስቦ ነበር። ጾሙ ከመጀመሩ አስቀድሞ የሱዳንን ጦር ኃይል ከሚመሩት አንደኛው ጀነራል ፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሣሪያውን ሳያስቀምጥ በረመዳን ተኩስ አይቆምም ብለዋል። ከዋና ከተማ ኻርቱም ቀጥሎ ዋነኛ የሁለቱ ኃይሎች የጦር ሜዳ የሆነችው ኦምዱርማን ከተማ ነዋሪ የሆኑት አል ተይብ ሼክ ኢድሪስ በጦርነቱ ውስጥ መጾሙ አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻሉ።

«እንዲህ ባለው ሁኔታ ረመዳን በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ሆኖም ስለሁሉም ነገር ፈጣሪ ይመስገን። ጦርነቱም ለበጎ ነው የመጣው። በመሠረቱ ሰዎች ወደዚህ ጦርነት ውስጥ ባይገቡ ኖሮ ነገሮች እንደውም በጭራሽ አይስተካከሉም ነበር። ጦርነቱ አእምሯችንን ከፍቶልናል፤ እናም ሁኔታችንን እንድናውቅ አድርጎናል። በፈጣሪ ፈቃድም የወደፊት ሕይወታችንን ማቃናት እንድንችል መንገድ አመላክቶናል።»

የሱዳንን ተፋላሚዎች የሚያነጋግሩት አሜሪካ እና ሳውድ አረቢያ ሁለቱም ኃይሎች ዳግም ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንዲመለሱ እየጠየቁ ነው። ሆኖም ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ውይይቶችም ሆኑ የተደረጉ ጥረቶች እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላስገኙም።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ