ስለፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ግድያ የፖለቲከኞች አስተያየት
ዓርብ፣ ሚያዝያ 4 2016ባለፈው ማክሰኞ ሚያዚያ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ሌሊት ተገድለው ረቡዕ ጠዋት አስከሬናቸው ከትውለድ አከባቢያቸው መቂ ከተማ ወጣ ባለ መንገድ ተጥሎ የተገኙት የፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ኅልፈትን ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሐዘናቸውን ገልጸዋል ። ፖለቲከኛውን በቅርበት የሚውቁና አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ፖለቲከኞች የአገሪቱ የፖለቲካ አውድ ለሰላማዊ ትግል በሁነኛ መንገድ የሚታገድ ሰው ነው ያጣው ይላሉ ። መሰል የፖለቲከኞች ግድያ በየትኛውም አቅጣጫ ለሚታገል የፖለቲካ አውድ ፋይዳ የሌለው ሲሉ ተችተዋልም ።
ፖለቲከኛው በትግል ጓዶቻቸው ዕይታ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሰሞኑ የተገደሉትን የፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ ኅልፈትን ተከትሎ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ አሰቃቂ ያለውን የፖለቲከኛውን ግድያ አውግዟል ። ሟች ፖለቲከኛውን በቅርበት እንደሚያውቃቸው የሚገልጹት የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ፖለቲከኛ ደስታ ድንቃ አቶ በቴ ሐሳብን የማይፈሩ ከየትኛውም አመለካከት ጋራ ለመነጋገር ዝግጁነት የነበራቸው ሲሉ ገልጸውአቸዋል ።
«በቴ ዑርጌሳን ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በቅርበት አውቀዋለሁ ። በንግግር የሚምን በሳል ፖለቲከኛ ከመሆኑም ባሻገር የተለያየ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋራ በቀላሉ መነጋገር የሚችል ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቁርጠኛ የሆነ ሰው ነበር» ብለዋል ።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹም አቶ በቴን የገለጹት እንዲህ ሲሉ ነው፦ «በቴን የማውቀው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ነው ። ባጣሙን ተባባሪ መናገር የምፈልገውን ሁሉ ፊትለፊት የሚናገር ቅን ፖለቲከኛ ነበር ። ፖለቲከኛው ለአገር ይጠቅማል ብሎ ይዞ በተነሳው የፖለቲካ አስተሳሰቡ ምክኒያት ከሥራ መባረር እስከ ቤተሰቦቹን ጥሎ መታሰር የተለያዩ መከራዎች የተፈራረቁበትም ነው» ብለው ግድያውም ለየትኛውም ፖለቲካ ትቅም የሌለው ብለውታል ።
የሰላማዊ ፖለቲካ ተከታዮች ግድያ ጦስ
መሰል በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፖለቲከኞች ላይ የሚፈጸም ግድያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ ጉልህ ነው የሚሉት ፖለቲከኞቹ ። ድርጊቱ በማንም ይፈጸም በማን በዚህ መንገድ ተጠቃሚ የሚሆን አካልም ሆነ የፖለቲካ መስመር አይኖርም ሲሉም ተደምጠዋል ። ፖለቲከኛ ደስታ «ድርጊቱ ሕጋዊና ሕገመንግስታዊ የፖለቲካ ትግል ላይ ጠባሳ የሚሳርፍ፤ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉቱ ላይ መሸማቀቅን የሚፈጥር» ሲሉ.. ፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ በፊናቸው «በግድያ እና መሰል መንገዶች የሚቀየር ነገር ባለመኖሩ ስለ እውነት ፊት ለፊት በመነጋገር ብቻ ችግሮችን ለመፍታት መጣር ይበጃል» ነው ያሉት ። አክለውም ግድያው ለማንኛውም የፖለቲካ መንገድ ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደማያመጣ ገልጸው፤ መንግስት በማያሳማ አኳሃን ገለልተኛ በሆነ አካል ሂደቱን አጣርቶ ፍትህ እንዲያሰጥም ጠይቀዋል ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የፖለቲከኛውን መገደል ተከትሎ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ የፀጥታ አካላት ስለግድያው ሙሉ ምርመራውን እስኪያደርጉ የትኛውንም አካል ተጠያቂ ማድረግ እንደማይገባ ዐስታውቆ መንግስት ሂደቱ ስጠናቀቅ የምርመራውን ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ ማሳወቁ አይዘነጋም ።
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ