የሸዋል ኢድ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ሀረሪዎችን አስደስቷል
ሐሙስ፣ ኅዳር 27 2016የሸዋል ኢድ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ማዕከል ዩኒስኮ በመመዝገቡ የሀረሪ ነዋሪዎች ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። የማስመዝገብ ሂደቱ አምስት አመታትን መወሰዱን የተናገሩት የክልሉ ባህል ፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው እውቅናው ለክልሉ እና ለሀገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አስረድተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርዲን በድሪ ሀረርን - በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ከተማ ሲሉ ደስታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልፀዋል።
የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በዓለሙ የቅርስ መዝገብ
የሀረር ከተማ ነዋሪው ወጣት ዲኔ አብዱከሪም የሀረሪዎች ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓል የሆነው የሸዋል ኢድ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ማዕከል ዩኒስኮ በመመዝገቡ ደስታውን በመግለጽ በዓሉ ወጉን ጠብቆ እንዲቀጥል እኛ ወጣቶች የበኩላችንን እንወጣለን ብሏል ።
አስተያየቷን የሰጠችው ሌላኛዋ የሀረሪ ወጣት ደሀብ አብዲ "ማንነታችንን የምናሳይበት የሸዋል ዒድ በዓል በዩኒስኮ መመዝገቡ ትልቅ ደስታ ነው የሰጠኝ " በማለት ደስታዋን በመግለፅ ለክልሉ ቱሪዝም እድገት ጠቃሚ ነው ብላለች።
የሀረሪ ክልል ባህል ፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ የሸዋል ዒድ በዓለም አቀፉ ተቋም እውቅና አግኝቶ እንዲመዘገብ ማድረግ "ቀላል ሂደት አይደለም" ሲሉ ሂደቱ አምስት አመታትን መፍጀቱን አስረድተዋል።
ሀረሪዎች የታላቁ ረመዳን ወር ፃም ማብቃቱን ተከትሎ ካለው አንድ ሳምንት በኃላ በጀጎል ውስጥ በድምቀት የሚያከብሩት ይህ የሸዋል ዒድ በዓል በዓለም አቀፉ የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ማዕከል ዩኒስኮ መመዝገቡ ባህሉን ከትውልድ ትውልድ ለማሸጋገር እና ለክልሉ እና ለሀገሪቱ የቱሪዝም እድገት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በማበራዊ ትስስር ገፃቸው በዓሉ በዓለም የማይደሰስ ቅርስነት በመመዝገቡ ደስታቸውን በመግለፅ ምዝገባው እንዲሳካ አስተዋፅኦ አድርገዋል ላሏቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የሸዋል ዒድ አከባበር
ሀረሪዎች በተለይም የብሄሩ ወጣቶች በጉጉት ጠብቀው የሚያከብሩት ዓመታዊ በዓል ነው - ሸዋል ዒድ።ከምሽት አንስቶ እስከ ንጋት በሀረር ጀጎል ውስጥ በሚከበረው በዚህ በዓል ዋዜማ በተለይ ወጣቶች ልዩ ተሳትፎ ሲኖራቸው ሁሉም በአንድነት በባህላዊ አልባሳት ተውበው በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ። ባህላዊ ጨዋታዎች እና ሃይማኖታዊ ዝማሬዎች የበዓሉ ደማቅ ድባብ መገለጫዎች ናቸው። በዚህ በዓል ወጣቶች ይተጫጩበታል።
ከትውልድ ትውልድ ሲሻገር ከዛሬ የደረሰውን ለሀረሪዎች ልዩ መገለጫ የሆነው የሸዋል ዒድ በዓልም በአለም አቀፉ የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ማዕከል እውቅና እንዲያገኝ ሲደረጉ የቆዩ ጥረቶች ሰምረው ትናንት ምዝገባው ይፋ ሲደረግ ሁሉም ደስታቸውን ገልፀዋል።
በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች በኢትዮጵያ የመጀመርያዋ ከተማ ሲሉ ሀረርን ያወዱሱት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንኳን ደስ አለን ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል። ወትሮም የቱሪስት ማዕከል ለሆነችው ሀረር የሸዋል ዒድ በአለም አቀፉ ተቋም አሁን ያገኘው እውቅና ከተማይቱን የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ያደርጋል የሚል እምነት ፈጥሯል።
መሳይ ተክሉ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ