1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል እየተስፋፋ የመጣ ሕገወጥ የማዕድን እና መሬት ወረራ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 1 2016

በትግራይ ክልል ሕገወጥ የመዓድን እና መሬት ወረራ አሳሳቢ መሆኑን የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ገለፀ። ፓርቲው በሕገወጥ የመዓድን ብዝበዛ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት እና ታጣቂዎች በቀጥታ ተሳታፊ ናቸው ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወረራ ተስፋፍቷል ያሉ ነዋሪዎች ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/4eaMx
Äthiopien | Tigray Region
ምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ የማዕድን እና ህገ ወጥ የመሬት ወረራ አሳሳቢ ሆኗል

በትግራይ ክልል ሕገወጥ የመዓድን እና መሬት ወረራ አሳሳቢ መሆኑን  የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ገለፀ። ፓርቲው በሕገወጥ የመዓድን  ብዝበዛ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት እና ታጣቂዎች በቀጥታ ተሳታፊ ናቸው ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወረራ ተስፋፍቷል ያሉ ነዋሪዎች ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ።

በተለይም በጦርነቱ ወቅት እና ከጦርነቱ በኃላ ባለው ግዜ በትግራይ እየተንሰራፋ እንደሆነ የሚገለፅለት ሕገወጥ የማዕድናት ማውጣት ስራ እና የመሬት ወረራ፥ በሕብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ እየፈጠረ ይገኛል።

የትግራይ ጡረተኞች አቤቱታቸው መልስ ማግኘት ጀመረ

በተለይም እምቅ የወርቅ ሀብት ባለባቸው የትግራይ ሰሜን ምዕራብ እና ማእከላዊ ዞን አካባቢዎች በርካቶች ከአስተዳደር ፍቃድ አግኝተው ሌሎች ያለፍቃድ በወርቅ ቁፋሮ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የሚገለፅ ሲሆን ማዐድኑ ለመቀራመት በሚደረግ እንቅስቃሴ ታጣቂዎች ጭምር የሚታኮሱበት ሁኔታ መኖሩ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር በዚህ የወርቅ ማዕድን ቅርምት እጃቸው እንዳለበት በትግራይ የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚው ፖለቲካ ፓርቲ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ አስታውቋል።

በትግራይ የተንሰራፋው ይህ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ስራ ትግራይን ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋርጥ ሲሉ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ኮምኒኬሽን ሐላፊ አቶ ገብረስላሴ ካሕሳይ ይገልፁታል። "በአንዳንድ ባለስልጣናት መሪነት እየተደረገ ያለው ሕገወጥ የወርቅ ማውጣት ስራ አሳሳቢ እና ትግራይን ወደ አደገኛ ሁኔታ እየዳረገ ያለ ነው" ሲሉ አቶ ገብረስላሴ ገልፀዋል።

የብልጽግናና የህወሓት ባለሥልጣናት ዉይይት

ከዚህ በተጨማሪ የኮምኒኬሽን ሐላፊው በወርቅ ማዕድን ቅርምት ላይ ታጣቂዎች ጎራ ለይተው የሚታኮሱበት ሁኔታ መኖሩ ያነሳሉ። "አንድ ላይ ሆነው ፀረ ጠላት የተዋደቁ ታጋዮች፥ የአንዳንድ ባለስልጣናት የግል ገቢ ለማሳደግ፣ የግል ፍላጎት ለማሳካት ተብሎ በዚህ የወርቅ ማውጣት ስራ ላይ እርስበርሳቸው እንዲጋደሉ እየተደረገ ነው። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት መጥፎ ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም የፓርቲያችን ማእከላይ ኮሚቴ አሳስቧል" ብለዋል።

በትግራይ አሁን ላይ ባለው ገበያ የአንድ ግራም ወርቅ ዋጋ እስከ 8 ሺህ ብር ይሸጣል። ከጦርነቱ በፊት በነበረ ግዜ ትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የወርቅ አቅራቢ ነበረች።

የፌዴራል መንግስት የአማራ ታጣቂዎችን «ከምዕራብ ትግራይ» ለማስወጣት መግባባት ላይ ተደርሷል፤ አቶ ጌታቸው ረዳ

በሌላ በኩል በክልሉ በስመ ኢንቨስትመንት የሚደረግ የመሬት ወረራ ጉዳይም አሳሳቢ ሆኖ እንዳለ በተለያዩ አካላት ይገለፃል። በኢንቨስትመንት ስም ይደረጋል ያሉት የመሬት ወረራ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ባለፈው ሳምንት በትግራይ ደቡባዊ ዞን መኮኒ የተደረገ ሲሆን፥ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች በአካባቢያቸው መሬት አጥተው እየተሰደዱ መሆኑ፥ ይሁንና ኢንቨስተሮች የተባሉ የተለየ ሀብት ይሁን ቴክኖሎጂ ሳያቀርቡ መሬት መቆጣጠራቸው ፍትሐዊ አይደለም ብለዋል።

በጦርነት የተጎዱት የትግራይ ክልል የጤና ተቋማት

ከአካባቢው ያነጋገርናቸው አቶ ሀፍቱ ካሕሳይ በአብዛኛው መሬቱ የተቆጣጠሩት "ኢንቨስተር ናቸው" ማለት የማይቻል፣ እንደ ነባሩ ገበሬ የክረምት ዝናብ ጠብቆ የሚዘራ፣ የስራ ዕድል የማይፈጥር ነው ይሉታል። አስተያየት ሰጪው ጨምረውም የአካባቢው ህዝብ እያነሳው ያለው የፍትህ ጥያቄ ነው ይላሉ።

በዚህ የሚነሳ የመሬት ወረራ እንዲሁም የማዕድናት ምዝበራ ጉዳይ ዙርያ ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልሰመረም።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ታምራት ዲንሳ 

ሸዋዬ ለገሰ